ፈልግ

በስፔይን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝትን የተደረገ ዝግጅት በስፔይን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝትን የተደረገ ዝግጅት   (ANSA)

ማድሪድ የ. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛን መምጣት እና እምነት ለማነቃቅት እየተጠባበቀች መሆኗ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ባከበሩባት ማድሪድ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ምዕመናንን በማበረታታት እምነትን እንደገና ለማደስ ተስፋ ማድረጋቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ መድረሻ ማድሪድ ቅዱስነታቸውን ለመቀበል ተዘጋጅታለች። ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተዋል፣ “ሊዮ 14ኛ” የሚሉ ጽሑፎች እና የቫቲካን ባንዲራ በከተማው ማዕከላዊ ጎዳናዎች ላይ ይታያል።

ቅዱስነታቸው ወደ ማድሪድ አየር ማረፊያ ከመድረሳቸው ከ24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የቅዱስነታቸው የስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና አስተባባሪ ፕሮፌሰር ያጎ ዴ ላ ቺየርቫ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፥ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በማድሪድ እና በስፔን ውስጥ ላሉ ሰዎች የተስፋ ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።

የስፔይን ጎዳናዎች በባንዲራዎች አሽበርቀው
የስፔይን ጎዳናዎች በባንዲራዎች አሽበርቀው   (AFP or licensors)

“ተስፋው ሁለት እጥፍ ነው” ያሉት ፕሮፌሰር ያጎ ዴ ላ ሲየርቫ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት የክርስቲያኖችን እና የካቶሊካዊ ምዕመና መንፈሳዊ ሕይወት ያጠናክራል” ብለው፥ ሁለተኛው ደግሞ ከእምነት ለራቁት ወይም ስለ እምነት ፈጽሞ ያሰሙት በሙሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ፣ ሰላምን እና ደስታን እንደሚያገኙ ጥሪ የሚያቀርብ ይሆናል” ብለዋል።

የእምነት መነቃቃት

ስፔይን በአንድ ወቅት በርካታ ካቶሊካዊ ምዕመናን የነበሩባት አገር ስትሆን፥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የምዕመናን ቁጥር በተከታታይ እየቀነሰ መምጣቱ ተነግሯል። 52% የሚሆኑት ካቶሊኮች እንደሆኑ ቢነገርም ነገር ግን ከእነዚህ መካከል 15% የሚሆኑት ብቻ እምነቱን እየተለማመዱ እንደሚገኙ ተነግሯል። ፕሮፌሰር ዴ ላ ሲየርቫ በቃለ ምልልሳቸው፥ ይህ የእምነት መዳከም በስፔን ብቻ ሳይሆን በመላው አውሮፓ የሚታይ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ “የስፔይኑ ቆይቶ የጀመረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ፍጥነቱ እየጨነረ መጥቷል” ሲሉ አስረድተዋል።

የሚጠመቁት ሕጻናት ቁጥር ከ50% በታች ወርዷል ያሉት ፕሮፌሰር ዴ ላ ሲየርቫ፥ በቤተ ክርስቲያን የሚጋቡት ከ20% ያነሱ ቢሆኑም ስታትስቲክስን ብቻ መመልከት እንደማይገባ አሳስበው፥ ቁጥሮችን መመልከቱ ሁሉም ጨለማ እና አሳዛኝ እንደሚያስመስል ገልጸው፥ ባሁኑ ወቅት ብዙ አዳዲስ ተቋማት፣ አዳዲስ እና በእውነት ንቁ የሆኑ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና ቁምስናዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

በስፔይን የጥምቀት ምስጢርን የሚቀበሉ ሰዎች
በስፔይን የጥምቀት ምስጢርን የሚቀበሉ ሰዎች

ይህም በዋና ከተማዋ ማድሪድ ውስጥ በግልጽ እንደሚያታይ ተናግረው፥ በማድሪድ ሀገረ ስብከት ውስጥ አሥራ ሁለት አዳዲስ ቤተ ክርስቲያናትን እየተገነቡ እንደሚገኝ፥ ከዚህም በላይ በከተማው ውስጥ የክርስትና ሕይወት እያደገ እንደሚገኝ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማድሪር እንዲጀምሩ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል። ማድሪድ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በብዛት ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል አንዷ እንደ ሆነች እና የክርስትና ሕይወት ሕያው እንደ ሆነም አስረድተዋል።

