የሆንግ ኮንግ እና የማካው ብፁዓን ጳጳሳት ወደ ሮም ያደረጉት የአድ ሊሚና ጉብኝት የሆንግ ኮንግ እና የማካው ብፁዓን ጳጳሳት ወደ ሮም ያደረጉት የአድ ሊሚና ጉብኝት  

የሆንግ ኮንግ እና የማካው ጳጳሳት በአድ ሊሚና ጉብኝት ወቅት ሲኖዶሳዊነት እና ተስፋን አስመልክተው ሃሳባቸውን አጋርተዋል

የሆንግ ኮንግ እና የማካው ብፁዓን ጳጳሳት ወደ ሮም ባደረጉት የአድ ሊሚና ጉብኝት ወቅት የሚስዮናውያን ተሃድሶን፣ የቤተ ክህነት ህብረት እና የሲኖዶሳዊው የህይወት ተሞክሮን በውይይት፣ በማዳመጥ እና በማስተዋል በኩል ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ቆይታ ማድረጋቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

‘አድ ሊሚና’ ተብሎ የሚታወቀው የካቶሊክ ጳጳሳት በየአምስት ዓመቱ ወደ ሮም የሚያደረጉት ወቅታዊ እና ይፋዊ ጉብኝት ሲሆን፥ በዚህም ብፁዓን ጳጳሳቱ በቅድስት መንበር ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና ከቫቲካን ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ስለ ሀገረ ስብከታቸው ሁኔታ እና በቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩ፣ ብሎም በቅዱስ ጴጥሮስ እና ጳውሎስ መቃብር ሥፍራ ተገኝተው ጸሎት እንደሚያደርጉ ይታወቃል።

ይሄንን ተከትሎ የሆንግ ኮንግ እና የማካው ብፁዓን ጳጳሳት ቫቲካንን በጎበኙበት ወቅት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት ቀደምት አባቶችን ስለማመስገን፣ የሚስዮናውያን ተሃድሶን አስፈላጊነትን እና ስለ ሲኖዶሳዊነት የህይወት ተሞክሮ ላይ ውይይት ማድረጋቸው እና በሮም በነበራቸው የአድ ሊሚና ጉብኝት ወቅት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እንዲሁም ከተለያዩ የቅድስት መንበር ጽህፈት ቤቶች ጋር በመገናኘት ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን ጋር የነበራቸውን ጥልቅ ቁርኝት ገልጸዋል።

ይህ ጉብኝት የመጣው ሁለቱም አህጉረ ስብከቶች ጉልህ የሆነ ዓመታዊ ክብረ በዓሎቻቸውን እያከበሩ በሚገኙበት ወቅት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የማካው ሀገረ ስብከት የተመሰረተበትን 450ኛ ዓመቱን ሲያከብር፣ ሆንግ ኮንግ ደግሞ ወደ ሀገረ ስብከት ያደገበትን 80ኛ ዓመት እያከበሩ በሚገኝበት ወቅት መሆኑ ተነግሯል።

ሲኖዶሳዊነት
የሆንግ ኮንግ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ስቴፈን ቹ ሳኡያን ጉብኝቱን በሲኖዶሳዊ ዓይን በመመልከት እንደተናገሩት ብፁዓን ጳጳሳቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ባደረጉት ውይይት የነበረውን የጋራ መደማመጥ አጉልተው ያሳዩ ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ በሆንግ ኮንግ እና ማካው ቤተክርስቲያናት ‘ጎንግ ዪ ቶንግ ዢንግ’ በሚል አገልግሎት ላይ የዋለውን ቻይንኛ የሲኖዶሳዊ ትርጉም እትም ለቅዱስ አባታችን እንዳበረከቱላቸው ብፁዕ ካርዲናሉ አመልክተዋል።

“የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቃላት አንድ ላይ መነጋገርን፣ መወያየትን እና አንድ ላይ ማስተዋልን ያመለክታል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ስቴፈን፥ የመጨረሻዎቹ ሁለት ቃላት ደግሞ አብሮ መራመድን እና መጓዝን የሚያመላክት እንደሆነ ጠቅሰው፥ ‘ስለዚህ ይህ ሲኖዶሳዊነት ምን እንደሆነ ሙሉ መግለጫ የሚሰጥ ይመስለኛል’ ብለዋል።

ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር የተደረገው ግንኙነት ስለ ሲኖዶሱ ሂደት ያለውን ግንዛቤ በትክክል ያሳያል ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ ወደ ቅድስት መንበር በመምጣታችን ልምዳችንን ለቅዱስ አባታችን ለማካፈል እድሉን ሰጥቶናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አዳማጭ እንደሆኑ እና ብፁዓን ጳጳሳቱን ለማዳመጥ ይሄንን እድል ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ብሎም እነሱም ከብፁዕነታቸው ጋር ሃሳባቸውን ለመካፈል እድሉን ማግኘታቸው በጣም ጠቃሚ ነገር እንደሆነም ጭምር ብፁዕ ካርዲናሉ አስረድተዋል።

እንዲህ ዓይነት መደማመጥ የቤተክርስቲያኗን ግንዛቤ እና ተልዕኮ እንደሚያገለግል ያስታወሱት ካርዲናሉ፥ በተለይም በቻይና ያለችውን ቤተክርስቲያንን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ “በዚህ መንገድ ቤተክርስቲያንን በመምራት የተሻለ ማስተዋልን ይሰጣል” ብለዋል።

በዚህ ጊዜ ብፁዓን ጳጳሳቱ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ተስፋ እና ስጋት ማዳመጥ እንደቻሉ የጠቆሙት ብፁዕ ካርዲናል ስቴቨን፥ “ጭንቀታቸውን፣ ፍላጎታቸውን እና ማብራራት የፈለጉትን ጉዳይ ስናዳምጣቸው ከእኛ የተሻለ ማብራሪያ ያገኛሉ” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ስቴቨን ከሆንግ ኮንግ እና ማካው ልምድ በመነሳት እንዲሁም ከቻይና ጋር ከነበራቸው የረጅም ጊዜ ግንኙነት በመነሳት ከቅዱስ አባታችን ጋር አመለካከቶችን እና ልምዶችን መካፈል አስፈላጊ መሆኑን ያሳሰቡ ሲሆን፥ በዚህ መንገድ ልምዶቻቸውን፣ አመለካከቶቻቸውን እና መረዳታቸውን ለእርሳቸው ሊያካፍሉ እንደሚችሉ እና ይህ አካሄድ ሲኖዶሳዊነትን እንደሚያመላክት ጠቅሰው፥ “ይህ ለእኛ እጅግ አስፈላጊ ነበር ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

የመታደስ ጭብጥ
የማካው ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ስቴፈን ሊ ቡን-ሳንግ በበኩላቸው ዓመታዊ ክብረ በዓሉ የተመሰረተው በምስጋና እና በታደሰ ሚስዮናዊ ቁርጠኝነት ላይ እንደሆነ አስታውሰው፥ ሃገረ ስብከቱ የተመሰረተበትን 450ኛ ዓመትን ሲያከብር ‘ተሃድሶ’ ከጭብጦቹ ውስጥ አንደኛው እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ የኢዮቤልዩው የመጀመሪያ ገጽታ ቅዱስ ወንጌልን ከማካው ተነስተው ወደ መላው ኢስያ ላስተላለፉ የሚስዮናውያን ትውልዶች ምስጋና ማቅረብ እንደሆነ አመላክተዋል።

“450 ዓመታት ረጅም ጊዜ ነው፥ በሚስዮናውያኑ አማካይነት በርካታ ጸጋ የሰጠንን እግዚአብሔር ማመስገን አለብን” ያሉት ብፁዕ አቡነ ሊ ቡን ሳንግ፥ አብዛኛዎቹ ከማካው፣ ከዚያም በሩቅ ምሥራቅ አካባቢ ወደሚገኙ በርካታ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን ለማዳረስ ሕይወታቸውን መሥዋዕት ማድረጋቸውን ገልጸው፥ የሀገረ ስብከቱን መሪ ሃሳብ በማስታወስ ምዕመናን በ450 ዓመታት ውስጥ የእግዚአብሔርን መሐሪ ፊት ለማየት እንደተጋበዙ ተናግረዋል።

