የካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት ዩናይትድ ስቴትስን ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ አደራ መስጠታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአሜሪካ 250ኛ የነፃነት ክብረ በዓል እ.አ.አ ሐምሌ 4 ቀን 2026 ዓ.ም. የሚከበር ታሪካዊ ክስተት ሲሆን፥ በዋይት ሃውስ እና በመላው ሃገሪቱ የተለያዩ የፌስቲቫል፣ ታሪካዊ ትርኢቶች እና የዓለም ዋንጫን ጨምሮ በትላልቅ የስፖርት ኩነቶች በሃገሪቱ ውስጥ እና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አሜሪካውያን ኤምባሲዎች ጭምር በድምቀት ይከበራል።
ይህ ቀን የአሜሪካ ኮንግረስ እ.አ.አ ሃምሌ 4 ቀን 1776 ዓ.ም. በእንግሊዝ ሥር የነበሩት ቅኝ ግዛቶች ነፃ መውጣታቸው የታወጀበትን ሰነድ በሙሉ ድምፅ ያጸደቀበት ቀን እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ ይሄን ተከትሎ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ዩናይትድ ስቴትስ የተመሰረተችበት 250ኛ ዓመት ዋዜማ ላይ የሀገሪቱ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት በፍሎሪዳ ግዛት ሥር በምትገኘው ኦርላንዶ ከተማ ተሰባስበው አስደናቂ እና ጥልቅ ምሳሌያዊ ተግባር የሆነውን ዩናይትድ ስቴትስን ለቅዱሱ ልበ ኢየሱስ መስጠታቸው ተገልጿል።
የፖለቲካ ክፍፍሎች እየሰፉ በሄዱበት እና የተቋማት ተአማኒነት እያሽቆለቆለ ባለበት በዚህ ወቅት፣ እንዲሁም በርካታ አሜሪካውያን ስለወደፊቱ ጊዜ እርግጠኛ አለመሆናቸውን እየገለጹ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፥ የሃገሪቱ ብፁዓን ጳጳሳት የፖሊሲ ለውጥ ጥያቄም ሆነ የፖለቲካ እንድምታ የሌለው የጸሎት ጥሪ ማቅረባቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይህ የጸሎት ጥሪ የተለመደ መንፈሳዊ የጸሎት ጥሪ እንዳልነበረም ተገልጿል።
መቀደስ ከቤተክርስቲያን ጥልቅ መንፈሳዊ ተግባራት ውስጥ አንዱ ሲሆን፥ መቀደስ ማለት አደራ መስጠት እና ራስን በፍቅር በክርስቶስ ጥበቃ ስር ማድረግ እንደሆነ እና ምንም እንኳን የሰው ልጆች ስኬቶች እና ውድቀቶች ቢኖሩም፥ ታሪክ በመጨረሻም የእግዚአብሔር እንደሆነ እውቅና ለመስጠትም ጭምር መሆኑ ይገለፃል።
የባልቲሞር ሊቀ ጳጳስ ዊልያም ኢ ሎሪ ክብረ በዓሉን በማስመልከት በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን የወቅቱን ትርጉም በግልፅ እና በጸና እምነት የገለጹ ሲሆን፥ ሊቀጳጳሱ ለመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ከተሰበሰቡት ሌሎች ብፁዓን ጳጳሳት እና ምዕመናን ፊት በመቅረብ እንደተናገሩት በመጀመሪያ ደረጃ ቤተክርስቲያን ውስጥ የምንሰበሰበው ራሳችንን ለማክበር ሳይሆን፥ ከዚህም ይልቅ ለመቀደስ እና አደራ ለመስጠት እንደሆነ ገልጸው፥ እነዚህ ቀላል የሚመስሉ ቃላት የዕለቱን አስፈላጊነት ለመረዳት የሚያስችል ቁልፍ ነገር መሆናቸውን አስረድተዋል።
የእምነት ድርጊት
ሊቀ ጳጳስ ሎሪ መቀደስ በመሠረቱ የእምነት ተግባር መሆኑን ለምዕመናኑ ያሳሰቡ ሲሆን፥ የአንድ ሀገር ታሪክ የፖለቲካ መሪዎች ታሪክ፣ ወታደራዊ ድሎች፣ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች ወይም የባህል ውጤቶች ብቻ እንዳልሆነ ያላቸውን ግንዛቤ ገልጸው፥ የሃገር ታሪክ ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች በኩል የሚሰራው የእግዚአብሔር ጥበቃ እና ጸጋ ታሪክ ነው ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ይሄንን የነፃነት ቀኗን ለማክበር የተወሰኑ ቀናቶች ብቻ በቀረበት በአሁኑ ወቅት የክብረ በዓላት፣ የመታሰቢያ ዝግጅቶች እና የታሪክ ነጸብራቆች እጥረት እንደማይኖር የተገለጸ ሲሆን፥ ነገር ግን ብፁዓን ጳጳሳቱ ይህንን መታሰቢያ በዓል ለመጀመር የመረጡት በድል ሳይሆን በትህትና እንደሆነ የጠቆሙት ሊቀ ጳጳስ ሎሪ፥ “ሕዝባችንን ወይም ሃገራችንን የምንቀድሰው ፍጹም ስለሆነ ሳይሆን በእግዚአብሔር የተወደደ ስለሆነ ነው” ብለዋል።
