ፈልግ

ሃምሌ 2017 ዓ.ም. በታይቤህ መንደር በእስራኤላውያን ሰፋሪዎች የተቃጠለውን መኪና የአካባቢው ሰዎች ሲመለከቱ ሃምሌ 2017 ዓ.ም. በታይቤህ መንደር በእስራኤላውያን ሰፋሪዎች የተቃጠለውን መኪና የአካባቢው ሰዎች ሲመለከቱ  (ANSA)

ኢሃብ ሀሰን በፍልስጤም ክርስቲያኖች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ‘ተጠያቂ የሆነ ሰው የለም’ ማለታቸው ተነገረ

የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ኢሃብ ሀሰን የእስራኤል ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ሊያጠናክሩ ስለሚችሉበት “ያለመቀጣት” ሁኔታ አስመልክቶ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ ሃሳባቸውን ያጋሩ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ‘የዌስት ባንክ ክርስቲያኖችን እናድን’ በሚል ጭብጥ አዲስ የተጀመረውን ተነሳሽነት አስተዋውቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከዚህን በፊት የእስራኤል ሰፋሪዎች በዌስት ባንክ ሙሉ በሙሉ የክርስቲያን መንደር በሆነችው የታይቤህ መንደር ላይ በተከታታይ ጥቃት መፈጸማችውን ተከትሎ ሃምሌ 2017 ዓ.ም. ለመጨረሻ ጊዜ ከቫቲካን ዜና ጋር ውይይት አድርገው የነበሩት የፍልስጤም ክርስቲያኖች ሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ኢሃብ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት ‘ማድረግ የሚያስፈልገው ሰፋሪዎች ለፈጸሙት ግፍ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ’ መሆኑን ገልጸው፥ ይህ ካልተደረገ ጥቃቱ ተባብሶ እንደሚቀጥል አሳስበው እንደነበረ ተገልጿል።

ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ኢሃብ ሀሰን ሰሞኑን ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ ሰፋሪዎች ለፈጸሙት ድርጊት “በምንም ሁኔታ ተጠያቂ እንዳልተደረጉ” ጠቁሟል።

በመላ ፍልስጤም ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚያሳዩ ምስሎችን የሚሰበስቡት እና በተለያዩ ሚዲያዎች የሚያጋሩት አክቲቪስቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰፋሪዎች ተሽከርካሪዎችን ሲያቃጥሉ፣ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን መስኮቶች ሲሰባብሩ እና በከተማዋ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚገኘውን ስፍራ መያዛቸውን ጨምሮ በርካታ ተጨማሪ ጥቃቶችን በማስረጃ ማቅረባቸው ይታወቃል።

ሀሰን ሰፋሪዎች ጥቃታቸውን አጠናክረው የቀጠሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ ጥቃት አድራሾቹ “ስለማይከሰሱ እና ስለማይቀጡ” መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶ የገለጹ ሲሆን፥ የእስራኤል መንግስት የሰፋሪዎቹ አንዳንድ ድርጊቶች ቢያወግዝም፥ ጥቃቱን ለማስቆምም ሆነ ወንጀለኞቹን ለመያዝ “ምንም ዓይነት ትክክለኛ እርምጃ” እንዳልተወሰደ ገልጸዋል።

ከጥር ወር ጀምሮ በዌስት ባንክ 16 ሰዎች ሞተዋል
ይህ ሁኔታ በታይቤህ ወይም በፍልስጤም የክርስቲያን ማህበረሰብ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፥ ተመሳሳይ ጥቃቶች ከኬብሮን እስከ ጄኒን፣ በአጠቃላይ በዌስት ባንክ እየተፈጸሙ መሆኑን ሀሰን አስረድተዋል።

ባለፈው ወር አንድ የ14 ዓመት ልጅን ጨምሮ ሁለት ፍልስጤማውያን በሙጋየር ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት በጥይት ተመተው መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የገለጹ ሲሆን፥ ከሁለት ሳምንት በፊት የፍልስጤም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በአጠቃላይ 16 ፍልስጤማውያን በዌስት ባንክ መገደላቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

“እነዚህን ሰፋሪዎች በእውነት የሚያበረታታቸው የእስራኤል መንግስት ፖሊሲ ነው” ያሉት ሀሰን፥ እስራኤል በቅርቡ በዌስት ባንክ ከዚህ በፊት ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ህገወጥ የሆኑ 34 አዳዲስ ሰፈራዎችን ማጽደቋን ገልጸው፥ እነዚህ ቦታዎች ሰፋሪዎች በፍልስጤም ከተሞች እና መንደሮች ላይ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች እንደ ‘መነሻ ቦታ’ ተደርገው እንደሚያገለግሉ አክለው ገልጸዋል።

የአንድነት ጥሪ
ሀሰን በዌስት ባንክ ውስጥ እያሽቆለቆለ ስላለው የሰብአዊ ሁኔታን በማስታወስ ‘የዌስት ባንክ ክርስቲያኖችን እናድን’ በሚል ጭብጥ አዲስ ተነሳሽነት ወይም ፕሮጄክት መጀመሩን ገልጸዋል።

በአሜሪካዊው የፊልም ሰሪ እና በጎ አድራጊ ጄሰን ጆንስ የተመሰረተው ፕሮጀክቱ በቅድስቲቷ ምድር ጥንታዊ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ላይ በህገ ወጥ እስራኤላዊያን ሰፋሪዎች የሚደርሰውን “ነባራዊ” ስጋት ለማጉላት ያለመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት “ምንም አይነት የፖለቲካ አቋም እንደማይጠይቅ” የጠቆሙት ሀሰን፥ ከዚህም ይልቅ እየጠየቁ ያሉት በዓለም ዙሪያ ያሉ ክርስቲያኖች እነዚህን ጥቃቶች እንዲያቆሙ ኃላፊነት በተጣለባቸው ሰዎች ላይ ጫና እንዲያደርጉ እና እንዲተባበሩ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

ሀሰን በመጨረሻም በቅርቡ መኖሪያ ቤታቸው በእስራኤል ሰፋሪዎች ጥቃት የደረሰበት፣ ናቡልስ አቅራቢያ በሚገኘው ጃሉድ መንደር ከሚገኝ ቤተሰብ ጋር የተደረገውን የስልክ ውይይት በማስታወስ፥ ይህ ቤተሰብ ሰፋሪዎቹ በቅርቡ ድጋሚ ጥቃት ይሰነዝራሉ ብለው እንደሚያስቡ እና ማንም ሰው ይህንን ጥቅት ለማስቆም ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳልወሰደ ብሎም ቢሞቱ እንኳን ማንም ሰው እንደማያስተውል መናገራቸውን በማስታወስ አጠቃለዋል። 

11 May 2026, 14:40