የአሜሪካ ካቶሊካዊ ምዕመናን የሞት ቅጣትን ለማስቀረት በመጣር ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ. ም. በአሜሪካ ግዛቶች 47 ወንዶች እና ሴቶች በሞት የተቀጡ ሲሆን፥ ይህም ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ከተፈጸሙት የሞት ቅጣቶች በእጥፍ እንደሚበልጥ ታውቋል። ክሪሳን ሜርፊ እንዳሉት፥ “በተለይ አሜሪካውያን የሞት ቅጣት እንዲቀር የሚያቀርቡት ጥያቄ እያደገ ባለበት ወቅት የታየ ከፍተኛ እና አሳዛኝ ተግባር ነው” ብለዋል።
የሞት ቅጣት እና ካቶሊካዊ አስተምህሮ
አሃዞችን ስንመለከታቸው በግዛቶቹ መካከል ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን የገለጹት ወ/ሮ ሜርፊ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. ከ 47 የአሜርካ ግዛቶች መካከል የሞት ቅጣትን ተግባራዊ ያደረጉት 11 ብቻ መሆናቸን እና በተቀሩት 39 ግዛቶች ውስጥ ምንም እንዳልተገበረ ገልጸው፥ በአሁኑ ጊዜ 23 ግዛቶች የሞት ቅጣን ማስቀረታቸውን አስረድተዋል።
በፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ እንደ ጎርግሮሳውያኑ 2025 ዓ. ም. 19 የሞት ቅጣት መፈጸሙን፥ ይህም በግዛቲቱ በየሁለት ሳምንት አንድ ሰው እንደሚገደል ገልጸው፥ እያንዳንዱ የሞት ፍርድ በንብረት ላይ የበለጠ ጉዳት በማስከተል በቤተሰቦች ላይ መበታተንን እንደሚያስከትል ወ/ሮ ሜርፊ ተናግረዋል።
“የሞት ቅጣት ለተጎጂዎች የቅርበት እና የፈውስ ስሜትን አያመጣም” ያሉት ወ/ሮ ሜርፊ፥ የበለጠ ዓመፅ እና ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረው፥ “ዓመፅ ዓመፅን ከመፍጠሩ በላይ ተጨማሪ ጉዳቶችን እና ሰለባዎችን ይፈጥራል” ብለዋል።
የሞት ቅጣት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን የሚቃረን ሲሆን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በቁ. 2267 (CCC) ላይ፥ “የሞት ቅጣት በሰው ልጅ የማይጣስ ክብር ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” ሲል ያስረዳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአሜሪካ-ኢሊኖይ ግዛት የሞት ቅጣት የቀረበት 15ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ 24/2026 በላኩት የቪዲዮ መልዕክት የሞት ቅጣትን ለማስወገድ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ በአሜሪካ እና በዓለም ዙሪያ የሞት ቅጣት እንዲወገድ ለሚጥሩት በሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረው፥ “ጥረታችሁ የእያንዳንዱ ሰው ክብር የበለጠ እውቅና እንዲያገኝ እና ሌሎችም ለተመሳሳይ ፍትሃዊ ዓላማ እንዲነሳሱ እጸልያለሁ” ብለዋል።
የሞት ቅጣት የሰውን ክብር ከማዳከም በተጨማሪ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎችን ተጠያቂ እንደማያደርጋቸው እና ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈጽሙ የሚያደርግ አለመሆኑን ወ/ሮ ሜርፊ ተናግረዋል።
የምሕረት ልዩ ዕድል
በአሁኑ ጊዜ በኦሃዮ ግዛት የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው 114 ሰዎች መኖራቸው ሲነገር ከእነዚህም ውስጥ 28ቱ የይግባኝ ሂደቱ እንደተቋረጠ ሲነገር፥ እንደ ወ/ሮ ሜርፊ ገለጻ የኦሃዮ ገዥ ማይክ ደዋይን የሥልጣን ዘመናቸው በጥር 2027 ከማብቃቱ በፊት የ114ቱ ሰዎች የሞት ፍርድ ለማስቀረት ዕድል እንዳላቸው አስረድተዋል።
የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑት ዴዋይን የሞት ቅጣትን በይፋ መቃወማቸውን ገልጸው፥ በኦሃዮ የስምንት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ቅጣቱ እንዲታገድ ማድረጋቸው ታውቋል።
“የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር ነው” ያሉት ወ/ሮ ሜርፊ፥ “ጉዳት ቢደርስበትም የመዋጀት ዕድሎችን በመፍጠር የማኅበረሰቡን ደህንነት መጠበቅ እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ እንችላለን” ብለው፥ ይህም ለዴዊን ትልቅ ዕድል መሆኑን አስረድተዋል።
የዓመፅ ዑደትን ለሕይወት አክብሮት በማሳየት ማብቃት
ሌሎች የፍርድ አማራጮችን መፈለግ የሞት ቅጣትን እንደሚያስወግድ እና ይህም በእስር ቤት ውስጥ እንዲያገለግሉ እንጂ በነፃ እንዲለቀቁ እንደማያደርጋቸው ነገር ግን ከክርስቲያን ዕይታ አንጻር ወንጀለኛው ከኃጢአቱ ንስሐ እንዲገባ እና ዓመፅን እንዲያቆም ዕድልን እንደሚሰጠው ተገልጿል።
“ተጎጂዎችን በቁም ነገር ልንመለከታቸው ይገባል” ያሉት ወ/ሮ ሜርፊ፥ “ጉዳታቸውን ለመፈወስ እና ያጋጠማቸውን ችግር ለመፍታት የሚያግዙ መገዶችን ለማግኘት በመሞከር ይቅርታ የሚቻልባቸው ዕድሎችንም መፍጠር አለብን” ብለዋል።
በምርጫ ወቅት የሚሰጥ የሞት ቅጣት ፍርድ ቀስ በቀስ ተወዳጅነቱን እያጣ እንደሚሄድ ወ/ሮ ሜርፊ ተናግረው፥ ካቶሊካዊ ምዕመናን ከፅንስ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ ለሕይወት ተገቢ አክብሮት መስጠት እንደሚገባ ያላቸውን ጠንካራ የሞራል ግዴታን ለዓለም ማሳየት እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ወ/ሮ ሜርፊ በመጨረሻም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በግልጽ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደፊት እንድጓዝ እና የሞት ቅጣትን የምትቃወም መሆኗን ለአሜሪካ እና ለዓለም በማሳየት ሕይወትን በሁሉም ደረጃዎች ማክበር እንደሚገባ ማበረታታቸውን አስረድተዋል።