ከዚህም በላይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዘወትር ልዩ ምልክት ትቶ የሚያልፍ እና ማድሪድም ከዚህ የተለየች አይደለችም ብለው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አምስት ጊዜ እንደጎበኟት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ሦስት ጊዜ እንደጎበኟት አስታውሰው፥  በዚህም የእምነት መነቃቃት ልምድ እንዳላቸው አፅንዖት ሰጥተዋል።

አዳዲስ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ በላይ የለጋሾች ቁጥር መጨመር እና ወላጆች በትምህርት ቤቶች የሃይማኖት ትምህርት እንዲሰጥ የሚያቀርቡት ጥያቄ የማኅበረሰቡን ሐዋርያዊ ጉዞ እንደገና እያነቃቃ እንደሚገኝ ገልጸው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2011 ዓ. ም. የታየው ይህ ለውጥ በያዝነው ዓመትም እንደገና እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ፕሮፌሰር ደ ላ ሲየርቫ ተናግረዋል።

ፖለቲካ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ነገ የሚያገኟት ስፔይን በካቶሊክ እምነት ጥልቅ ሥር የሰደደች እንደምትሆን ሲነገር፥ አገሪቱ ለዘመናት ያህል በካቶሊክ ነገሥታት ትተዳደር እንደ ነበረች እና መንግሥቱም በካቶሊክ ሃይማኖት ይቋቋም እንደ ነበር ይታወሳል።

እንደ አብዛኛዎቹ አገራት ዛሬ በስፔይን ቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት የተለያዩ ቢሆኑም ነገር ግን በተለያዩ ዘርፎች እና ጉዳዮች ላይ አብረው ሊሠሩ እንደሚችሉ ታውቋል። የአሁኑ መንግሥት እና ቤተ ክርስቲያን ወደ ስፔይን ለሚመጣ እያንዳንዱ ስደተኛ አስፈላጊነት እንክብካቤ ሊሰጠው እንደሚገባ መስማማታቸውን ፕሮፌሰር ደ ላ ሲየርቫ ጠቁመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገሪቱ እጅግ ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ እንደሚካሄድ አፅንዖት ሰጥተው፥ ቅዱስነታቸው ፖለቲከኞ አብረው እንዲሠሩ፣ ለጋራ ጥቅም እንዲቆሙ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለማውጣት  እንደሚያበረታቱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ማድሪድን በጎበኙበት ወቅት
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ማድሪድን በጎበኙበት ወቅት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ብዙ ጊዜ ያልተለመደውን የፓርላማ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ የገለጹት ፕሮፌሰር ደ ላ ሲየርቫ፥ በተመረጡ ባለስልጣናት፣ በንጉሡ፣ በንግሥቲቱ እና በሌሎች ፖለቲከኞች ፊት ንግግር ማድረግ “የአዲስ ተስፋ ምልክት” ነው ሲሉ ተናግረዋል።

15 ዓመታት ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲመለከቱ

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ከ15 ዓመታት በፊት በማድሪድ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን መርተዋል። በወቅቱ የተመረጠው ዋና ጭብጥ “በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር በመስደድ በእምነት መጽናት” የሚል ነበር እና ወጣቶች አዲሱ የወንጌል ስርጭት  ወኪሎች እንዲሆኑ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ከሁለት አሥርት ዓመታት ገደማ በኋላ፥ በቅርቡ የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቴክኖሎጂ በሚመራ ዓለም ውስጥ ወጣቶች እንደገና የወደፊት ተስፋ መሆናቸው ታውቋል። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥር እየቀነሰ ባለበት ወቅት ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ ወጣቶች ለካቶሊክ እምነት ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን፥ የቅዱስነታቸው የስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና አስተባባሪ ፕሮፌሰር ያጎ ዴ ላ ቺየርቫ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል። 

 

06 Jun 2026, 15:45