አንጎላ ውስጥ የሚያገለግሉ አንድ ሱዳናዊ ካህን ‘ሱዳን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን የሰላም መልዕክት ትፈልጋለች' ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
“በሱዳን ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው መለያየት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያበቃበት፣ ጥላቻና ብጥብጥ የሌለባት፣ የሙስና አስከፊነት በአዲስ የፍትህ እና የመጋራት ባህል የሚፈወስባትን አገር በጋራ መገንባት ይቻላል” ብለው የተናገሩት በአንጎላ ለ13 ዓመታት ያክል ያገለገሉት የሱዳናዊው ካህን ሃሳብ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በኪላምባ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ከተናገሩት ንግግር ጋር በጥልቅ እንደሚስማማ ተነግሯል።
በሉዋንዳ በሚገኘው የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከአራት ዓመታት በፊት የክህነት ማዕረግ የተቀበሉት አባ ሳሚር፥ በአሁኑ ወቅት በሉዋንዳ ሃገረ ስብከት ውስጥ በክህነት እያገለገሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለስብከተ ወንጌል እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአንጎላ በነበራቸው ቆይታ ሚያዝያ 12 ከብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ቅዱሳን ወንዶች እና ሴቶች፣ እንዲሁም በሉዋንዳ የሚገኘው እመቤታችን ፋጢማ ቁምስና ሃዋሪያዊ አገልግሎት ሠራተኞች ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ አባ ሳሚር ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት የአንጎላን ኅብረተሰብ ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸው፥ ሃገሪቷ ከማኅበራዊ ኢፍትሐዊነት እና ከድህነት ጋር እያደረገች ያለውን ትግል ያብራሩ ሲሆን፥ በተለይም “በቤተሰብ ውስጥ መከፋፈልን” ስለሚፈጥሩት እና በአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ለሚደረገው የወንጌል ስርጭት ስጋት የሆኑ አዳዲስ አመለካከቶችን ጠቅሰዋል።
“በእምነታችን እንድንጸና እንደ ጴጥሮስ ያለ ቅዱስ አባት እንፈልጋለን” ያሉት ካህኑ፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በስፍራው መገኘት “ጥልቅ የሆነ ደስታን” እንደሚሰጥ እና “ለሕዝቡ በርካታ ጸጋን እንደሚያመጣ” ጠቁመው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በኪላምባ ባደረጉት ንግግር ያስተላለፉትን የሰላም መልዕክት በመጥቀስ፥ ‘አንጎላ የረጅም ዓመታት የጦርነት ታሪክ እንዳላት’ ያስታወሱ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት አንጎላ የ“ወንድማማችነት” እና የ“ክርስቲያናዊ መንፈስ” ይበልጥ ያስፈልጋታል ሲሉ አበክረው ተናግረዋል።
ለሱዳን የተደረገ የሰላም ጥሪ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአንጎላ ሰላም እንዲሰፍን ያቀረቡት ጥሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀያቸው የተፈናቀሉባት የትውልድ ሀገራቸው ሱዳንን ጨምሮ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የተደረገ ጥሪ መሆኑን ያመላከቱት አባ ሳሚር፥ የሱዳን ጦርነት ከዓለም አቀፉ ትኩረት ውጭ በመሆን የሰብአዊ ቀውሱን እያባባሰ ይገኛል ብለዋል።
“ስለ ሱዳን የሚናገሩት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው” ያሉት ካህኑ፥ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በርካታ ውጥረቶች እና የጦር ቀጠናዎች እንዳሉ ብናውቅም፥ ነገር ግን ለሱዳን ከዚህ የተሻለ ትኩረት እንዲሰጥ እንፈልጋለን ብለዋል።
ይህ በመሆኑም ምክንያት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለሰላም ያቀረቡትን ተደጋጋሚ ጥሪ እንደሚያደንቁ የገለጹት አባ ሳሚር፥ ብፁዕነታቸው “ጦርነት ይቁም፣ ጦርነት ይብቃ” ብለው የተናገሩትን ሐረግ በመጥቀስ፥ በሱዳን የሚያስፈልገው ነገር ይህ መሆኑን በአጽንዖት ገልጸዋል።
“ሱዳን ለረጅም ጊዜያት በጦርነት ስትሰቃይ ኖራለች” ያሉት ካህኑ፥ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተካሄደው ግጭት “ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ስደተኛ መሆናቸውን፣ በርካታ ሰዎች በስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን እና በርካታ ሰዎች ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ እንደሚገኝ ገልጸው፥ “ሱዳን የሁሉንም ሰው ትኩረት፣ እርዳታ እና ጸሎት ትፈልጋለች” በማለት አጠቃለዋል።