ፈልግ

ር.ሊ.ጳ. ሊዮ በስፔን የሚያደርጉትን ጉብኝት በማስመልከት በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ መነኮሳት የተለያዩ መቁጠሪያዎችን እያዘጋጁ እንደሆነ ተነገረ ር.ሊ.ጳ. ሊዮ በስፔን የሚያደርጉትን ጉብኝት በማስመልከት በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ መነኮሳት የተለያዩ መቁጠሪያዎችን እያዘጋጁ እንደሆነ ተነገረ 

ር.ሊ.ጳ. ሊዮ በስፔን የሚያደርጉትን ጉብኝት በማስመልከት መነኮሳት የተለያዩ መቁጠሪያዎችን እያዘጋጁ እንደሆነ ተነገረ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሚቀጥለው ወር መጀመሪያ ላይ በስፔን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት በአስር የሚገመቱ በሃገሪቱ የተለያዩ ገዳማት ውስጥ ያሉ መነኮሳት በሺዎች የሚቆጠሩ መቁጠሪያዎችን እያዘጋጁ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ አነስተኛ መጠን ያላቸው እነዚህ በእጅ የሚሰሩ መቁጠሪያዎች በጸጥታ፣ በጸሎት፣ በእጅ ጥበብ እና በወጣት በጎ ፈቃደኞች እርዳታ የተሰሩ መሆናቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 እነዚህ በማይታይ ክር እና ከእንጨት ዶቃዎች በእጅ ጥበብ የተሰካኩ የተስፋ መቁጠሪያዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በሃገሪቷ የሚያደርጉትን ሃዋሪያዊ ጉብኝት በማስመልከት በጸጥታ ውስጥ የሚሰሩ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ የእነዚህ መቁጠሪያዎች ሥራ አጀማመር በካስቲል፣ ናቫሬ፣ ካታሎኒያ እና አንዳሉሺያ ከተሞች ውስጥ ተበታትነው በሚገኙት የመነኮሳት ገዳማት ውስጥ እንደሆነ እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ አሥራ አራተኛን ሃዋሪያዊ ጉብኝት በተስፋ የሚጠባበቁ ምዕመናን ዘንድ መድረሱም ጭምር ተነግሯል።

ከክር እና ከእንጨት ዶቃ በመነኮሳቱ የተሰሩት መቁጠሪያዎቹ በኪስ ውስጥ የሚያዙ አነስተኛ መጠን ያላቸው መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጉብኝት በማስመልከት በጣም ትርጉም ካላቸው ምልክቶች ውስጥ አንዱ ይሆናሉ ተብሎም ይጠበቃል ተብሏል።

ከእያንዳንዱ መቁጠሪያ ዶቃ ጀርባ የተደበቀ ህይወት፣ ዝቅ ያለ እና ትሁት ድምፅ፣ በይፋዊ መርሃ ግብሮች ወይም በቴሌቭዥን ምስሎች ላይ የማይታይ የፍቅር ኃይል መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፥ ስፔን የሆነ ወቅት ላይ በቅርበት የምታውቀውን እና አሁን የተረሳ የሚመስለውን ዓለም በጨረፍታ ሊመለከተው የሚቻልበት በእነዚህ መቁጠሪያዎች በኩል እንደሆነ ተመላክቷል።

ለዓመታት የተረሱ ማህበረሰቦችን በእደ ጥበባት ሥራ፣ ከምንም በላይ ከሚጎበኟቸው ሰዎች ጋር በሚመሰርቱት መንፈሳዊ ትስስር ወይም ከገዳሙ ደጃፍ ባሻገር በሚገኘው የተደበቀ ውበት በኩል ገዳማዊያቱ እራሳቸውን እንዲደግፉ የሚረዳው ‘ኮንቴምፕላር ፋውንዴሽን’ (Fundación Contemplare) የተባለ ትስስር ባልደረባ የሆኑት አሌጃንድሮ ሲሞን ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት በሃገራቸው ከሰባት መቶ በላይ ገዳማት እንዳሉ ገልጸው፥ “እኛ በዓለም ላይ ካሉት የታላላቅ ገዳማት እውነታዎች መካከል አንዱ ነን” በማለት አስረድተዋል።

