አባ ኢኖሴንሶ ሞይስ ሚያዝያ 13 በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ስም የተሰየመው የብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ ምርቃት ላይ አባ ኢኖሴንሶ ሞይስ ሚያዝያ 13 በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ስም የተሰየመው የብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ ምርቃት ላይ 

የክላሬቲያን ካህን የሆኑት አባ ሞይስ በኢኳቶሪያል ጊኒ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ለውጥ ማሳየቷን ገለጹ

የኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ በሆነችው ማላቦ እያገለገሉ የሚገኙት እና እ.አ.አ. በ 1849 ዓ.ም. በቅዱስ አንቶኒ ሜሪ ክላሬት በስፔን ሃገር ውስጥ የተመሰረተው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሆነው የክላሬቲያን ማህበር ካህን የሆኑት አባ ኢኖሴንሲዮ ሞይስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ አብዛኛው ዜጎቿ ካቶሊክ በሆኑባት ሃገር ውስጥ እያደረጉት የሚገኘውን ሃዋሪያዊ ጉብኝት ያለውን ጠቀሜታ ካቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሃሳባቸውን ያጋሩ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 1982 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለመጨረሻ ጊዜ ካደረጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት በኋላ በኢኳቶሪያል ጊኒ የምትገኘው ቤተክርስትያን የተለወጠችባቸውን ቁልፍ መንገዶች በማስታወስ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከ44 ዓመታት በፊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ኢኳቶሪያል ጊኒን በጎበኙበት ወቅት ህፃን ልጅ የነበሩት አባ ሞይስ፥ አሁን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሃገራቸውን በሚጎበኙበት ወቅት የሃገረ ስብከቱ አስተባባሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ በዚህም ተግባራቸውም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አባ ሞይስ ‘ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ካምፓስ’ ተብሎ በተሰየመው በማላቦ የሚገኘው ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ የምርቃት ሥነ ስርዓት ወቅት ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት የቅዱስ አባታችን አብዛኛው ህዝብ ካቶሊክ በሆኑባት ሃገር ውስጥ መገኘት ያለውን ጠቀሜታ አስመልክተው ሃሳባቸውን ያጋሩ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ከ 1982ቱ ሃዋሪያዊ ጉብኝት በኋላ የክህነት ጥሪ እና የአጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት መስፋፋትን ጨምሮ ቤተክርስቲያን የተለወጠችባቸውን ቁልፍ መንገዶች ጠቅለል ባለ መልኩ አቅርበዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የኢኳቶሪያል ጊኒ ሃዋሪያዊ ጉብኝት አስፈላጊነትን አስመልክተው እንደተናገሩት በእውነቱ ይህ ለእርሳቸው ልዩ ጊዜ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ሲመጡ በወቅቱ ልጅ እንደነበሩ እንዲሁም ጉብኝቱ ለአጭር ሰዓታት ብቻ እንደነበር እና ሁነቱን በጥቂቱ ብቻ እንደሚያስታውሱ ገልጸዋል።

ከአርባ አራት ዓመታት በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አብዛኛው ህዝቦቿ ካቶሊክ የሆኑባትን ሃገር ለመጎብኘት በመምጣታቸው እድለኛ መሆናቸውን የጠቀሱት አባ ሞይስ፥ ለመርሃ ግብሩ ያዘጋጁት መዝሙር እንደሚገልጸው ሃዋሪያዊ ጉብኝቱ ለአብዛኛው ሰው የተስፋ እና የደስታ ምንጭ መሆኑን አስረድተዋል።

“የምንኖረው በርካታ ቤተሰብ ችግር ውስጥ በሚገኝበት አውድ ውስጥ ነው” ያሉት ካህኑ፥ በተለይ ደግሞ አፍሪካ በተለያዩ ግጭቶች እና ጥላቻዎች ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ይህ ጉብኝት ትልቅ ተስፋን ይዞ እንደሚመጣ ጠቅሰው፥ ይህ ወቅት የተስፋ፣ የአንድነት እና እምነታችንን የምናጠናክርበት ወቅት ነው ብለን እናምናለን ብለዋል።

“በዚህ አከባቢ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እና የተለያዩ ቤተ እምነቶች ስላሉ ወንጌልን በመስበክ ብዙ ጊዜ አሳልፈናል” ያሉት ካህኑ፥ ነገር ግን ህዝቡ ሃይማኖቱን በትክክል እንዲረዳ የካቶሊኮችን እና የክርስቲያኖችን እምነት ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተው፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት የቅዱስ አባታችን ጉብኝት ለእርሳቸው ትልቅ ማበረታቻ፣ እጅግ ጠቃሚ እና ልዩ እንደሆነ አመላክተዋል።

አባ ሞይስ ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ይሄንን ጉብኝት እንደ ባህላዊ ትዕይንት ጊዜ ብቻ አድርገው ሊመለከቱት እንደሚችሉ አስታውሰው፥ ነገር ግን ምዕመናን ብቻ ሳይሆን ካህናት እና ገዳማዊያትም ጭምር፣ አብዛኛው ህዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጠብቀው የኖረ እንደ አንድ ተጨማሪ የመታደስ ምንጭ እንደሚመለከተው አስረድተዋል።

እ.አ.አ. በ 1982 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሃገሪቷን ከጎበኙ በኋላ በኢኳቶሪያል ጊኒ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የተለወጠችበትን መንገድ የተጠየቁት ካህኑ፥ ቤተክርስቲያኒቷ በጣም መለወጧን ጠቁመው፥ የክላሬቲያን ማህበር አባል ስለሆኑ ሳይሆን፥ ነገር ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ እንደተናገሩት ሃገሪቷ ውስጥ የወንጌል ስርጭት በአብዛኛው የሚከናወነው በክላሬታውያን እንደነበር አስታውሰው፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት በስፍራው የምትገኘውን ቤተክርስቲያን በወንጌል ስርጭት ያስፋፉት በአብዛኛው ክላሬታዊያን እንደነበሩ አስረድተዋል።

