ፈልግ

የአሜሪካ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የዳይሬክተሮች ቦርድ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ አቀባበል ሲደርግላቸው የአሜሪካ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የዳይሬክተሮች ቦርድ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ አቀባበል ሲደርግላቸው  (@VATICAN MEDIA)

የአሜሪካ የካቶሊክ በጎ አድራጎቶች ድርጅት የአገልግሎት ተግዳሮቶች መካከል ባለበት ወቅት በር.ሊ.ጳ. ሊዮ መበረታታቱ ተነገረ

የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ በጎ አድራጎቶች ድርጅት የዳይሬክተሮች ቦርድ በቫቲካን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ እንደተናገሩት ‘የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቃላቶች ድርጅቱ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ አቅመ ደካሞችን ለወንጌል ታማኝ በመሆን ለማገልገል ያለውን ቁርጠኝነት ያጠናክራል’ ማለታቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሰኞ ዕለት ከአሜሪካ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት አመራር አባላት ጋር በቫቲካን በተካሄደው ስብሰባ ላይ እንደገለጹት ተቋሙ እየሰራ ለሚገኘው መልካም ተግባር የማበረታቻ እና የምስጋና ቃል አቅርበው፥ ድሆችን እና አቅመ ደካሞችን የማገልገል ተልዕኳቸውን “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር መገለጫ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል።

የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ የአሜሪካ ቅርንጫፍ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኬሪ አሊስ ሮቢንሰን ከሳምንታዊው ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መርሃ ግብር በኋላ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ካቶሊክ ካሪታስ በሁሉም የአሜሪካ 50 ግዛቶች ውስጥ፣ በአምስቱ የአሜሪካ ክልሎች እና በኮሎምቢያ አውራጃ ውስጥ እያከናወነ ያለው ተግባር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር መገለጫ እና የተስፋ ብርሃን ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን በመጥቀስ አድናቆታቸውን እንደገለጹ አስታውሰዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚረዷቸው ሰዎች የሚደርስባቸው መከራ ይበልጥ “በድህነት የተወሳሰበ እና የተባባሰ ነው” ማለታቸውን ያስታወሱት ፕርዚዳንቷ፥ በበጎ አድራጎት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በመግለጽ ልዑካኑ በአገልግሎታቸው እንዲጸኑ ቅዱስ አባታችን ማሳሰባቸውን አክለው ገልጸዋል።

“ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በትንሳዔው ወቅት ላይ መሆናችንን እና የሰው ልጆችን መከራ ከቀን ወደ ቀን መመስከር አስቸጋሪ ቢሆንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ብሎ የሰጠንን የተስፋ ቃል ማሰብ እንደሚገባን አስታውሰውናል” ያሉት የድርጅቱ ፕረዚዳንት ወይዘሮ ሮቢንሰን፥ ከብፁዕነታቸው ጋር የነበራቸውን ቆይታ “በጣም ልብ የሚነካ” ሲሉ በመግለጽ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቃላት የልዑካን ቡድኑን “ከየትኛውም ቦታ፣ ከተለያዩ እምነት የተውጣጡ ድሆችን እና አቅመ ደካሞችን ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያድሱ ማድረጉን ገልጸዋል።

“ከባድ ሥራ፥ ነገር ግን ጥልቅ ትርጉም ያለው”
የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ስለሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በንግግራቸው ወቅት ስላቀረቡት ምሳሌ ከጋዜጠኞቹ የተጠየቁት ወይዘሮ ሮቢንሰን፥ የብፁዕነታቸውን ንግግር በዋነኛነት በመንፈሳዊ እና በሃዋሪያዊ እይታ እንደሚረዱት ገልጸው፥ በየቀኑ የሰው ልጅ የሚያጋጥመውን ስቃይ ስለሚያዩ እና ይህ ሥራ ከባድ እንደሆነ ስለሚረዱ ንግግራቸውን የሰሙት ከእውነታው አንጻር እንደሆነ ጠቅሰው፥ ከዚህም በተጨማሪ ‘የድሃ ቤተሰቦችን እና ማህበረሰቦችን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል በቂ ሃብት አለመኖሩን’ አክለው ገልጸዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቃላት የበጎ አድራጎት አገልግሎት አስተዳደራዊ ወይም አቅርቦት ብቻ ሳይሆን ግንኙነታዊ እና ወንጌላዊ መሆኑን ጭምር መረዳትን ያንጸባርቃሉ ያሉት ወይዘሮ ሮቢንሰን፥ በዚህም መሰረት ብፁዕነታቸው ይህ ሥራ ቀላል እንዳልሆነ መረዳታቸውን ገልጸው፥ “የተገልጋዮችህን ስም ስታውቅ፣ ታሪካቸውን ስትረዳ እና ሰብዓዊነታቸውን ስትመለከት ግንኙነቱ የሁለት አቅጣጫ መንገድ ይሆንና እግዚአብሔር ለድሆች ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ እናስታውሳለን” በማለት አስረድተዋል።