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉዞ ላይ መሳተፍ

ገዳማቱ ከዓለም የተገለሉ ሳይሆኑ፥ ይልቁንም ከችኮላ እና ከጩኸት አመክንዮ ውጭ የሆኑ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጩኸቶችን የሚያስተጋቡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሃዋሪያዊ ጉብኝት በሚደረገው ዝግጅት በኩል ትኩረትን እንደሚያገኙም ጭምር ተገልጿል።

የመቁጠሪያው ሃሳብ የተጠነሰሰው ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሃዋሪያዊ ጉብኝት ጋር አብሮ መሄድ የሚችል ቀላል እና ትሁት የሆነ ነገርን የመስራት ተፈጥሮአዊ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የኮንተምፕላሬ ፋውንዴሽን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብዙ ሺ መቁጠሪያዎችን ማምረት ይቻል እንደሆነ ለመጠየቅ በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ ገዳማትን በማነጋገር ያገኘውን ፈጣን መልስ ተከትሎ የተጀመረ ሃሳብ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

የፋውንዴሽኑን ጥያቄ ተከትሎ ሁሉም ገዳማት አዎንታዊ መልስ መመለሳቸውን ያስታወሱት አቶ ሲሞን፥ ጥቂት አባላት ያላቸው ገዳማት ሳይቀሩ ለዚህ ትልቅ ለሆነ ጥያቄ እሺታቸውን የገለጹት በዚህ ሥራ በኩል በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሃዋሪያዊ ጉዞ  ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ስለተረዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በገዳማቱ ውስጥ ያለው የሥራ ዘይቤ መለወጡን ያስታወሱት የፋውንዴሽኑ ባልደረባ፥ የሰም እና የእንጨት ሥራ ማዕከሎች፣ የስፌት ክፍሎች እና የእጅ ጥበብ ስቱዲዮዎች በመነኮሳቱ እና ገዳማዊያቱ ብርቱ ልፋት መዘውተራቸውን ገልጸው፥ የተወሰኑት መነኮሳት ዶቃዎቹን ሲሰበስቡ፣ ሌሎች ደግሞ መቁጠሪያዎቹ የሚከፋፈሉበትን መስቀሎች ወይም ትናንሽ የጨርቅ ቦርሳዎችን በማዘጋጀት እንደተጠመዱ አስረድተዋል።

የበጎ ፈቃደኞች አስተዋፅዖ

በበርካታ ገዳማት ውስጥ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ይሄንን ሥራ ለመርዳት መምጣታቸውን የጠቆሙት ሲሞን፥ ከእነዚህም ውስጥ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ቤተሰቦች እና የሰበካ ቡድኖች ከመነኮሳቱ ጋር በጸጥታ ለመተባበር ገዳሙ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸው፥ አብዛኛዎቹ የገዳሙን ህይወት ለመጀመሪያ ጊዜ ማየታቸውን አመላክተዋል።

“በጎ ፈቃደኞቹ ከዚህ በፊት ከማያውቁት ዓለም ጋር እንደተገናኙ” የገለጹት አቶ ሲሞን፥ “በዚህ ስፍራ ጊዜ ሌላ ዜማ ያለው፣ ያለ ጭንቀት ሥራ የሚሰራበት እና ዝምታ ባዶነት ሳይሆን መገኘት የሆነበት ዓለም” እንደሆነ መገንዘባቸውን አስታውሰዋል።