እነዚህ ቃላት ክርስቲያናዊ የአገር ፍቅር ራዕይን ያሳያሉ የተባለ ሲሆን፥ የሀገር ፍቅር ለጥፋቱ ተጠያቂ አለመሆንን እንደማይጠይቅ፥ ከዚህም ይልቅ እውነተኛ ፍቅር መልካሙን ነገር ብቻ እንደሚፈልግ፣ ለተበደሉት እውቅና እንደሚሰጥ እና ሁለቱንም ለእግዚአብሔር ምሕረት አደራ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ስለዚህም መቀደሱ የምስጋና እና የንስሐ፣ የምስጋና እና የልመና ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ሊቀ ጳጳሱ፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ የሀገሪቱን ስኬቶች እና ውድቀቶች፣ ጥንካሬዎች እና ቁስሎች፣ ተስፋዎች እና ስጋቶች ለክርስቶስ ልብ አደራ መስጠታቸውን አስረድተዋል።
የክርስቶስ ልብ እና የአንድ ሀገር ልብ
ሊቀ ጳጳስ ሎሪ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በፍቅሬ ኑሩ” በማለት ባቀረበው ግብዣ ላይ በማሰላሰል የተቀደሰ ልብ የአምልኮ ወይም መንፈሳዊ ምስል ብቻ ሳይሆን፥ የሚታይ ሥጋን የፈጠረ የእግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ ጠቅሰው፥ የክርስቶስ ልብ ጓደኝነትን እና ክህደትን፣ ደስታን እና ሀዘንን፣ መከራን እና መስዋዕትን ያሳለፈ ልብ ነው ብለዋል።
የዚህ ግንዛቤ አስፈላጊነት በቃላት ሊገለጽ እንደማይቻል የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ብዙውን ጊዜ ራስን በራስ ማስተዳደር እና ራስን መቻልን በሚያወድስ ባህል ውስጥ ብፁዓን ጳጳሳቱ ግለሰቦችም ሆኑ ሃገራት ከእግዚአብሔር በቀር ሊደምቁ እንደማይችሉ በይፋ እውቅና መስጠታቸውን አስረድተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ሎሪ የሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ምንም እንኳን ጠቃሚ ቢሆኑም በጠንካራ ተቋማት ወይም በተሻሉ ፖሊሲዎች ላይ ብቻ የተመካ ሳይሆን፥ ነገር ግን በመለኮታዊ ፍቅር በተለወጡ ልቦች ላይ እንደሆነ ያስታወሱ ሲሆን፥ ቅዱሱ ልብ እግዚአብሔር ከሰው ልጅ ተጋድሎ የራቀ እንዳልሆነ አማኞችን እንደሚያሳስብ ጠቅሰው፥ ይህ ልብ ወደ እነርሱ እንደሚዘልቅ፣ እንደሚሸከማቸው እና እንደሚቤዣቸው ገልጸዋል።
ፍሬ እንዲያፈራ ተልኳል
ከዚህም ባሻገር ሊቀ ጳጳስ ሎሪ መቀደስ መጨረሻ ሳይሆን መጀመሪያ መሆኑን ለምዕመናኑ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ቤተክርስቲያን በረከቶችን ለመቀበል ብቻ እራሷን ለቅዱስ ልብ አሳልፋ እንደማትሰጥ፥ ከዚህም ይልቅ በዓለም ላይ የተሻለ ታማኝ የክርስቶስ ፍቅር መሳሪያ ለመሆን እራሷን ትቀድሳለች ብለዋል።
“የተቀደሰ ልብ ያስታርቃል እንጂ አይከፋፈልም” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ልቦችን የሚያጸና ሳይሆን የሚለውጥ መሆኑን ጠቅሰው፥ በርዕዮተ ዓለም ግጭት እና በባህላዊ አክራሪነት እራሱን ለመግለጽ በተፈተነ ሃገር እና ህዝብ ውስጥ እነዚህ ቃላት ወቅታዊ እና ትንቢታዊ ናቸው ብለዋል።
የዚህ ቅድስና እውነተኛ ፍሬ የሚለካው በስርዓተ አምልኮው ውበት ወይም በሥነ ሥርዓቱ አስፈላጊነት ሳይሆን፥ ካቶሊኮች በቤተሰቦቻቸው፣ በአብያተ ክርስቲያናቸው፣ በሥራ ቦታቸው፣ በማህበረሰባቸው እና በህዝባዊ ህይወት ውስጥ የክርስቶስን ፍቅር የሚመሰክሩ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ሲሆኑ ነው ብለዋል።
ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረውን ማመን
ሊቀ ጳጳስ ሎሪ በስብከታቸው ማገባደጃ ላይ የዕለቱን በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት የሰጡ ሲሆን፥ አሜሪካውያን የሀገሪቱን 250ኛ የነፃነት መታሰቢያ ክብረ በዓልን ሲያስቡ ያለፈውን በመናፈቅ እና ስለወደፊቱ በመጨነቅ በሁለት ፈተናዎች ውስጥ እንደሚገቡ አመላክተው፥ ለሁለቱም ጥያቄ የክርስቲያኖች መልስ ‘እምነት’ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ “ዛሬ የተሻለውን ነገር እንመርጣለን፥ እሱም ‘ማመን’ ነው” ብለዋል።
ይህ እምነት በመጨረሻም የሚገለጸው በቅድስና መሆኑን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ አሜሪካዊያን እንከን የለሽ ናቸው ወይም የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው የተረጋገጠ ነው ብለው የሚያምኑ ባይሆንም፥ ሃገሪቱን ግን ለቅዱስ ልብ አደራ መስጠታቸውን አረጋግጠዋል።
ከዚህም ይልቅ ብፁዓን ጳጳሳቱ ጥልቅ እውነትን በማወጅ፥ ሃገሪቱ እንደማንኛውም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር የተወደደች እና ምህረቱን የምትሻ መሆኗን በማመላከት፥ ይህ በአሜሪካ 250ኛ የነፃነት ዋዜማ ላይ ቤተክርስቲያን የምታቀርበው በጣም አስፈላጊ መልዕክት ሊሆን ይችላል በማለት አጠቃለዋል።