የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት በጋዛ የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት በጋዛ  (ANSA)

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በጦርነት ውስጥ መጠቀምን የሚከለክል የጋራ ሰነድ በጄኔቫ መፈረሙ ተነገረ

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና መንግስታት ‘በወታደራዊ የግድያ ሰንሰለት’ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓቶችን “ማቅረብ እንዲያቆሙ” የሚያስገድድ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል "አስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ" የሚጠይቅ ሰነድ ላይ ከፈረሙት 226 ፈራሚዎች መካከል የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት አንዱ እንደሆነ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ‘የሚደገፍ’ ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የግድያ ዘዴን ‘በፍጥነት እና በመጠን’ እያሰፋው መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ በተመሳሳይ ጊዜ እነዚህ ለውጦች በዓለም አቀፍ ህግ ላይ ከሚያደርሱት ተግዳሮቶች የተነሳ የሚያስከትሉትን ገዳይ እና አስከፊ መዘዞች ለመከላከል የሚያስችል “ሙያዊ ወይም የአሰራር መፍትሄዎች” እንደሌሉ ተገልጿል።

ይህን አስቸጋሪ ዳራ በመቃወም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት (WCC) መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ማህበራትን፣ ባለሙያዎችን እና የቴክኖሎጂ ኩባንያ ተወካዮችን ጨምሮ ከሌሎች 225 ፈራሚ አካላት ጋር በመሆን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለጦርነት መጠቀምን የሚቃወም የጋራ ሰነድ አጽድቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ስብሰባ በጄኔቫ
ሰነዱ በግልጽ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ላይ ያሉ ኩባንያዎች እና መንግስታት “በወታደራዊ የግድያ ሰንሰለት” ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የታቀዱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶችን ‘ማቅረብ እንዲያቆሙ እና የሚያቀርቧቸው ማናቸውም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ እና ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግ ጥሰት ምክንያት ወይም አስተዋጽዖ እንዳያደርጉ ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ የሚያቀርብ መሆኑ ተገልጿል።

ሰነዱ ላይ የመፈረም ሥነ ስርዓቱ የተፈጸመው “ሰው ሰራሽ አስተውሎት በወታደራዊ መስክ እና ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ያለው አንድምታ” በሚል ጭብጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትጥቅ የማስፈታት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አማካይነት ከሰኔ 8 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በጄኔቫ በተካሄደው ስብሰባ ላይ መሆኑም ጭምር ተነግሯል።

ይህ ስብሰባ የተካሄደው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ‘ማግኒፊካ ሂዩማኒታስ’ ወይም ‘የሰው ልጅ ታላቅነት’ በሚል ባወጡት ሃዋሪያዊ መልዕክት ውስጥ ዓለም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚደገፍ ጦር መሳሪያ ከማምረት እንድትቆጠብ ጥሪ ካቀረቡ ከሳምንታት በኋላ እንደሆነ ተነግሯል።

የሰው ልጅን ሃላፊነት “የማቅለል” አደጋ
በሰነዱ መሠረት ከመንግሥታዊ ወታደራዊ ኤጀንሲዎች ጋር የሚዋዋሉትን ጨምሮ ሁሉም ኩባንያዎች ምርቶቻቸው እና አገልግሎቶቻቸው ከሰብዓዊ መብት ረገጣና ከዓለም አቀፍ ወንጀሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እና አስተዋጽዖ እንዳያደርጉ ወይም በቀጥታ እንዳይገናኙ የሚቻለውን ሁሉ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የሚያስገድድ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ “ኩባንያዎች እንደዚህ ያሉትን አደጋዎች መከላከል ወይም ትርጉም ባለው መንገድ ማቃለል በማይችሉበት ጊዜ እነዚህን ስምምነቶች መፈጸም እንደሌለባቸውም ጭምር የሚያስገድድ መሆኑ ተመላክቷል።

ሰነዱ የሚዲያ ዘገባዎችን እና የፔንታጎን ይፋዊ መግለጫዎችን በመጥቀስ፣ ለአብነትም ‘ፈጣን ኢላማዎችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያዎች አማካይነት መፈለግ አሜሪካ ኢራን ላይ የምትወስደውን ጥቃት ፍጥነት፣ መጠን፣ ስፋት እና የማጥፋት ሃይሉን እንዲጨምር አስችሏታል’ ያለ ሲሆን፥ በእስራኤል የጦር ኃይሎች ጥቅም ላይ የዋሉ ሥርዓቶችን በተመለከተም ተመሳሳይ ግምገማዎች ሊደረጉ እንደሚችሉም አክሏል።

ሰነዱ እንደገለጸው እንደነዚህ ያሉት ቴክኖሎጂዎች “በሕይወት እና በሞት በሚወስኑ ውሳኔዎች ውስጥ የሰውን ልጅ ኃላፊነት” የሚያቃልሉ እና ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን በግልጽ ከሚታየው ስልተ-ቀመር ተጨባጭነት ያለው ሽፋን ለመደበቅ እንዲሁም በተመሳሳይ ጊዜ ከተጠያቂነት ለማምለጥም እንደሚረዱ ገልጿል።