መቁጠሪያዎቹ የቅንጦት ዕቃዎች ሳይሆኑ፥ አብዛኛዎቹ ከቀላል እንጨት፣ ከገመድ እና ከትናንሽ የብረት መስቀሎች የተሠሩ፥ ነገር ግን ዋጋቸው በትህትና ውስጥ የሚገለጹ መሆናቸው የተመላከተ ሲሆን፥ እያንዳንዱ ሰው ይህን ለመገንዘብ ሥራው የወሰደውን ጊዜ፣ ጸሎት እና ለዚህ ሥራ የተከፈለ የተደበቀውን መስዋዕትነት ማየት እንደሚገባው ተገልጿል።

ለእነዚህ ማህበረሰቦች የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ከብሔራዊ ክስተት በላይ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን፥ የብፁዕነታቸው ጉብኝት አብዛኛውን ጊዜ በዝምታ፣ በማስተዋል እና በችግር ውስጥ የሚገኙ፥ ነገር ግን አሁንም ድረስ በሥራ የሚታይ የመነኮሳት ህይወት እንዳለ ህብረተሰቡን ለማስታወስ እድሉን እንደሚያመቻች ተገልጿል።

በስፔን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ገዳማት ከእድሜ መግፋት፣ ከኢኮኖሚያዊ ችግር እና ከሥራ እጦት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚሰሩ የተገለጸ ሲሆን፥ አንዳንዶቹ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በቅርብ ዓመታት ውስጥ የመዘጋት እድል ያጋጠማቸው እንደሆነ እና ሌሎቹ ድግሞ የተለያዩ ጣፋጭ ምግቦችን፣ ባህላዊ ልብሶችን፣ መንፈሳዊ ቁሳቁሶችን፣ ሳሙናዎች ወይም ሌሎች በእጅ የተሰሩ ምርቶች በመሸጥ ከመዘጋት መትረፋቸው ተገልጿል።

የጸሎት ትስስር

ሆኖም ግን እነዚህ ገዳማት ምንም እንኳን ደካማ ቢሆንም በርካታ አማኞች አሁንም ድረስ አስፈላጊ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩትን የማይታይ የጸሎት ትስስር ማስቀጠላቸው የተነገረ ሲሆን፥ አቶ ሳይመን ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት ‘ለበሽታ፣ ለቤተሰብ ሁኔታ፣ ለሥራ አጥነት እና ብቸኝነትን በተመለከተ ጸሎት እንዲያደርጉላቸው ዘወትር የሚጠይቋቸው ሰዎች እንዳሉ’ ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት ገዳማቱ ብዙ ጊዜ የማይታይ ትልቅ መንፈሳዊ ሸክም እንደሚሸከሙ አስረድተዋል።

በዚህ ምክንያት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ ጉብኝት የሚዘጋጁት መቁጠሪያዎች ከቀላል የአምልኮ ዕቃዎች በላይ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህ ይልቅ በቤተክርስቲያኑ እና በህብረተሰብ ውስጥ የሚገኝ ድብቅ የመነኮሳት ህይወት መገኘት ምልክት መሆናቸው ተመላክቷል።

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በሺዎች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን ከእነዚህ መቁጠሪያዎች ውስጥ አንዱን በእጃቸው የሚቀበሉ ሲሆን፥ እነዚህ መቁጠሪያዎች ከየት እንደመጡ የሚያውቁት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ፥ ጥቂቶች የመኖኮሳቱን ዝምታ፣ ታጋሽ የሆኑ የአረጋውያን እጆች ወይም ሥራውን አስመልክቶ በቀስታ የሚደረጉ ንግግሮችን ብቻ ሊገምቱ ይችላሉ ተብሏል።

ነገር ግን በእያንዳንዱ መቁጠሪያ ውስጥ የዚያ ስውር የሆነ ዓለም የሆነ ምልክት እንደሚኖር እና የገዳማዊያቱ ጸሎት ከግድግዳቸው ጀርባ ሆነው የቤተክርስቲያንን ጉዞ አጅበው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።  

 

05 Jun 2026, 14:36