በደቡብ ኮሪያ ለሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል አምስት ቅዱሳን መሰየማቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሴኡል ከሐምሌ 27 እስከ ነሐሴ 2/2019 ዓ. ም. ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል አምስት ቅዱሳን መምረጣቸውን ያስታወቀው ኮሚቴው (LOC)፥ ቅዱሳኑ የተመረጡት የዝግጅቱ የእውነት፣ የፍቅር እና የሰላም ጭብጦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ተናግሯል።
የቅዱሳኑ የስም ዝርዝር የዓለም ወጣቶች ቀን መሥራች የሆኑትን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን፣ የኮሪያ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕታት ቅዱስ አንድሪው ኪም ታጎን እና ጓደኞቻቸውን ያካተተ እንደሆነ ታውቋል። የስም ዝርዝሩ በተጨማሪም ለስደተኞች ባበረከተው አገልግሎት የሚታወቀው ቅዱስ ፍራንሲስ ዛቪየር ካብሪኒ፣ ሕይወቷ በመከራ መካከል እምነትን የምትገልጽ ቅድስት ጆሴፊን ባኪታ እና በዲጂታል ዘመን ሕይወቱ ከወንጌል ምስክርነት ጋር የተያያዘው ቅዱስ ካርሎ አኩቲስን እንደሚገኝበት ታውቋል።
የቅዱሳኑ የስም ዝርዝሩ በጦርነት፣ በስደት፣ በባርነት እና በዘመናዊ ባህል ተግዳሮቶች የተገናኙ አኅጉራትን እና ትውልዶችን ያካተተ ሲሆን፥ አዘጋጆቹ እንደሚሉት ተሞክሮዎች ብዙ ወጣቶችን ዛሬ ከሚያጋጥሟቸው እውነታዎች ጋር እንደሚስማሙ አስረድተዋል።
የምርጫ ሂደቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. መጨረሻ ላይ የተጀመረ ሲሆን፥ በመላው አገሪቱ ውስጥ በወጣቶች፣ በሐዋርያዊ አገልጋዮቻቸው እና እረኞቻቸው ላይ የተደረጉ ጥናቶችን እና ውይይቶችን ያካተተተ እንደሆነ ታውቋል።
የፌስቲቫሉ የወጣት በጎ ፈቃደኞች ቡድን የቅዱሳንን ሕይወት እና መንፈሳዊነት በማጥናት፣ ጸሎቶችን እና የቅዱሳኑን ምሳሌነት በጽሑፍ ለማዘጋጀት ሁለት ወራት እንደፈጁበት ታውቋል።
በቅድስት መንበር የምዕመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል፥ ደጋፊ ቅዱሳኑ የፌስቲቫሉ መንፈሳዊ ዝግጅትን በመቅረጽ ረገድ ማዕከላዊ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።
“ደጋፊ ቅዱሳን በእያንዳንዱ የዓለም ወጣቶች ቀን ዝግጅት ውስጥ መሠረታዊ ሚና ይጫወታሉ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል፥ ወጣቶች፣ የፌስቲቫሉ አዘጋጆች እና ሐዋርያዊ እረኞች በእግዚአብሔር የጥሪ ስጦታ ላይ በማስተንተን ስለ ጥምቀት፣ ስለ ክህነት፣ ስለ ምንኩስና ሕይወት እና ስለ ጋብቻ ሕይወት በሚናገሩ ቅዱሳት ምስጢራት ላይ እንዲያስተነትኑ መጋበዛቸውን ገልጸው፥ “መጪው ዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ጭብጥ እንደሚያስታውሰን፥ ዓለምን ያሸነፈውን ክርስቶስን በመከተል በልግስና እና በድፍረት ምላሽ እንድንሰጥ ያበረታቱናል” ብለዋል።
ካርዲናል ፋሬል አክለውም፥ “የእነዚህ ደጋፊ ቅዱሳን ምስክርነት በተለይም በችግር እና በስደት ውስጥ በምትገኝ ዓለማችን ውስጥ ቅድስና የሩቅ ሃሳብ ሳይሆን ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማትኮር ለጥሪያቸው በልግስና ምላሽ እንዲሰጡ ያነሳሳቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል
የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ፒተር ሱን-ታይክ ቹንግ፥ “የተመረጡት አምስቱ ቅዱሳን ለወጣቶች ተጨባጭ ምሳሌዎችን ይሰጣሉ” ብለዋል። “የተመረጡት ቅዱሳን አኅጉራትን እና ትውልዶችን የሚወክሉ እና እንዲሁም እያንዳንዱን ወጣት ዛሬ በሚያጋጥሙት እውነታዎች መካከል እምነትን በተጨባጭ ለመኖር መንገድ የሚያሳዩ ናቸው” ብለዋል። “ወጣቶች ከእነዚህ ቅዱሳን ውስጥ ለሕይወት ምሳሌ የሚሆኑት እንዲያገኙ እና ለዓለም ወጣቶች ቀን ከሚያደርጉት ዝግጅት ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ትስስር እንደሚፈጥሩ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
የፌስቲቫሉ አዘጋጆችም በበኩላቸው፥ በይፋዊ መድረኮች በኩል ቅዱሳንን ማስተዋወቅ እና ከ2027 ስብሰባ በፊት ተሳትፎን ለማጠናከር ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን እንደሚያዘጋጁ ተናግረዋል።
“ከደጋፊ ቅዱስ ጋር ይተዋወቁ!” የሚል መስተጋብራዊ ዝግጅት መጀመሩን ገጸው፥ ይህም የመስተጋብሩ ተጠቃሚዎች ጥያቄዎችን እንዲመልሱ እና ከአምስቱ ቅዱሳን ውስጥ የየትኛው ሕይወት ይበልጥ እንደሚቀርብ እንዲያውቁ ይጋብዛል” ብለዋል።