ለዚህም ክብሩን ለእግዚአብሔር እና ለመንፈስ ቅዱስ የሰጡት አባ ሞይስ፥ በአሁኑ ወቅት በእዚህ አከባቢ በርካታ ሃይማኖታዊ ጉባኤዎች እና የሃገረ ስብከቶች ካህናት መኖራቸውን ጠቁመው፥ በዚህም ሰፊ አጥቢያ ቤተክርስቲያን መሆኗን እና ከሌላ ሃገራት የሚመጡ ሚስዮናውያን በየጊዜው እየቀነሱ መምጣታቸውን እንዲሁም በየሃገረ ስብከቱ የሚሾሙት ብፁዓን ጳጳሳት የሃገሬው ተወላጅ መሆናቸው የኢኳቶሪያል ጊኒ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥንካሬ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በአከባቢው የሚታየው ነገር በተሻለ ሁኔታ እየተለወጠ መሆኑን ያስታወሱት አባ ሞይስ፥ ቀደም ሲል ሚስዮናውያን ሊደርሱባቸው በማይችሉባቸው በጣም ሩቅ ወደሆኑ አካባቢዎች እንኳን ሳይቀር ጉልበታቸውን ለመስጠት ዝግጁ የሆኑ በርካታ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቁመው፥ ከዚህም ባለፈ የእርሳቸውን ማህበር ጨምሮ ሁሉም ሃይማኖታዊ ጉባኤዎች በአሁኑ ወቅት በአከባቢው እንደሚንቀሳቀሱ አስረድተዋል።

በስፍራው ከሚያገለግሉ ሃምሳ ያክል ክላሬታዊያን መካከል ከሁለቱ በስተቀር ሁሉም የሃገሬው ተወላጆች ማለትም ጊኒያዊያን መሆናቸውን የጠቆሙት ካህኑ፥ ይህ ደግሞ በሚስዮናዊ መንፈሳቸው በኩል በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የህይወት መንገድ እንዲቀበሉ ያነሳሳቸው የሀገረ ስብከቱ ካህናት እና ገዳማዊያት መሆናቸውን አመላክተዋል።

በአከባቢው የሚገኘውን የሃይማኖታዊ ጥሪ ምስረታ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው አባ ሞይስ በርካታ ወጣቶች ለሃይማኖታዊ የሕይወት ጥሪ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ጠቁመው፥ ለዚህም ማሳያ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ መስፋፋት የነበረበት ቢሆንም በባታ ከተማ የሚገኘው የሀገረ ስብከቶች የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት መሙላቱን አመላክተዋል።

ሆኖም ግን ለምን እንደሆነ ባይታወቅም ይህ ስኬት በሴቶች ጉባኤዎች ውስጥ እየተፈጸመ እንዳልሆነ የጠቆሙት ካህኑ፥ በአሁኑ ወቅት ለወጣት ሴቶች ሃይማኖታዊ ህይወትን መቀበል በጣም አስቸጋሪ የሆነበትን ምክንያት ማጥናት እና መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምናልባትም የሴት ጉባኤዎች የአካዳሚክ ምስረታ አቀራረባቸውን እንደገና ማጤን እንዳለባቸው የግል አስተያየታቸውን የሰጡት አባ ሞይስ፥ በተለያዩ ምክንያቶች ከዚህን በፊት የትምህርት አሰጣጡ በጣም ውስን እንደነበር አስታውሰው፥ በአሁኑ ወቅት ግን የ17 እና የ18 ዓመት ታዳጊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ለከፍተኛ ትምህርት ፍላጎት ከሌላት ይህ ትልቁ ችግር ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል።

ወጣት ሴቶችን ለተሻለ የትምህርት ዝግጅት ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን የሚመክሩት ካህኑ፥ ወደ ሃይማኖታዊ ጉባኤዎች የሚገቡ በርካታ ሴቶች የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ምኞት ቢኖራቸውም፥ ነገር ግን የሃይማኖታዊ ትምህርቱን ብቻ ይከታተሉና ይሄም የትምህርት ህይወታቸው መጨረሻ እንደሚሆን አስታውሰው፥ በእርሳቸው አመለካከት ይህ ሁኔታ ትክክል እንዳልሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ በወንድ ጉባኤዎች ወይም ካህናት ላይ እንደማይከሰት የጠቆሙት አባ ሞይስ፥ ምክንያቱም ካህናቱ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው እንዲከታተሉ እድል ስለሚሰጣቸው መሆኑን አስረድተው፥ አንዲት ወጣት ሴት ግን ይህን ማድረግ ካልቻለች ይህ ትልቁ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መዘናጋት ሳይኖር የጥሪ አገልግሎትን ማጠናከር እንደሚገባ ያመላከቱት አባ ሞይስ በመጨረሻም፥ ተመሳሳይ መልዕክት በአዲስ መንገድ ማስተላለፍ እንደሚገባ፣ ቋንቋን ማስተማር፣ አሁን ያለውን ጊዜ መረዳት እና ባለፈው ዘመን ውስጥ ተጣብቆ አለመቆየት እንደሚገባ አሳስበው፥ ወንጌልን ወይም የወንጌል አስተምህሮዎችን መቀየር ባይቻልም፥ ነገር ግን ከጊዜው ጋር ማስማማት ይገባናል በማለት አጠናቀዋል።

22 Apr 2026, 14:20