ለገንዘብ እና ለፖለቲካ ጫናዎች ምላሽ መስጠት
ወይዘሮ ሮቢንሰን ከዚህም በተጨማሪ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ኤጀንሲዎች በተለይም አንዳንድ የፌደራል የስደተኞች መልሶ ማቋቋሚያ የገንዘብ ድጎማ መቀነሱን ተከትሎ የሚደርስባቸውን የገንዘብ እና ፖለቲካዊ ጫና ያነሱ ሲሆን፥ የአሜሪካ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በአብዛኛው ወይም ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በግል ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ቢሆንም፣ አንዳንድ የአካባቢው የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ከስደተኞች ጋር በተገናኘ የመንግስት ድጋፍ በመቋረጡ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሟቸው ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ45,000 የሙሉ ጊዜ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሠራተኞች ውስጥ ወደ 450 የሚጠጉ የሥራ መደቦች እንደተቋረጡ በማስታወስ፥ በአብዛኛው ግን ያጋጠማቸው ቅነሳዎች በስደተኞች መልሶ ማቋቋሚያ ሥራዎች ላይ እንደነበሩ ጠቁመው፥ እነዚህ መሰናክሎች ቢኖሩም ድርጅቱ ለተልዕኮው ቁርጠኛ መሆኑን ሮቢንሰን በአጽንዖት ተናግረዋል።

በእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ፕረዚዳንቷ፥ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የገንዘብ ክፍተቶችን ለመሙላት እና እያደገ የሚሄደውን ፍላጎቶች ለማሟላት በለጋሾች ልግስና ላይ መተማመንን እንደቀጠሉ አስታውሰው፥ አሜሪካውያን የተራቡ ሰዎችን ስም እና ፊት እንዲያውቁ ሲደረግ የመርዳት ፍላጎት እንደሚኖራቸው የገለጹ ሲሆን፥ ድርጅቱ የፌደራል የምግብ ዕርዳታ ከቆመ በኋላ 25 ሚሊዮን ፓውንድ ምግብ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከፋፈል ያስቻለውን የቅርብ ጊዜ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ጥሪ አስታውሰዋል።

'የምናገለግላቸውን ሰዎች የምንገናኝበት የርህራሄ መንገድ'
ወይዘሮ ሮቢንሰን አበክረው እንደተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የካቶሊክ የበጎ አድራጎት ሥራ ልዩ ምስክርነት በቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ ተልዕኮ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንደሚገነዘቡ ጠቁመው፥ “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የምንገኝ የማኅበራዊ አገልግሎት ኤጀንሲ ብቻ ሳንሆን፥ ነገር ግን የምናገለግላቸውን ሰዎች የምንገናኝበት ምሕረት የተሞላበት መንገድ መሆናችንን እንደሚረዱ ግልጽ ነው” ብለዋል።

“መታወቅ ያለበት የሰብዓዊ እርዳታን ማቅረባችን ብቻ ሳይሆን፥ ተገልጋዮቻችንን በመንከባከብ፣ ክብራቸውን በመጠበቅ፣ በሥማቸው በመጥራት እና ለእነሱ በመጸለይ የምንሰራውን ምህረት የተሞላበትን መንገድ ማሳየታችን ነው” በማለት አክለው ገልጸዋል።

በቤተክርስቲያኑ የበጎ አድራጎት ሥራ በኩል እያደገ የመጣው አንድነት
ወይዘሮ ሮቢንሰን በብፁዓን ጳጳሳት፣ በካቶሊክ አገልግሎቶች፣ በመምህራን እና በጤና አጠባበቅ መሪዎች መካከል ያለው ትብብር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፥ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በካቶሊክ መሪዎች መካከል የበጎ አድራጎትን እና የማህበራዊ አገልግሎትን በመደገፍ ረገድ አንድነት እያደገ መምጣቱን የገለጹ ሲሆን፥ “በአሜሪካ በሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ እንዲህ ያለ አንድነት ከዚህ በፊት አይቼ አላውቅም” ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ሃላፊዋ ካቶሊካዊያን ለወንጌል የምሕረት ጥሪ እንዲጸኑ በማበረታታት ረገድ የአሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳትን እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን በማመስገን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ ሁሉንም ካቶሊካዊያንን እና መልካም ፍቃድ ያላቸውን ሰዎች ቅዱስ ወንጌል መሃሪ መሆን እንደሚገባ ያዘዘውን ትዕዛዝ እንዲፈጽሙ በማስታወስ በአንድ ድምጽ እየተናገሩ እንደሆነ አስረድተዋል።

ወይዘሮ ሮቢንሰን በመጨረሻም ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር የነበራቸውን ቆይታ በማስታወስ፥ ብፁዕነታቸው የተናገሩት የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት መሪዎች ለወንጌል ታማኝ ሆነው ሥራቸውን ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዳጠናከረላቸው ገልጸው፥ “በዚህ ሥራ እንድንቀጥል እና የእምነታችን ግዴታዎችን በጽናት ለመውጣት እንድንችል አበረታተውናል” በማለት አጠቃለዋል።

06 May 2026, 14:41