ፈልግ

እህት አኔ ኢሊያ በባርሴሎና፥ ስፔን እህት አኔ ኢሊያ በባርሴሎና፥ ስፔን   (©Servants of the Sacred Heart of Jesus)

በባርሴሎና የሚኖሩ አንድ ኬንያዊት እህት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሃገሪቱ ያደረጉት ጉዞ ተሃድሶን እንዲያመጣ ጸሎት እንደሚያደርጉ ገለጹ

በባርሴሎና እየኖሩ እና እየሰሩ የሚገኙት የቅዱስ ልበ ኢየሱስ አገልጋዮች ጉባኤ አባል የሆኑት ኬንያዊት እህት አኔ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በባርሴሎና እና በስፔን ያደረጉት ጉብኝት ለሁሉም ሰው የመታደስ ጊዜ እንዲሆን ጸሎት እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ ስፔን በታሪክ በዓለም ዙሪያ በርካታ ሚስዮናውያንን የላከችበትን መንገድ አስመልክተው፣ እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ ህይወታቸው እና አገልግሎታቸው የተመሰረተው በዚህ የእምነት ስጦታ መሆኑን አስመልክተው ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በባርሴሎና ውስጥ ያላቸው ተልዕኮ የሰጣቸውን ደስታ የገለጹት እህት አኔ ኢሊያ፥ ለመጀመሪያ ጊዜ እምነትን ከሰጠቻቸው ቤተክርስትያን ጋር በመስራታቸው እና በመተባበራቸው ስላገኙት ሙልአት የገለጹ ሲሆን፥ ስፔን የክርስቶስን ወንጌል እንዲሰብኩ ሚስዮናውያንን በዓለም ዙሪያ ከላኩ የመጀመሪያዎቹ ሃገራት መካከል አንዷ እንደነበረች አስታውሰዋል።

እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ሰዎች እግዚያብሔርን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቁት በእነዚህ ሚሲዮናዊያን ምስክርነት እንደሆነ የጠቆሙት እህት አኔ፥ በአሁኑ ወቅት በሚያስገርም የእምነት ሽግግር በአንድ ወቅት እርሳቸውን ጨምሮ በእነዚያ ሚስዮናውያን ወንጌል የተሰበኩ ሰዎች አሁኑ ላይ እዚህ ተመሳሳይ የወንጌል ተልዕኮን ለመደገፍ እና ለመተባበር ወደ አውሮፓ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በባርሴሎና ውስጥ የምትገኝ ቤተክርስቲያንን እና ማህበረሰብን እያገለገሉ የሚገኙት በሃገሪቷ ውስጥ በሚገኝ አንድ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ በመምህርነት እንደሆነ የገለጹት እህት አኔ፥ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ህፃናትን እና ወጣቶችን ለማስተማር እና ለመደገፍ ራሳቸውን ሰጥተው እያገለገሉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በቁምስናቸው ውስጥ በሃዋሪያዊ ሥራዎች እያገለገሉ እንደሚገኝ የጠቆሙት እህት አኔ፥ እንደ ሙያዊ ተልዕኮዋቸው መምህር ሆነው በአካባቢው ያሉ ወጣቶችን በማስተማር፣ በመርዳት እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳየን ፍቅር መሰረት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን በፍቅር በመምራት ላይ እንደሚገኙ አክለው ገልጸዋል።

እ.አ.አ. በ 1891 ዓ.ም. በባርሴሎና ከተማ በስፔናዊው ካህን አባ ሁዋን ኮሌል የተመሰረተው የቅዱስ ልበ ኢየሱስ አገልጋዮች ማህበር በትምህርት፣ በወጣቶች እድገት እና በማህበራዊ ደህንነት ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት እህት አኔ፥ “እኛ የቅዱስ ልበ ኢየሱስ አገልጋዮች የክርስቶስን የፍቅር እና የርህራሄ መንገድ በመከተል የተቸገሩትን ለማገልገል ቁርጠኞች ነን” ብለዋል።

‘ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ብቻችንን እንዳልሆንን ያስታዉሱናል’
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በባርሴሎና ያደረጉትን ሃዋሪያዊ ጉብኝት አስመልክቶ ያላቸውን ሃሳብ የተጠየቁት እህት አኔ፥ የቅዱስ አባታችን ጉብኝት የሁሉንም ሰዎች እምነት እንደሚነካ እና እንደሚያድስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በከተማዋ መገኘት ከዚህ በተሻለ ተስፋ እና ድፍረት እንዲሞላቸው፥ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታቸው የበለጠ እንዲገኝ ማድረግ እንዲችል ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

እህት አኔ አክለውም ‘ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ባርሴሎናን በሚጎበኙበት ወቅት ቤተክርስቲያን ጥልቅ የሆነ የልብ መታደስ እና የእምነት መጠናከር እንደምታገኝ’ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ከቤተክርስቲያኑ የራቁ ወይም ግድዬለሽ የሆኑ ሰዎች የባለቤትነት ስሜትን እና ደስታን ዳግመኛ እንዲያገኙ፣ ብሎም አዲስ ህይወትን እና ቅድመ ሁኔታ የሌለውን የክርስቶስን ፍቅር እንዲለማመዱ ጥልቅ የሆነ የለውጥ ጎዳናን እንደሚያመጣላቸው ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ይህ ወቅት ወጣቶች ለጋብቻ ሕይወት፣ ለተቀደሰ ሕይወት ወይም በዓለም ውስጥ ላላቸው አገልግሎትም ይሁን በሌላ ለሚደረግላቸው የእግዚአብሔር ጥሪ በድፍረት እና በጨዋነት ምላሽ እንዲሰጡ ያነሳሳቸዋል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ “የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቃል እና መገኘት እኛ ብቻችንን እንዳልሆንን መላውን ቤተክርስቲያን ሊያስታውስ እንደሚችል አምናለሁ” ብለዋል።

“እኛ በጸሎት፣ በተልዕኮ እና በክርስቶስ ፍቅር አንድ በመሆን የአንድ ሁለንተናዊ ቤተሰብ አካል ነን” ያሉት እህት አኔ፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ ጉብኝት በአጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት፣ በገዳማዊያን ማህበረሰቦች፣ በምዕመናን እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን መንፈሳዊ ቁርኝት እንደሚያድስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

እህት አኔ በመጨረሻም ሃዋሪያዊ ጉብኝቱ ሁላችንም በየዕለቱ ከእኛ ጋር ወደሚጓዘው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንመለከት ይረዳናል ካሉ በኋላ፥ “የብፁዕነታቸው ድምጽ በእኛ ዘመን የፍትህ እና የሰላም ጥሪ እንዲሆን እጸልያለሁ” በማለት አጠቃለዋል።

16 Jun 2026, 15:09