ወንጌልን ለማወጅ ከማካው የወጡትን ሰዎች ምስክርነት በመጠቆም፣ “በሚሲዮናዊያኑ እና በሰጠን ጸጋ አማካይነት የእግዚአብሔርን ምሕረት በእውነት ልናውቅ እንችላለን” ያሉት ጳጳሱ፥ ከዚህም ባሻገር በዓሉ ያለፈውን ጊዜ ለማስታወስ ብቻ እንዳልሆነ አሳስበው፥ ያለፈው መልካም እና ትርጉም ያለው ትውስታ ውስጥ ብቻ መቆየት እንደማይገባ፥ ከዚህም ይልቅ ወደ ፊት ለመጓዝ እና እራሳችንን ለማደስ መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል።

ይህ መታደስ ሁሉንም ምዕመናን ወደ ሚስዮናዊ ደቀ መዝሙርነት እንደሚመራ ጠቅሰው፥ በቅርቡ የተጠመቁትን ካቶሊኮች ጨምሮ ሁሉም ሰው ይሄንን የሚስዮናዊነት መንፈስ፣ ወንጌልን ለማስፋፋት እና በእግዚአብሔር መሐሪ ጸጋ እንደገና ለመጓዝ ከፍተኛ ጉጉት ሊኖረው ይገባል ካሉ በኋላ፥ “በቅድስናችን ብቻ ሳይሆን ወንጌልን ለማስፋፋት ባለው ሐዋርያዊ ቅንዓት እራሳችንን ማደስ የምንችለው በዚህ መንገድ ነው” ብለዋል።

የተስፋ መልዕክት
የሆንግ ኮንግ ረዳት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ በበኩላቸው በተመሳሳይ መልኩ በተልዕኮ እና በተስፋ ላይ በማንጸባረቅ የሆንግ ኮንግ ሀገረ ስብከት በተስፋ መሪ ቃል ወደ ሀገረ ስብከት ደረጃ ያደገበትን 80ኛ ዓመት በማክበር ላይ እንደሚገኝ ያስታወሱ ሲሆን፥ ‘የሃገረ ስብከቱ በዓል መሪ ሃሳብ የተስፋ መልዕክት’ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ተስፋ የሚሰጣቸውን ወንጌልን ከሚስዮናውያን መቀበላቸውን፣ ነገር ግን እነርሱ ደግሞ የማስተላለፍ ሀላፊነት እንዳለባቸው አመላክተው፥ የአድ ሊሚናን መንፈሳዊ ንግደት አስፈላጊነት ላይ በማሰላሰል “በጣም ልዩ ትርጉም ያለው ለእኛ በጣም ውድ ጊዜ ነው” በማለት ገልጸውታል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ ከጳጳሳዊ ጽህፈት ቤቶች እና ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ የዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን አካል የመሆን ጥልቅ ስሜት እንደተሰማቸው ገልጸው፥ ይህ ከዓለም አቀፋዊት ቤተክርስትያን ጋር የመተሳሰርን ልዩ ትርጉም እንደሚሰጣቸው እንዲሁም ከመላው ማህበረሰብ እና ከመላው የክርስቶስ መንጋ ጋር መተባበር አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በተልዕኮዋ እንድትጠነክር ያደርጋታል ብለዋል።

“ይህ ጉዞ የቤተክርስቲያኒቷ አካል መሆናችንን ያረጋግጥልናል” ያሉት ጳጳሱ፥ በርትተን ወደ ፊት እንድንቀጥል እና ከወንጌል የምናገኘውን የተስፋ ቃል ለሌሎች እንድናስተላልፍ ያበረታታናል ያሉ ሲሆን፥ መጪውን ጊዜ አስመልክተው የዛሬዎቹ ካቶሊኮች ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው አስምረውበት፥ ጉብኝቱን በእርግጥም ለእነሱ የእግዚአብሔር እቅድ እንደሆነ በማስታወስ፥ “እኛ እራሳችን በሆንግ ኮንግም ሆነ በሌላ ስፍራ ለሚመጡት ትውልዶች ሚስዮናውያን መሆን አለብን” በማለት አጠቃለዋል።

22 Jun 2026, 14:57