ፈልግ

የፔምባ፣ በሞዛምቢክ የፔምባ ሃገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አንቶኒዮ ጁሊዬስፌሬራ ሳንድራሞ የፔምባ፣ በሞዛምቢክ የፔምባ ሃገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አንቶኒዮ ጁሊዬስፌሬራ ሳንድራሞ 

በሞዛምቢክ ቤተክርስቲያን በጂሃዲስቶች መቃጠሉን ተከትሎ አንድ የሃገሪቱ ጳጳስ የአብሮነት ጥሪ ማቅረባቸው ተነገረ

በሞዛምቢክ ካቦ ዴልጋዶ ግዛት ውስጥ ጂሃዲስቶች በድጋሚ በስፍራው በሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ የቃጠሎ ጥቃት መፈጸማቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ብፁዕ አቡነ ጁሊዬስ ፌሬራ ሳንድራሞ በአከባቢው ‘ለዘጠኝ ዓመታት ያህል አብያተ ክርስቲያናት እና ቤተመቅደሶች መውደማቸውን እና መቃጠላቸውን’ ጠቅሰው፥ ይሄንን ጥቃት ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሰሞኑን በሞዛንቢክ በካቦ ዴልጋዶ ግዛት አዲስ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በጂሃዲስቶች በተፈጸመ ጥቃት ቤተ ክርስቲያን መቃጠሏን እንዲሁም የፒያሪስ ማህበር ካህናት መኖሪያ ቤት እና መዋዕለ ህፃናትም ጭምር ጥቃት እንደደረሰባቸው የተነገረ ሲሆን፥ ከስምንት ዓመታት በላይ በዘለቀው ጦርነት ከ6,200 በላይ ህይወት መጥፋቱ እና ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል።

በሃገሪቱ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት የኮምቦኒ ሚስዮናውያን እህቶች የክልል የበላይ አለቃ የሆኑት እህት ላውራ ማልናቲ ሰሞኑን የተክሰተውን ጥቃት አስመልክተው ለጣሊያኑ አቬኒር ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኮምቦኒ እህት ማልናቲ ምስክርነት
እህት ላውራ በሰጡት ማብራሪያ መሰረት ሚያዝያ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ‘አይ ኤስ’ ወይም እስላማዊ መንግስት ተብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ቁርኝት እንዳለው የሚነገርለት እና እ.አ.አ. ከ 2017 ጀምሮ በአከባቢው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ‘አህሉ አል-ሱና ዋ አል-ጃማአ’ ተብሎ የምጠራው የታጣቂዎች ቡድን በአንኩዌቤ አውራጃ፣ ሰሜናዊ ካቦ ዴልጋዶ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ሜዛ መንደር ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ገልጸዋል።

አሁንም ድረስ ከድንጋጤው ያልወጡት እህት ላውራ ታጣቂዎቹ መንደሩን በእሳት ማጋየታቸውን እና እንደ እድል ሆኖ በስፍራው የነበሩት ካህናቱ አሸባሪዎቹ ከመድረሳቸው በፊት ማስጠንቀቂያ ስለደረሳቸው በጊዜ ከሜዛ መንደር መውጣት መቻላቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ታጣቂዎቹ አንዳንድ የቁምስናው ሕንፃዎችን ከማቃጠላቸው በተጨማሪ በርካታ መኖሪያ ቤቶችን ማውደማቸውን ጠቁመው፥ እ.አ.አ. በ 1946 ዓ.ም. ተገንብቶ በቅዱስ ሉዊስ ደ ሞንትፎርት የተሰየመው ይህ ቁምስና በክልሉ የካቶሊክ መገኘት ምልክት ተደርጎ እንደሚታይ አስረድተዋል።

በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የሚገኝ ማህበረሰብ
ይሄንን ተከትሎ የካቦ ዴልጋዶ ዋና ከተማ የሆነችው የፔምባ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አንቶኒዮ ጁሊያሴ ፌሬራ ሳንድራሞ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አቢያተ ክርስቲያናት ድጋፍ ለሚያደርገው ‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢንኒድ’ ባስተላለፉት መልዕክት ታጣቂዎቹ ከቀኑ 4 ሰዓት ላይ ወደ መንደሩ መድረሳቸውን እና ወደ ቤተ ክርስቲያኑም ቅጥር ጊቢ ገብተው ቤተክርስቲያኑን በእሳት ማቃጠላቸውን ገልጸዋል።

ይህ ትክክለኛ የሽብር ትዕይንት እንደሆነ የገለጹት ጳጳሱ፥ ሁሉም ነገር በፍጥነት ወደ ፍርስራሽነት መቀየሩን፣ በጥቃቱ ወቅት ሰላማዊ ሰዎች መያዛቸው እና የጥላቻ መልዕክቶች እንደተላለፈባቸው የገለጹ ሲሆን፥ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሚስዮናውያኑ ደህና መሆናቸውን፥ ነገር ግን ማህበረሰቡ አሁንም ድረስ በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ይህ ሁሉ ቢፈጸምም የዚህ ሕዝብ እምነት ፈጽሞ እንደማይጠፋ በአጽንዖት ገልጸዋል።

ለዓለም አቀፍ ትብብር የተደረገ ጥሪ
ብፁዕ አቡነ አንቶኒዮ በማከልም በክልሉ በተፈፀመው ጥቃት ሰለባ ለሆኑት ሰዎች “ትኩረት እንዲሰጥ እና ትብብር እንዲደረግ እንጠይቃለን” በማለት ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ “ለዘጠኝ ዓመታት ያክል በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ የጸሎት ቤቶች እና አብያተ ክርስቲያናት ጥቃት እንደደረሰባቸው፣ እንደወደሙ እና በእሳት እንደተቃጠሉ” አስታውሰዋል።

የካቦ ዴልጋዶ ግዛት ሞዛምቢክ ውስጥ ከሚገኙ በጣም ድሃ ግዛቶች አንዱ እንዲሁም ከዓለም ድሃ ሃገራት መካከል ቀዳሚ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ሆኖም የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በማዕድን እና በተፈጥሮ ጋዝ ክምችት የበለፀገ እንደሆነ እና በርካታ የምዕራባውያን ኩባንያዎች ሀብቱን በማውጣት ሥራ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት መሰረት በተፈጠረው ሁከት ምክንያት እ.አ.አ. በ 2025 ዓ.ም. ብቻ ከ110,000 በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ለቀው ለመሰደድ እንደተገደዱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

04 May 2026, 14:23