በሱዳን ያለው የሰብአዊ ቀውስ ጉልህ የሆነ መፈናቀል አስከትሏል በሱዳን ያለው የሰብአዊ ቀውስ ጉልህ የሆነ መፈናቀል አስከትሏል  (AFP or licensors)

ዩኒሴፍ ዳርፉር ውስጥ የሚገኙ ህፃናት በሰብአዊ አደጋ ውስጥ ተጠምደው እንደሚገኙ ገለጸ

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው በበሃገሪቷ ከ5,700 በላይ ህፃናት ላይ በተፈፀመ ከባድ የመብት ጥሰቶች ቢያንስ 5,100 ህፃናት ላይ ጉዳት መድረሱን እና ከ4,300 በላይ የሚሆኑ ህፃናት ደግሞ መገደላቸውን ወይም አካል ጉዳተኛ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አዲስ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው ‘በዳርፉር ህፃናት ለ20 ዓመታት በስጋት ውስጥ ናቸው” በሚል ርዕስ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በህፃናት ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እየተባባሰ መምጣቱን እና ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን በማመላከት አዲስ ሪፖርት ያወጣ ሲሆን፥ በተለይም በምዕራብ ሱዳን የሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ በሆነችው አል ፋሸር በርካታ ህፃናት ህይወት ማለፉን እና የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቁሟል።

ሪፖርቱ እንዳመላከተው በህፃናቱ ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች መካከል አብዛኛዎቹ በፈንጂዎች፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት፣ አፈና እና በታጣቂ ቡድኖች ያለፍላጎት መመልመልን እንደሚያካትቱ አብራርቷል።

በሱዳን እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ግጭት መጠነ ሰፊ ብጥብጥ፣ የጅምላ መፈናቀል እና ከፍተኛ ረሃብ እንዳስከተለ የገለጸው የዩኒሴፍ ሪፖርት፥ በርካታ ቤቶች መውደማቸውን፣ የገበያ ስፍራዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን አመላክቷል።

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እንደገለጸው በዳርፉር ዙሪያ አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮች ውድመት ድርቅን፣ ረሃብን እና በሽታን ማስፋፋቱን ጠቁሞ፥ የተራዘመው ግጭት እና ከበባ ቤተሰቦችን ያለ ምግብ፣ ንፁህ ውሃ እና የጤና አጠባበቅ በማስቀረት በርካታ ሰዎች ወደተጨናነቁ አካባቢዎች እንዲሰደዱ ማስገደዱን ገልጿል።

መሠረተ ልማቶች መውደማቸው
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት የትምህርት እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን ማጣታቸውን፥ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው በርካታ ሰዎች በታጣቂ ሃይሎች ወይም ቡድኖች ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በሽታ እና ጥቃት መገለጣቸውን ይፋ ያመላከተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋሙ በርካታ ቤተሰቦች ድንበሮችን አቋርጠው፥ በተለይም ወደ ምስራቃዊ ቻድ መሰደዳቸውን የገለጸ ሲሆን፥ ቀድሞውኑ በቂ ያልሆኑት በአካባቢው የሚገኙ አገልግሎት መስጫ ተቋማት አዲስ የሚመጡትን ስደተኞች ለማስተናገድ ከባድ ተግዳሮት እንደገጠመው ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እያለ ዩኒሴፍ እና አጋሮቹ በዳርፉር እና በአጎራባች ሀገራት የህይወት አድን እርዳታ ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን፥ ነገር ግን የጸጥታ ችግር፣ ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች እና የገንዘብ ድጎማዎች እጥረት ሰብዓዊ ጥረቶችን በእጅጉ እንዳደናቀፉ እና በርካታ ህፃናት ለአደጋ በሚጋለጡበት ጊዜ ድጋፍ እንደማያገኙ ሪፖርቱ ጠቁሟል።

ይህ በመሆኑም ምክንያት የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት - ዩኒሴፍ በግጭቱ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ዓለም አቀፍ ህግን እንዲያከብሩ እና ህፃናትን ጨምሮ ለሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፥ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ያልተገደበ ሰብዓዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንዲሁም በህፃናት ላይ የሚደርሱ ከባድ ጥሰቶችን ማቆም እና መከላከል እንደሚገባ አሳስቧል።

30 Apr 2026, 15:30