ፍልሰት እና የካናሪ ደሴቶች፡ ከውርደት ወደብነት ወደ ተስፋ ወደብነት
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መስከረም 2017 ዓ.ም. ወደ ኢስያ እና ኦሺኒያ ካደረጉት ረጅሙ ሐዋርያዊ ጉዞ ሲመለሱ የስደተኞች እንክብካቤ የጵጵስናቸው አንዱ እና ዋናው ጭብጥ ስለነበረ የካናሪ ደሴቶችን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ይሄን ተከትሎ የካናሪያ ሀገረ ስብከትን ለመጎብኘት ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተፈረመ ደብዳቤ ደርሶት እንደነበር ቢገለጽም፥ ይሁን እንጂ አርጀንቲናዊው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጉዞውን ማጠናቀቅ ሳይችሉ ከዚህ ዓለም ድካም እንዳረፉ ይታወቃል።
ነገር ግን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ ጉብኝት ከተካሄደ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በኋላ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሞሮኮ የባህር ዳርቻ ወደሚገኙት የስፔን ደሴቶች በመጓዝ የብፁዕነታቸውን የረጅም ጊዜ ፍላጎት ያሟላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
አንድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በይፋዊ ሐዋርያዊ ጉዞ የካናሪ ደሴቶችን ሲጎበኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፥ ከቀደምት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ዮሃንስ ጳውሎስ 2ኛ እና ቤኔዲክት 16ኛ ወደ ስፔን በአጠቃላይ ስምንት ጊዜ ሲጓዙ፥ ዮሃንስ ጳውሎስ 2ኛ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በአቅራቢያው የምትገኘውን ሞሮኮን መጎብኘታችው ይታወሳል።
ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሃዋሪያዊ ጉብኝት በፊት ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የሃገረ ስብከቱ ሃዋሪያዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ እና የግራንድ ካናሪ ደሴቶች የሐዋርያዊ ጉዞ አስተባባሪ የሆኑት ኤኔሊዳ ሄርናንዴዝ ሞንዞን ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለዚህ ታሪካዊ ጉብኝት መነሻ የሆኑትን ስሜቶች አብራርተዋል።
ወይዘሮ ሄርናንዴዝ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ “ትልቅ ሥራ፣ ቅንጅት እና ትብብር” መኖሩን ገልጸው፥ ነገር ግን መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመው አንዳንድ ጥድፊያዎችም መኖራቸውን ጭምር ያስታወሱ ሲሆን፥ ነገር ግን በደስታ፣ በተስፋ እና በጉጉት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን መምጣት እየተጠባበቁ ስለሆነ ሥራው የበለጠ አስደሳች እንደሚሆን አመላክተዋል።
ድርብ የሆነ አስገራሚ አጋጣሚ
የካናሪ ደሴቶች ነዋሪዎች የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ሃዋሪያዊ ጉብኝት በተስፋ ሲጠባበቁ የነበረ ቢሆንም፥ ነገር ግን በአጭር ጊዜያት ይከሰታል ብለው እንዳልጠበቁ የገለጹት ዋና ጸሃፊዋ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለብዙ ጊዜያት ለመምጣት ፍላጎት እንደነበራቸው የሚያውቀው የአከባቢው ህዝብ በአሁኑ ሃዋሪያዊ ጉብኝት ግን በጣም መገረማቸውን ገልጸው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተመረጡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እነዚህን