የኢሰብአዊነት አዝማሚያ
በሰነዱ ላይ የፈረሙ 226ቱ አካላት “በገሃዱ ዓለም ያለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ሁኔታ እንደሚያመለክተው የበለጠ አስከፊ፣ ሰብአዊነት የጎደለው እና አጥፊ የጦርነት ዘዴዎችን እያመቻቸ” መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን፥ ከእነዚህ ፈራሚ አካላት መካከል አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በርካታ የሃገር ውስጥ ቡድኖች እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ተቋማቱ በማከልም በተለይም ‘ግዙፍ የቋንቋ ሞዴሎችን’ (LLMs) የመሳሰሉ ሥርዓቶችን ኢላማን ለመፈለግ ተግባራት መጠቀሙ ወታደራዊ ተዋናዮችን ወደዚህ ዓይነት ጦርነት እየገፋ መሆኑ እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ፥ ልዩነት፣ ተመጣጣኝነት እና ቅድመ ጥንቃቄን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ መሰረታዊ መርሆች ላይከበሩ ይችላል በማለት ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

ፈራሚዎቹ የእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ፍጥነት እና ስፋት፣ የግብአት መረጃው ተዓማኒነት ከሌለው፣ አድሏዊ እና አብዛኛውን ጊዜ ከህግ ውጭ በሆነ መንገድ የመነጨ ባህሪ ጋር ተዳምሮ፣ እንደዚህ አይነት ስርዓቶች የሰብአዊ መብት ረገጣን፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እና የጦር ወንጀሎችን በማስፋፋት ላይ መሆናቸውን አስጠንቅቀው፥ ከዚህም በላይ በአጠቃቀማቸው ዙሪያ ያለው ግልጽነትን የማጣት ተግዳሮት ስህተቶች በሚከሰቱበት ጊዜ የሞራል ወይም ህጋዊ ሃላፊነትን የመወጣት እድልን በእጅጉ ይጎዳል ብለዋል።

በሰው ልጅ የሚከናወን ትርጉም ያለው ቁጥጥር
ሰነዱ በተጨማሪም ኢላማ ለማድረግ ጥቅም ላይ የሚውሉት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች የመጨረሻውን የመግደል ውሳኔ ባይወስኑም፣ መጠነ ሰፊ አውቶማቲክ የግድያ ማፅደቂያ ዘዴዎች ሊሆኑ ስለሚችሉ ትክክል ያልሆነ መረጃን በመስጠት የሰውን ሃላፊነት እና ትጋትን ሊያስወግዱ ይችላሉ ያለ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት የጅምላ ግድያዎችን ለማፋጠን እና ለማስፋፋት አስተዋፅዖ ያደርጋሉ ብሏል።

“እነዚህ ስርዓቶች የህይወት እና ሞት ጉዳዮችን ወደ ቀላል የመተግበሪያ መድረክ በመቀነስ ሰብዓዊነትን ያጎድላሉ” ያለው ሰነዱ፥ የሰውን ህይወት የማጥፋት ውሳኔ ጥልቅ የሞራል እና ህጋዊ ክብደት ስላለው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች የመነጩ ምክሮችን መቀበል ወይም አለመቀበል ወደሚሉ ውይይቶች ፈጽሞ መውረድ እንደሌለበት በአጽንዖት ገልጸዋል።

ወታደራዊ ሃይሎች በእንደዚህ ዓይነት ፍጥነት እና መጠን ዒላማዎችን ለመለየት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ሲተማመኑ የሰው ልጅ ሃሳቦች ችላ እየተባሉ እንደሚመጡ እና ጭካኔ የተሞላባቸው የጅምላ ጥቃቶች ሊከሰቱ እንደሚችል በማሳሰብ፥ በዚህም ምክንያት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ ላይ የተቀመጠው የቅድመ ጥንቃቄ መርህ በቀጥታ ይጣሳል ብሏል።

የላቀ ተጠያቂነት እና ግልጽነት
በጄኔቫ የተፈረመው ሰነድ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሰብአዊ መብት ረገጣን እና አሰቃቂ ወንጀሎችን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ህግን ሊጥሱ ከሚችሉ ወታደራዊ ኤጀንሲዎች ወይም ታጣቂ ቡድኖች ጋር ውል ከመግባት ወይም ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ያሳሰበ ሲሆን፥ መንግስታት በበኩላቸው ‘ትላልቅ የቋንቋ ሞዴሎችን’ ጨምሮ በወታደራዊ ኢላማ ተግባራት ላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያዎችን መጠቀም እንዲያቆሙ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግጋት እና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ህጎች መከበራቸውን እንዲያረጋግጡ በማሳሰብ፥ በአሁኑ ወቅት ያለውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን በተመለከተ ግልጽነትን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

17 Jun 2026, 13:22