እህት ሴሊና ምቡሊ እና የጤና ማዕከሉ ሰራተኞች የህብረት ምልክትን ሲያሳዩ እህት ሴሊና ምቡሊ እና የጤና ማዕከሉ ሰራተኞች የህብረት ምልክትን ሲያሳዩ  

በኬንያ የሚገኙ የምሕረት እህቶች በአከባቢው የሚገኙ ሰዎችን ህይወት እና ነባራዊ ሁኔታ እየቀየሩ መሆኑ ተነገረ

በኬንያ ሰሜናዊ ምስራቅ በምትገኘው፣ ከመሃል ከተማው ራቅ ወዳለው እና በረሃማው የሎኮሪ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የሎድዋር ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የምሕረት እህቶች ጉባኤ አባላት የአከባቢውን ማህበረሰቦችን የኑሮ ሁኔታ እየለወጡ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በአብዛኛዎቹ ከፊል ዘላኖች የሆኑ በአንዳንድ የኬንያ በጣም ተጋላጭ ህዝቦች መካከል ሰብዓዊ ክብርን እየመለሱ እንደሆነም ጭምር ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሎድዋር ሀገረ ስብከት በሃዋሪያዊ እና በማህበራዊ ሥራዎች ውስጥ በስፋት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የምህረት እህቶች ገዳም አባል የሆኑት እህት ሴሊና ምቡሊ ተልዕኮዋቸውን አስመልክተው እንደተናገሩት በሎኮሪ ግዛት ውስጥ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎችን ጨምሮ ለአርብቶ አደር ቤተሰቦች፣ ተጋላጭ ለሆኑ ህፃናት እና አረጋውያን ወሳኝ የሆኑ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአከባቤ ህሙማን በአንድ ወቅት ግጦሽ እና ውሃ ፍለጋ የሚንቀሳቀሱ ዘላን ቤተሰቦችን የሚያገለግሉ ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮችን ጨምሮ በሎኮሪ የምህረት እህቶች ጤና ጣቢያ ውስጥ አጠቃላይ የሆነ እንክብካቤን ያገኙ እንደነበር ያስታወሱት እህት ሴሊና፥ በአሁኑ ወቅት ይህ አሰራር ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ከስፍራው መልቀቅን ተከትሎ የገንዘብ ድጋፍ በመቋረጡ ምክንያት በአገልግሎታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸው፥ ጠንካራ የጤና ባለሙያዎችን በመመልመል እና በማሰልጠን በአገልግሎታቸው ውስጥ አቋቁመው የነበረ ቢሆንም አብዛኛዎች በአሁኑ ወቅት በደመወዝ መቀነስ እና የተሻለ እድልን ለመፈለግ ከማዕከሉ ለቀው እየወጡ እንደሆነ ያስረዱ ሲሆን፥ ጉባኤው እነዚህን የመሳሰሉ ፈተናዎች ቢኖሩበትም ለኤችአይቪ ተገልጋዮች የተቀናጀ አገልግሎት በመስጠት ድጋፍ ማድረጉን ቀጥሏል ብለዋል።

ኤች አይ ቪን ለመዋጋት ከጊዜ ጋር የሚደረግ ውድድር
በየዓመቱ የሎኮሪ ጤና ጣቢያ የዓለም የኤድስ ቀንን የመድሀኒት እና የምግብ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ጤናን በተመለከተ የተለያዩ ትምህርቶችን በመስጠት እንደሚያከብር የጠቆሙት እህት ሴሊና፥ ኤች አይ ቪን ከህዝብ ጤና ስጋትነት ለማስወገድ ያለመው ዓለም አቀፍ የ 2030 ግብን ለማሳካት ጥቂት ዓመታት ብቻ እንደሚቀሩም ጭምር ገልጸዋል።

“አሁንም ድረስ ከጊዜ ጋር እየተሽቀዳደምን ነው” ያሉት እህት ሴሊና፥ ኤች አይ ቪ በአከባቢው እጅግ መንሰራፋቱን ጠቁመው፥ በበሽታው ተይዘው በህክምና ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚደርስባቸው መገለልን እና የተለያዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በምክር፣ በህክምና ተግባራት እና በተለያዩ ተነሳሽነቶች በኩል በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

መተዳደሪያን በማቅረብ ማህበረሰቦችን ማበረታታት
የምህረት እህቶች ከጤና አጠባበቅ ባሻገር ድህነትን፣ ረሃብን እና ጥገኝነትን ለመቅረፍ የገቢ ማስገኛ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ከ290 በላይ አባላት እና አሥር ቡድኖችን ያቀፈ ‘ሲልክ’ (SILC) የተሰኙ ቡድኖችን የመሳሰሉ የቁጠባ እና የብድር ማህበረሰቦችን በማቋቋም አባላቱ በመሰረታዊ የፋይናንስ እውቀት፣ የሥራ ፈጠራ ክህሎት እና አነስተኛ ብድር እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሎኮሪ ዳቦ መጋገሪያ ቤት ማቋቋማቸውን እና ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመው፥ በዚህም መሰረት “ሰዎች እድገታቸውን በባለቤትነት እንዲይዙ እና ክብራቸውን እንዲመልሱ እንፈልጋለን” ብለዋል።