ደሴቶችን ለመጎብኘት መወሰናቸው “ድርብ የሆነ አስገራሚ ሁኔታ እና ድርብ ደስታ” ማስከተሉን አስረድተዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የካናሪ ደሴቶችን መጎብኘት “በጣም ትልቅ ትርጉም አለው” ያሉት አስተባባሪዋ፥ ምክንያቱም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት “ሁሉንም ክርስቲያኖች በእምነታቸው እንዲጠነክሩ ስለሚያደርግ፥ በመንፈሳዊ ጉዟቸው ላይ ማረጋገጫ ስለሚሰጥ እና ለወንጌል በመስራት ተልዕኳቸውን እንዲቀጥሉ ስለሚያበረታታ መሆኑን አመላክተው፥ ጉብኝቱ “በካናሪ ደሴቶች ሀገረ ስብከት ውስጥ ለብዙ መቶ ዘመናት ሲከናወን የነበረውን ሥራ ያረጋግጣል” ብለዋል።
የተስፋ ስብሰባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በቅድስት አኔ ካቴድራል ውስጥ ከካህናት፣ ከገዳማዊያት እና ከሃዋሪያዊ አገልግሎት ሠራተኞች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ፣ በግራን ካናሪያ ስታዲየም መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያሳርጉ፣ ምናልባትም በላስ ፓልማስ ደ ግራን ካናሪያ ውስጥ በጣም ከሚጠበቁት ክስተቶች ውስጥ አንዱ የሆነው በአርጊኒጊን ወደብ ላይ ከሚገኙ ስደተኞች ጋር አብረው ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር ቆይታ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
እ.አ.አ. በ 2020 ዓ.ም. ከጀልባው የመሸከም አቅም በስድስት እጥፍ የሚበልጥ ከ 2,600 የሚበልጡ ስደተኞች በአከባቢው ምንም ዓይነት መሰረተ ልማት በሌለበት እና አደገኛ ሙቀት በነበረበት ሁኔታ በካምፕ ውስጥ እንዲሰፍሩ መደረጉ የሚታወቅ ሲሆን፥ በደሴቶቹ ላይ የሚሰፍሩት ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም በቂ አገልግሎት እንደማያገኙና በዚህም ምክንያት ወደቡ ‘የውርደት ወደብ’ ተብሎ እንደሚጠራ ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚህ ሃዋሪያዊ ጉዞዋቸው ይሄንን ወደብ እንደሚጎበኙ ወይዘሮ ሄርናንዴዝ የጠቆሙ ሲሆን፥ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጀልባዎች የተለያዩ ስደተኞችን በባህር ዳርቻዎቹ ካደረሱ በኋላ ከፍተኛ ስቃይና በደል እንደሚደርስባቸው ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና በስደተኞች መካከል የሚደረገው ግንኙነት በህይወት ዘመን ውስጥ አንድ ጊዜ የሚያጋጥም ብቻ ሳይሆን ጥሩ ዕድል እንደሆነም ጭምር አመላክተዋል።
የተሻለ ነገር ፈልገው እና ተስፋ ሰንቀው ከሃገራቸው የሚወጡት ስደተኞች ባረፉበት በዚህ ስፍራ የሚደረገው ጉብኝት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለስደተኞቹ ያላቸውን አጋርነት ያሳያል ያሉት ሄርናንዴዝ፥ ስደተኞቹ እራሳቸው በወደቡ ላይ ለሚገኙ ስደተኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ ድርጅቶች ማለትም ከሀገረ ስብከቱ ካሪታስ እና ከስደት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከተለያዩ ስደተኛ ማህበረሰቦች ጋር ለመስራት ከቆረጡ የተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፍራው ለሚያደርጉት ጉብኝት ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ገልጸዋል።
አንድ የካናሪያን ማህበረሰብ
