በእየሩሳሌም የትንሳኤ ክብረ በዓል በቅዱስ ጸባኦት ቤተ ክርስቲያን እንደሚከበር ተረጋገጠ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የእየሩሳሌም መንበረ ፓትርያሪክ እና የቅድስት ሀገር ጥበቃ ማህበረ ልኡካን ጽህፈት ቤት በጋራ ባወጡት መግለጫ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት፣ የተቀበረበት እና ከሙታን የተነሣበት አከባቢ ላይ በሚገኘው በቅዱስ ጸባኦት ቤተ ክርስቲያን ስለሚከበረው የህማማት ሳምንት እና የትንሳዔ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ አረጋግጠዋል።
ከእስራኤል ፖሊስ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በቅዱስ ጸባኦት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲደረጉ የነበሩ ጥንታዊ የትንሳዔ በዓል የአከባበር ልማዶችን ጠብቆ ለማቆየት እና ሥርዓተ አምልኮዎችን ለማከናወን የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ተደራሽነት እንዲኖር ጥበቃ እንደሚደረግ የገለጸው መግለጫው፥ ይህ ስምምነት የተደረሰው የሆሳዕና በዓልን ለማክበር እና የህማማት ሳምንትን ለማስጀመር ባለፈው እሁድ መስዋዕተ ቅዳሴን ለማሳረግ በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት የምትከተል ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ እና የቅድስት ሀገር ጥበቃ ገዳም ካህን የሆኑት ፍራንቺስኮ ኢልፖ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊገቡ ሲሉ በእስራኤል ፖሊስ መከልከላቸውን ተከትሎ በተደረገ ውይይት እንደሆነ ተገልጿል
የብጹዕ ካርዲናል ፒዛባላ ጽህፈት ቤት እንደገለጸው የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ የሆሳዕና በዓል ለማክበር ወደ ቅዱስ ቦታው እንዳይገቡ ሲከለከሉ “በዘመናት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ” እንደሆነ አስታውሷል።
በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፉት ክብረ በዓላት
ከዚህም ባሻገር የጋራ መግለጫው እንዳስታወቀው “አሁን ካለው የጦርነት ሁኔታ አንፃር በህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ያሉ እገዳዎች አሁንም እንደፀኑ መሆኑን ጠቅሶ፥ በዚህ ምክንያት አብያተ ክርስቲያናት ከስፍራው የሚከናወኑ መስዋዕተ ቅዳሴ እና የጸሎት ሥነ ስርዓቶችን በቀጥታ ስርጭት እንደሚያስተላልፉ ተገልጿል።
የሃይማኖት መሪዎቹ የእስራኤል ፕሬዝዳንት የሆኑት አይዛክ ሄርዞግ ላደረጉት ወቅታዊ እና ወሳኝ ጣልቃገብነት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ከእርሳቸውም በተጨማሪ አብዛኛዎቹ በግላቸው ያላቸውን ቅርበት እና ድጋፍ ለገለፁት እና በአስቸኳይ እርምጃ ለወሰዱት የአከባቢው መሪዎች እና ባለስልጣናት ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።
የሃይማኖት ነፃነት እንደ ሁለንተናዊ እሴት
መግለጫው በማከልም ሃይማኖታዊ እምነት ሁሉም ሀይማኖቶች ማለትም፣ አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ ድሩዛዊያን እና ሌሎችም የሚጋሩት ከሁሉም የላቀ የሰው ልጅ እሴት መሆኑን ጠቅሶ፥ በተለይም በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ችግሮች እና ግጭቶች በጸኑበት ወቅት የአምልኮ ነፃነትን መጠበቅ መሰረታዊ እና የጋራ ተግባር ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጿል።
ቀጣይነት ያለው ውይይት እና የሰላም ተስፋ
የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች “በአምልኮ ቦታዎች በተለይም በተቀደሱ ስፍራዎች፣ እንዲሁም በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ጸሎት እንዲደረግ የሚያስችል” ተገቢ መፍትሄዎች እንደሚገኙ ያላቸውን ተስፋ የገለጹ ሲሆን፥ ይህም ይሆን ዘንድ ቤተክርስቲያኗ የእስራኤል ፖሊስን ጨምሮ ከባለሥልጣናት ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት እንደምታደርግ እና አጠቃላይ ቀጠናውን በእጅጉ የሚጎዳው ጦርነት እንዲቆም ጸሎቷን በማደስ እንደምታቀርብ አመላክተዋል።
መግለጫው በመጨረሻም ‘የኢየሩሳሌም የላቲን መንበረ ፓትርያርክ እና የቅድስት ሀገር ጥበቃ ጉባዔ ጽህፈት ቤት ለውይይት፣ እርስ በርስ መከባበር እና ነባራዊ ሁኔታን ለመጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋግጣሉ’ በማለት አጠቃሏል።