በጋዛ ያሉ ህፃናት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላን እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊን ሲቀበሉ በጋዛ ያሉ ህፃናት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላን እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊን ሲቀበሉ  

የኢየሩሳሌም ፓትርያርኮች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የጋዛ ምዕመናንን መጎብኘታቸው ተነገረ

የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሣልሳዊ በጦርነት ወደተዳከመው ጋዛ በመጓዝ ከካህናት፣ ከሀይማኖት ማህበረሰቦች፣ ከአካባቢው የክርስቲያን ቤተሰቦች እና በጋዛ ሰርጥ በሰብዓዊ ቀውስ ከተጎዱ ሰዎች ጋር መገናኘታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከባድ መከራ ውስጥ የሚገኙትን በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናትን ለመጎብኘት እና ለማጽናናት የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሣልሳዊ ከሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ጋዛ በመጓዝ ሃዋሪያዊ ጉብኝት የጀመሩ ሲሆን፥ ከሁለቱ ፓትሪያርኮች ጋር የማልታ ሉዓላዊ ማህበር አባል የሆኑት ዶክተር ጆሴፍ ብሎትዝ እና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ክልሎች ውስጥ በእርዳታ ሥራዎች የሚንቀሳቀሰው ‘ማልታዘር ኢንተርናሽናል’ የተሰኘው የማህበሩ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተወካዮች መጓዛቸው ተገልጿል።

ሃዋሪያዊ አጋርነት
ይሄንን ሃዋሪያዊ ጉብኝት በማስመልከት በወጣው መግለጫ የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ እንደገለጹት ይህ ጉብኝት ቤተሰቦች ከባድ ሰብዓዊ ስቃይ፣ ፍርሃት፣ ኪሳራ እና እርግጠኛ አለመሆን ስሜት ውስጥ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት በመደረጉ የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናት ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና ለመላው የጋዛ ሕዝብ ያላቸውን ሃዋሪያዊ አጋርነት ያሳያል ያሉ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በመከራ በተሰበረ መንፈስ ውስጥ የጸሎትን የማይናወጥ ጠቀሜታ ጎላ አድርጎ ይገልፃል ብለዋል።

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ እና የብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በአከባቢው መገኘት ኢየሩሳሌም በጦርነቱ ለቆሰሉት ምዕመናን እና ስቃይ ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ፣ እንዲሁም በወንጌል ላይ በተመሰረተ የማጽናኛ፣ የምሕረት እና የጸና የክርስቲያን ምስክርነት አገልግሎት ውስጥ እና በቅድስት ከተማ የተቀደሰ ጥሪ ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ የምታደርገውን ጸሎት የሚያደርስ እንደሆነ ገልጸዋል።

የታደሰ ተስፋ
ይፋ በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ብፁዕ ካርዲናሉ እና ፓትርያርኩ ከካህናት፣ ከሃይማኖት ማህበረሰቦች፣ ከአካባቢው የክርስቲያን ቤተሰቦች እና በጦርነቱ ምክንያት ሰብዓዊ ቀውስ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር እንደሚገናኙ የተገለጸ ሲሆን፥ መንፈሳዊ መሪዎቹ በጸሎት እና በሃዋሪያዊ መገኘት አማካይነት መንፈሳዊ ጥንካሬን፣ መጽናናትን እና የታደሰ ተስፋን ለማቅረብ እንደሚፈልጉ ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ተልዕኳቸው አብያተ ክርስቲያናት ለጤና አጠባበቅ፣ ለእርዳታ ጥረቶች እና ለሰው ልጅ ክብር ጥበቃ ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጥ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

ደማቅ አቀባበል
መንፈሳዊ መሪዎቹ ለቅድስት ቤተሰብ የተሰጠው የላቲን ደብር መግቢያ በር ላይ ሲደርሱ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ እና ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ በጭብጨባ እና በታላቅ ደስታ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፥ የቁምስናው ካህን በሆኑት አባ ጋብርኤል ሮማኔሊ በተመራው የጸሎት እና የሰላምታ መርሃ ግብር በኋላ የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ምዕመናንን እና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚኖሩትን ብቻ ሳይሆን የዚህች መከራ የሞላባት ከተማ ነዋሪዎችንም ጭምር ማየት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

“ሁኔታው አሁንም ድረስ አስቸጋሪ ሆኖ ቀጥሏል” ያሉት ካርዲናሉ፥ ነገር ግን የቤተክርስቲያኑ መሪዎች በዚህ ቦታ መገኘት አብያተ ክርስቲያናት ለጋዛ ያላቸውን ትኩረት እና ስጋት እንደሚያሳይ እና ይህም ሁሌ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

ቀጣይነት ያለው ስጋት
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ከዚህን ቀደም ታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. የጋዛን ህዝብ ጎብኝተው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ከሁለት ቀናት በኋላ ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ብርሃነ ልደቱን በማስመልከት በቅድስት ቤተሰብ ደብር መስዋዕተ ቅዳሴን ማሳረጋቸው እና በበዓሉ ላይ በሥርዓተ አምልኮው እጅግ የተነኩ በርካታ ምዕመናን መገኘታቸው ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ሀምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. እስራኤል በቁምስናው ላይ ባደረሰችው ጥቃት ሶስት ሰዎች መሞታቸው እና ሌሎች አስራ አንድ ሰዎች መቁሰላቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ እና ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ ለተጎጂ ቤተሰቦች አጋርነታቸውን ለመግለፅ እና የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ለማግኘት በጋራ ወደ ጋዛ መጓዛቸው ይታወሳል።

በዚያን ጊዜ የተደረገው ጉብኝት በጦርነት ወቅት የተደረገ በዓይነቱ ልዩ እና የመጀመሪያ የሆነ የአቢያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጉብኝት ስለነበረ ታሪካዊ ተደርጎ ይቆጠር እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ ሁለቱ አባቶች በዚያ በነበሩበት ወቅት ጦርነቱን እንዲያስቆሙ እና ለመላው ቅድስት ሀገር የፈውስና የእርቅ መንገድ እንዲያስጀምሩ የዓለም መሪዎችን መማጸናቸው ይታወሳል።

23 Jun 2026, 15:06