በባህሬን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዕረፍት 800ኛ ዓመት እንደሚከበር ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በባህሬን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዕረፍት 800ኛ ዓመት መታሰቢያ እና የዘመናዊው ባህሬን ግዛት መሥራች እና በተቋማዊ ዕድሳቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በሚታሰቡት ሼክ ኢሳ ቢን አሊ አል ካሊፋ (ኢሳ አል ካቢር) ስም ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ታውቋል። “የኢሳ አል ካቢር ዓመት” የሚባለውን ይህን የመታሰቢያ በዓል በማስተባበር ላይ የሚገኙት ንጉሥ ሃማድ ቢን ኢሳ አል ካሊፋ እንደሆኑ ታውቋል።
ይህን በኅብረት ያስታወቁት በማናማ የሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ እና “This is Bahrain” ተብሎ የሚጠራ ማኅበር ባወጡት መግለጫ ሲሆን፥ መታሰቢያ በዓሉ የባህረ ሰላጤው መንግሥት ለውይይት፣ አብሮ ለመኖር እና ልዩነትን ለማክበር ቀጣይነት ያለውን ቁርጠኝነት እንዳለው ለመግለጽ እንደሆነ ታውቋል።
የቅዱስ ፍራንችስኮስ ውርስ
“ምንም እንኳን በጊዜና በባሕል የተለያዩ ቢሆኑም ሁለቱ ሰዎች የጋራ ውርስ እንዳላቸው የገለጸው መግለጫው፥ “ሕይወታቸው እውነተኛ ጥንካሬ የሚገኘው በርኅራኄ፣ በግልጽነት እና ልዩነትን በመቀበል መሆኑን ያስታውሰናል” ሲል ገልጿል። ባህሬን እነዚህን ውርሶችን መሠረት በማድረግ መታሰቢያ በዓሉን ለማክበር እንደምትፈልግ ታውቋል።
የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከ 1181–1228 ዓ. ም. (እ.አ.አ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም እና የውይይት ሰው መሆኑ ሲታወስ፥ ከግብፁ ሱልጣን ጋር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1219 ዓ. ም. ባደረጉት ታሪካዊ ግንኙነት ልዩነቶችን ለማክበር ምስክርነት መስጠታቸው ይታወሳል። መግለጫው በመቀጠልም፥ “ከዘመናት በኋላ ኢሳ አል ካቢር በመባል የሚታወቁት ሼክ ኢሳ ቢን አሊ አል ካሊፋ (1869–1932) የተለያዩ ማኅበረሰቦች እርስ በርስ የሚገናኙባቸውን መንገዶች በማመቻቸት ሃሳብ በመለዋወጥ እና በመግባባት ላይ የተመሠረተ አቀባበል ያለው ማኅበረሰብ ለመገንባት መሠረት ጥለዋል” ሲል ገልጿል።
አብሮነት እና ውይይትን የሚያበረታቱ ዝግጅቶች
በጋራ አብሮ የመኖር እና የውይይት እሴቶችን ለማጉላት ያለመ የመታሰቢያ በዓል መርሃ ግብሩ፥ መሪዎችን እና ምሁራንን በማሰባሰብ በባሕሎች እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ጉባኤ፥ በቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የሰላም መልዕክት ላይ፣ ከግብፁ ሱልጣን ጋር የመሠረተው ወዳጅነትም ለዘመናችን ድህነት ምላሽ ለመስጠት በሚጥር “የቅዱስ ፍራንችስኮስ ምጣኔ ሃብት” እና ምድሪቱን ከጉዳት ለመጠበቅ እና ሃብቷን ለማደስ ጥሪ ለማድረግ በሚያስችል “የቅዱስ ፍራንችስኮስ ስነ-ምህዳር” ለማሰላሰል ዕድል እንደሚሰጥ ታውቋል
በባህሬን የሚገኙ ተማሪዎች እና ወጣት አርቲስቶች ከሰላም፣ ከወዳጅነት እና ከተፈጥሮ ጋር ያሉ ጭብጦችን መሠረት በማድረግ የፈጠራ ሥራቸውን ለማበረታታት የሚያግዝ ብሔራዊ የስዕል ውድድር እንደሚቀርብ ታውቋል። እንዲሁም የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ስለ ፍጥረታት የዘመራቸውን መዝሙሮች የካተተ ኮንሰርት የሚቀርብ ሲሆን፥ ይህም የቅዱሱን እሴቶች እና ከፍጥረት እና ከሰብዓዊነት ጋር ያለውን ጊዜ የማይሽረውን የስምምነት መልዕክት የሚያከብር እንደሚሆን ተገልጿል።
የቅዱስ ፍራንችስኮስ ድምፅ ለዛሬው ዓለም
በማናማ የጣሊያን አምባሳደር አንድሪያ ካታላኖ በመግለጫቸው ላይ፥ “የቅዱስ ፍራንችስኮሰ የሰላም እና የውይይት ጥሪ መለያየት እና ግጭት በበዛበት በዛሬው ዓለምም በመቅረብ አጣዳፊነቱን ያስተጋባል” ብለዋል።
አክለውም በዚህ የችግር ጊዜ የእርሱ ውርስ የስምምነት መንገድ የሚገኘው በድል አድራጊነት ሳይሆን በርህራሄ፣ የልዩነት ግድግዳዎችን በመገንባት ሳይሆን መገናኛ ድልድዮች በመገንባት፣ በዝምታ ሳይሆን በውይይት ነው” ሲሉ አስታውሰዋል። በዚህ ምክንያት ክፍፍሎችን መፈወስ እና አለመግባባቶች በሚፈጠሩባቸው ቦታዎች የሰላም ዘር መዝራት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
ለሴቶች ሚና ትኩረት መስጠት
የ “ይህ ባህሬን ነው” የተባለ ማኅበር ፕሬዝደንት ቤቲ ማቲሰን በበኩላቸው፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ለሴቶች ሚና የሚሰጠውን ትኩረት በማስታወስ፥ “ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከቅድስት ክላራ ጋር በመተባበር ላቋቋመው የቅድስት ክላራ ማኅበር ባደረገው ድጋፍ፥ ሴቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ትርጉም ያለው፣ ታማኝ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችል መንገድ እንዲከተሉ መርዳቱን እና በሁለተኛው ሺህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የባህሬን መንግሥት የሴቶች ጠቅላይ ምክር ቤት ማቋቋሙን አስታውሰዋል።