በዱባይ ለብሔራዊ የሰላም ጸሎት የተሰበሰቡት የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በዱባይ ለብሔራዊ የሰላም ጸሎት የተሰበሰቡት የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች  (© Apostolic Vicariate of Southern Arabia (AVOSA))

የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በዱባይ ለብሔራዊ የሰላም ጸሎት መሰብሰባቸው ተገለጸ

በዱባይ በተዘጋጀው ብሔራዊ የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መሰብሰባቸው ተገለጸ። የደቡብ አረቢያ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ በስብሰባቸው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ሰላም በሰው ልጅ ብቻ የሚገነባ ሳይሆን ከልብ ልንፈልገ እና ልንከባከበው የሚገባን፣ በመልካም ግንኙነታችን በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚሰራጭ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአብያተ ክርስቲያን መሪዎች ሚያዝያ 21/2018 ዓ. ም. በዱባይ በሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለብሔራዊ የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተሰብስበዋል።

ብሔራዊ የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በመተባበር ያዘጋጁት የባሕረ ሰላጤው አገራት አብያተ ክርስቲያናት እና የሌሎች እምነቶች ኅብረት፣ የደቡብ አረቢያ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ውይይት ጽሕፈት ቤት እና በዱባይ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መሆናቸው ታውቋል።

የደቡብ አረቢያ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ ለእንግዶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው፥ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ለባሕረ ሰላጤው፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለመላው ዓለም የሰላም ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

“ሰላም በሰው ልጅ ብቻ የሚገነባ ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ስጦታ ነው” ብለው፥ በመልካም ግንኙነታችን በኅብረት ፈልገን የምናገኘው፣ የምናስተናግደው፣ እንክብካቤ የምናደርግለት እና በኅብረተሰቡ ውስጥ የምናሰራጨው ነው” ሲሉ ካስገነዘቡ በኋላ በቅርብ ወራት ውስጥ ለተደረገላቸው ጥበቃ የሲቪል ባለስልጣናትን በማመስገን የክርስቲያን ማኅበረሰብ በጸሎት የደገፋቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ አክለውም፥ እግዚአብሔር የጋራ ጸሎታቸውን እንዲሰማ፤ ሰላምን እና እርቅን፣ ስምምነትን እና ብልጽግናን እንዲሰጣቸው ለምነዋል።

የባሕረ ሰላጤው አገራት አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የሰላም ጸሎት ስብሰባ የተዘጋጀው በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣ በዱባይ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን እንደገና ለመክፈት እና የብርሃነ ትንሳኤውን ደስታ በኅብረት ለማክበር እንደሆነ ታውቋል።

በዱባይ የምትገኝ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከስድስት አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ተወካዮችን እና ምእመናንን ለመቀበል በሯን መክፈቷ ተገልጿል።

በሦስት ክፍለ ጊዜያት የተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ፥ በኒቂያው የሐዋርያት ጸሎት ሃይማኖት፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባትን በያዘ የሰላም ጸሎት፣ ከልዩ ልዩ የክርስትና ሥርዓተ አምልኮ ቋንቋዎች በተወሰዱ ጸሎቶች፣ በሻማ ማብራት እና በመቀባበል የሚደገም የሰላም ጸሎት ከቀረበ በኋላ የሰላምታ መለዋወጥ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

ከብጹዕ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ በተጨማሪ የየራሳቸውን ማኅበረሰቦች ወክለው በሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፥ የአርሜኒያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ መስሮብ ሳርኪሲያን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲሜጥሮስ፣ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሲን ሴምፕል፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳቅ ዛኩር እና የግብጽ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን አባ ሚና ሐና እንደ ነበሩ ታውቋል።

 

01 May 2026, 14:31