ከበረሃነት ወደ አረንጓዴነት፡ የሎኮሪ አረንጓዴ ልማት ተነሳሽነት
በላውዳቶ ሲ' አነሳሽነት እንዲሁም ለሰዎችም ሆነ ለአካባቢ ጥበቃ ማድረግ ላይ በመመስረት የምህረት እህቶች ጉባኤ ገዳማዊያት የሎኮሪ አረንጓዴ ልማት ተነሳሽነትን የጀመሩ ሲሆን፥ በዚህም ተነሳሽነት ሁለቱንም ሥነ-ምህዳራዊ እንክብካቤ እና ግላዊ ፈውስን እንደሚያበረታቱ እህት ሴሊና ገልጸው፥ ተነሳሽነቱን የጀመሩት ድንጋያማ እና ባዶ በሆነ መሬት ላይ እንደሆነ እና በጋራ በመሆን አፈር ማስገባታቸውን፣ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ ዘላቂ የግብርና አሰራርን መጀመራቸውን፣ በርካታ ዛፎችን መትከላቸውን እና በአሁኑ ወቅት 41 ቀፎዎች ያሉት የንብ እርባታ ሥራ መጀመራቸውን አብራርተዋል።

ትምህርት እና ጥበቃ፡ የሚቀጥለውን ትውልድ መደገፍ
ከዚህም ባሻገር ገዳማዊያት እህቶቹ ትምህርትን በማስፋፋት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመቅረፍ እና ወጣቶችን በማብቃት ረገድ በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ የገለጹት እህት ሴሊና፥ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በመተባበር ልጃገረዶችን ከግዳጅ ጋብቻ እንደሚታደጉ እንዲሁም በአንዳንድ ተቋማት ድጋፍ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እርዳታ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለከብት አርቢዎቹ ልጆች የሚያገለግሉ ትምህርት ቤቶችን እንደሚያስተዳድሩ ጠቁመው በእነዚህ የትምህርት ማዕከላት ውስጥ ቀን ቀን ከብት የሚጠብቁ ሴት እና ወንድ ህፃናት ማታ ላይ ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ገልጸው፥ በትምህርት አማካኝነት ማህበረሰቦችን እንደሚያበረታቱ አመላክተዋል።

በአንድ ወቅት ላይ የከብት እረኛ የነበረው ሲልቬስተር ሎኩቶ በአሁኑ ወቅት የ ‘ሎኮሪ አረንጓዴ ልማት ተነሳሽነት’ አስተባባሪ ሲሆን፥ ይሄንን ትምህርት ቤት ሲቀላቀል ገዳማዊያት እህቶቹ የአካዳሚክ አቅሙን ተገንዝበው እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በመደበኛ ትምህርት እንደደገፉት የገለጸ ሲሆን፥ የምህረት እህቶች ጉባኤ ገዳማዊያት በህይወቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ጠቅሶ ይሄንን ብድራት ለመመለስ እና ማህበረሰቡን ለማገልገል ወደ ማዕከሉ መመለሱን ገልጿል።

ለዚህ ተግባር የተነሳሳበትን ምክንያት የተጠየቀው ሲልቬስተር፥ ህዝቡን ለማነሳሳት ባለው ፍላጎት እና ጥልቅ ፍቅር መሆኑን አስረድቶ፥ ህልሙ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ እና አካባቢን ለመጠበቅ ‘የሎኮሪ አረንጓዴ ልማት ተነሳሽነት’ ወደሁሉም የማህበረሰቡ ክፍል ሲደርስ ማየት እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በበተጨማሪ በአከባቢው የሚገኙ ሰዎች ውሃ ለማግኘት ረጅም ርቀት ስለሚጓዙ እና ይሄንን ችግር የሚቀርፍ የውሃ ጉድጓድ እንዲኖራቸው ያለውን ተስፋ ገልጿል።

በምህረት ላይ የተመሰረተ ተልዕኮ
ይሄንን ተከትሎ በሎኮሪ ግዛት የተወሰነ መሻሻሎች ቢኖርም የውሃ እጥረት አሁንም ድረስ አንገብጋቢ ፈተና መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ሴቶች ቀኑን ሙሉ በጠራራ ፀሀይ ውሃ ለመቅዳት ረጅም ርቀት እንደሚጓዙ እና ይህ ሁኔታ ለተለያዩ አደጋዎች እንደሚያጋልጣቸው፣ ብሎም ምርታማነትን እንደሚቀንስ ተገልጿል።

ሴቶቹ ጠዋት ላይ ሲጸሊዩ አግኝተዋቸው ስለምን እንደሚጸልዩ የጠየቋቸው እህት ሴሊና፥ ውሃ ለማግኘት እየጸለዩ እንደሆነ መናገራቸውን አስታውሰው፥ በአቅራቢያቸው የሚገነባ አንድ የውሃ ጉድጓድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ህይወት እንደሚለውጥ አስረድተዋል።

ለእህት ሴሊና ይህ ሥራ ከአገልግሎትም በላይ ጥሪ እንደሆነ ጠቁመው፥ የምሕረት እህቶች ጉባኤ አባላት ፍቅር እና ቸርነት በእጅጉ እንዳበረታታቸው የገለጹ ሲሆን፥ በአከባቢው የተተከሉ ዛፎች እያደጉ፣ልጆች እየተማሩ እና ሕይወታቸው እየታደሰ በመሆኑ ጉባኤው በሎኮሪ ያለውን ተጽእኖ ማየት እንደቻሉ ገልጸዋል።

የእሳቸው ራዕይ እያንዳንዱ ልጅ የትምህርት እድል የሚያገኝበት፣ ኤች አይ ቪ ስጋት የማይሆንበት እና የአከባቢው ማህበረሰቦች ራሳቸውን ችለው የሚኖሩበትን ጊዜ መሆኑን ጠቁመው፥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል እና ወደፊት መጓዝ እንደሚገባ በማሳሰብ አጠቃለዋል።

18 Jun 2026, 13:25