ካናሪ ደሴቶች ለሚደርሱ አንዳንድ ስደተኞች እምነት ወይም ሃይማኖት ማለት ወደ ውህደት እና ወደ አዲስ ህይወት በሚያደርጉት ጉዞ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነገር መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪዋ፥ ቀደም ሲል ክርስቲያን ያልነበሩ አንዳንድ ሰዎች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እምነቱን በጥልቀት መቀበላቸውን አስታውሰው፥ በዚህም ወቅት የመለወጥ ሂደትን ማለፋቸውን ገልጸዋል።
እነዚህን ጨምሮ ሌሎች 50,000 የሚሆኑ ሰዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሚመሩት እና ከምሽቱ 11 ሰዓት አከባቢ በግራን ካናሪያን ስታዲየም በሚካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት ስደተኞቹ ልዩ የአምልኮ ጊዜን እንደሚያሳልፉ ተገልጿል።
ሄርናንዴዝ አሁን በምንገኝበት ዓለም አውድ ውስጥ ክርስቲያኖች ሁል ጊዜ ለመስማት ተስፋ የሚያደርጉት እና ብፁዕነታቸውም ያነሱታል ተብሎ የሚጠበቀው መልዕክት በመንፈሳዊ እድገታችን እንድንገፋ፣ እምነታችንን፣ ተስፋችንን እና ምጽዋታችንን ማጠናከር እንድንቀጥል የሚያበረታታ ነው ያሉ ሲሆን፥ ለራሳችን እና ለመጭው ትውልድ ብሎም ለቤተሰቦቻችን እና ጓደኞቻችን እንዲሁም ልናገኛቸው ለማንችላቸው ሰዎች የተሻለ ዓለም እንድንፈጥር ተጠርተናል ያሉት አስተባባሪዋ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሚያሳርጉት መስዋእተ ቅዳሴ “መልካም ማድረግ፣ ሌሎችን ማገልገል፣ አቅመ ደካሞችን እና የተቸገሩትን መደገፍ” ለሚለው ዓለም አቀፋዊ ጥሪ ማሳሰቢያ ይሆናል ብለዋል።
ወይዘሮ ሄርናንዴዝ የስታዲየሙ ዝግጅት ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን፥ ክርስቲያን ባልሆኑ ሙስሊሞች እንዲሁም የተለያዩ እምነቶች እና ሃይማኖታዊ ልማዶች ተወካዮች እንደሚሞላ ገልጸው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጉብኝት የአንድነት ብሎም ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን የተለያዩ ሰዎችን በእምነት እና በተስፋ መንገድ ላይ የመሳብ አንዱ ምልክት ነው ያሉ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ከትውልድ አገራቸው ወደ ካናሪ ደሴቶች የተጓዙት ስደተኞች አንድ ተጨማሪ የካናሪያን ማህበረሰብ አካል ይሆናሉ ብለዋል።
ለሌሎች ተምሳሌት መሆን
በአጠቃላይ በደሴቶቹ ላይ ያለውን የፍልሰት ሁኔታ ስንመለከት፥ የሀብት ውስንነት በሚታይበት እና ፖሊሲዎች አሁን ካሉት ፍላጎቶች ጋር በተሻለ ሁኔታ መላመድ በሚገባቸው በአሁኑ ወቅት ‘መሻሻል እየታየ እና ሰዎች ድጋፍ እያገኙ እንደሆነ’ ያመላከቱት ሄርናንዴዝ፥ የካናሪ ደሴቶች በተቋማት እና በቤተክርስቲያን ድርጅቶች አማካይነት ስደተኞችን ከአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር ለማዋሃድ ለሚደረገው ጥረት ጥሩ ተምሳሌት እንደሆኑ አስታውሰዋል።
ብቻቸውን ወደ ስፍራው የሚደርሱ ታዳጊዎች በቋንቋ ስልጠናዎች እና በልማት ተነሳሽነት ውስጥ እንደሚሳተፉ የገለጹት ሄርናንዴዝ፥ በላስ ፓልማስ ደሴት ውስጥ የሚገኝ የአንድ መንደር ሕዝብ ቁጥር መመናመኑን በምሳሌነት አቅርበው፥ ነገር ግን በአንድ ወቅት መላው ማህበረሰቡ ከአካባቢያቸው ባለስልጣናት ጋር በመሆን ቤተሰብ የሌላቸውን ስደተኛ ታዳጊዎችን ሲቀበሉ እንደነበር አስታውሰዋል።
እነዚህ ልጆች አካባቢውን የሚያነቃቁ እና ወደ መንደሩ የሚዋሃዱ ብቻ ሳይሆኑ፥ “ከሁሉም በላይ ታዳጊዎቹ ዳግመኛ ደስተኛ መሆን የሚችሉበትን መንገድ የሚያሳያቸው ቤተሰቦችን ማግኘታቸው እና ያጡትን ፍቅር እና እንክብካቤ እንደሚሰጧቸው ገልጸዋል።
ከእነዚህ የታዳጊዎቹ ቤተሰቦች መካከል አብዛኛዎቹ ይህ ስደት ለልጆቹ የተሻለ ሕይወት እንደሚያስገኝ በማሰብ ከባድ መስዋዕቶችን መክፈላቸውን የጠቆሙት ሄርናንዴዝ፥ በመጨረሻም እንደመታደል ሆኖ አብዛኛዎቹ ልጆች በደስታ በተቀበሏቸው የካናሪያን ቤተሰቦች በኩል ያንን እድል እንዳገኙ ገልጸዋል።