ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሚያዝያ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በኪላምባ ከተማ ለተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ሰላምታ ሲያቀረቡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሚያዝያ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በኪላምባ ከተማ ለተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ሰላምታ ሲያቀረቡ  (@Vatican Media)

ሙዚቀኞች፣ ሚስዮናውያን እና የህክምና ባለሙያዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በኪላምባ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ መገኘታቸው ተነገረ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ በአራት የአፍሪካ ሃገራት እያደረጉት በሚገኘው ሐዋርያዊ ጉዞ ሦስተኛ መዳረሻ ሃገር በሆነችው አንጎላ እሑድ ሚያዝያ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በኪላምባ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ በርካታ ሰዎች መገኘታቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ሉዋንዳ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኪላምባ ከተማ ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴ ያሳረጉ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ሚያዝያ 11 ባሳረጉት በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከሉዋንዳ ብቻ ሳይሆን ከፖላንድ፣ ጣሊያን እና ከኡራጓይ ጭምር የመጡ 100,000 የሚሆኑ ሰዎች መሳተፋቸው ተገልጿል።

እምነትን በሙዚቃ መግለጽ
የአንጎላ እና የሳኦ ቶሜ ጳጳሳት ጉባኤን (CEAST) የሚወክሉ የሀገረ ስብከቶች እና የአህጉረ ስብከት መዘምራንን በመወከል በብሄራዊ ሉጠርጊያ ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት የተዋቀረው “ቮዜ 500” የተሰኘው የመዘምራን ህብረት ለመርሃ ግብሩ ትልቅ ድምቀት እንደሰጠው የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ የመዘምራን ህብረት ውስጥ የሙዚቃ ተጫዋች የነበረው ሉዊስ ሙክሲንዳ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የተሳተፉትን ሰዎች ለማስደሰት የተቻለውን ሁሉ ማድረጉን ገልጿል።

ሉዊስ በዚህ ዓይነት ዝግጅት ላይ ተገኝቶ የሙዚቃ መሳሪያ ሲጫወት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቁሞ፥ ይህ በጣም ጥሩ እድል እንደሆነ እና በጣም እንደተደሰተ ተናግሯል።

ከኡራጓይ እና ፖላንድ የመጡ ሚስዮናውያን
በሦስተኛው የትንሳኤ እሁድ በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በርካታ የካህናት ቡድን ነጫጭ የቅዳሴ ልብሶቻቸውን ለብሰው በመጀመሪያዎቹ ረድፍ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ሉዋንዳ በሚገኘው የሳኦ ፓውሎ ቁምስና ውስጥ በማገልገል አንጎላ ለበርካታ ዓመታት የኖሩት ኡራጓዊ ካህን አባ አንድሬስ አልጎርታ ይገኙበታል።

“ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከእኛ ጋር በመገኘታቸው በጣም ደስተኞች ነን” ያሉት አባ አንድሬስ ቅዱስ አባታችን በባህር ዳርቻ ላይ ለምትገኘው እና ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ለደረሰባት የቤንግዌላ ከተማ ሕዝብ ላሳዩት አጋርነት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሚያዝያ 10 ለአንጎላ ባለስልጣናት ባደረጉት ንግግር ተጎጂዎችን እና ቤታቸውን ያጡትን ሰዎች ማስታወሳቸውን ገልጸዋል።

ኡራጓዊው ሚስዮናዊ ካህን እንደገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የህዝቡን መከራ ለመካፈል በስፍራው መገኘታቸውን ጠቅሰው፥ ቅዱስነታቸው ለቤንግዌላ ከተማ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአንጎላ ህዝብ ቅርበታቸውን እና አጋርነታቸውን ለማሳየት ወደዚህ ስፍራ መምጣታቸውን አመላክተዋል።

ከአባ አንድሬስ በተጨማሪም ከፖላንድ የመጡት ‘ፍራንቺስካዊ የማሪያም ሚስዮናዊያን’ ገዳም አባል የሆኑት እህት ክርስቲና ዛክዌጃ በሃዋሪያዊ ሥራ እና በትምህርት ዘርፍ እንዲሁም በአንጎላ የሚገኘውን ገዳም በመመስረት ረገድ ትልቅ ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደነበረ ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት ከብፁዕነታቸው ሃዋሪያዊ ጉብኝት በርካታ ልምዶችን እያገኙ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት በአንጎላ ለሚደረገው አዲስ የወንጌል አገልግሎት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነገር እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በተልዕኮ ላይ የሚገኙ ዶክተሮች
ከካህኑ በተጨማሪ ‘ዲቫይን ፕሮቪደንስ ሆስፒታል’ ተብሎ በሚጠራው ሉዋንዳ ከተማ በሚገኘው ሆስፒታል ውስጥ በህፃናት ህክምና ዘርፍ ለሁለት ዓመታት እያገለገሉ የሚገኙት እና ከጣሊያን የመጡት ሰርጂዮ ፋቺኒ እና ኤሌኖራ ቢያሶቶ በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ሲሆን፥ እነዚህ ሃኪሞች የአከባቢው ህፃናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ እና በዚህም ላይ እየሰሩ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ኤሌኖራ ይሄንን አስመልክታ እንደገለጸችው አንዳንድ ጊዜ በጣም “አስቸጋሪ ሁኔታዎች” ውስጥ የሚያስገባ “ውስብስብ” ነገር እንደሚገጥማቸው ጠቁማ፥ ሆኖም ግን ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጻለች።

ሰርጂዮ በበኩሉ አሁን በሚታየው አስቸጋሪ እውነታ ውስጥም ቢሆን ተልዕኳቸው ወደ አናሳ እና ወደ ተገለሉ ሰዎች እንደሚያቀርባቸው ጠቁሞ፥ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያላቸውን ቅርበት ለመግለጽ ለሚፈልጉት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፍራው መገኘት ጥንካሬን እንደሚሰጣቸው እና በሥራቸው በርትተው እንዲቀጥሉ ጉልበት እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።

የአንጎላ መለኮታዊ ቃል ሚስዮናውያን ገዳም ካህን የሆኑት አባ ዳንኤል ማላምባ በበኩላቸው አንጎላዊያን ክርስቲያኖች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን እንደ “የሰላም ተጓዥ” እና ለሃገሪቷ ተስፋን ይዘው እንደመጡ አድርገው መቀበላቸው የደስታ ምንጭ እንደሆነ ገልፀው፥ ሕዝቡ አሁንም “ማህበራዊ ሰላም፣ የልብ ሰላም እና ፍጹም አብሮ የመኖር ሰላም” ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

20 Apr 2026, 14:25