ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ የ 2017 ዓ.ም. የትንሳኤ በዓል ወቅት በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ የ 2017 ዓ.ም. የትንሳኤ በዓል ወቅት በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ  

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ‘ኢየሩሳሌም የዓለምን ቁስሎች ለመፈወስ ተጠርታለች’ ማለታቸው ተነገረ

ከኢየሩሳሌም የላቲን መንበረ ፓትርያርክ የወጣው አዲስ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ በቅድስት ምድር እየተካሄደ ስላለው ጦርነት አጽንዖት የሰጠ ሲሆን፥ ‘በአከባቢው የተከሰተው ግጭት አንድን ዘመን የዘጋ እና ሌላኛውን ዘመን የከፈተ’ መሆኑን ጠቅሶ፥ ይህም ሲሆን በከፋ መልኩ እንደሆነ አብራርቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
“በአሁኑ ወቅት ቅድስት ሀገርን እያስጨነቀ ባለው ግጭት ውስጥ ክርስቲያኖች እንዴት መኖር አለባቸው?” የሚል ጥያቄን ማዕከል ያደረገው እና የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ተጽፎ ሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. የተለቀቀው ሃዋሪያዊ ደብዳቤ “በታላቅ ደስታ ወደ እየሩሳሌም ተመለሱ፥ በቅድስት ሀገር የቤተክርስቲያን ጥሪን የመኖር ሀሳብ” በሚል ርዕስ መውጣቱ ተነግሯል።

የዓለምን ቁስሎች ለመፈወስ
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በፃፉት ሃዋሪያዊ ደብዳቤ ውስጥ ‘የኢየሩሳሌም ጥሪ የዓለምን ቁስሎች መፈወስ’ እንደሆነ የጠቆሙ ሲሆን፥ የፓትርያርኩ ሃሳብ የሚያጠነጥነው ‘በሲቪሉ እና በሃይማኖቶች መካከል ያለውን አብሮ የመኖር እና የመልካም ግንኙነት ነጸብራቅ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነችው የኢየሩሳሌም ከተማ አጠቃላይ ምስል ላይ እንደሆነ ተነግሯል።

ደብዳቤው በሦስት ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን፥ የመጀመሪያው የክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ የሚገመግም መሆኑን፥ ሁለተኛው የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ራዕይን እንዲሁም ሦስተኛው ክፍል ደግሞ በአጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት፣ ቤተሰቦች፣ ትምህርት ቤቶች እና ተቋማት ላይ ያለውን የሃዋሪያዊ ሥራዎች አንድምታ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ተነግሯል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ሃዋሪያዊ ደብዳቤውን አስመልክተው እንደተናገሩት ደብዳቤው ጥብቅ የሆነ የፖለቲካ ትንታኔ እንዳልያዘ አፅንዖት ሰጥተው በመግለጽ “ፖለቲካዊ” የሚባለው ሰፋ ባለ መልኩ ብቻ ከታየ እንደሆነ፥ ይህም ሁልጊዜም ወደ እውነተኛው እና ግልጽ ወደሆነችው ወደ ሰማያዊቷ እየሩሳሌም እያመራን እስከሆነ ድረስ እና እንደ ክርስቲያኖች በእውነታው ውስጥ መቆየታችንን ወይም በነባራዊው ዓለም ውስጥ እንደመኖራችን ስለሚመለከተን ነው ብለዋል።

ወሳኝ የሆኑ ክስተቶች
ፓትርያርክ ፒዛባላ ጦርነቱ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተጀመረበትን መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲገልጹ “በጣም በሚያሳዝን እና በከፋ ሁኔታ አንዱ ዘመን የተዘጋበት እና ሌላኛው የተከፈተበት ወሳኝ የሆነ ቀን” መሆኑን በማመላከት፥ እያጋጠመን ያለው የአካባቢ ግጭት ብቻ ሳይሆን በጣም ጥልቅ የሆነ እና የዓለም አቀፋዊ ለውጥ ምልክት እንደሆነ ያስረዱ ሲሆን፥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና በተለይም የምዕራቡ ዓለም፣ በመተዳደሪያ ደንብ፣ ስምምነቶች እና በባለብዙ ወገንተኝነት ላይ በተመሰረተው ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ያምን እንደነበር፥ ዛሬ ግን በሚያሳዝ ሁኔታ ሁሉም ነገር ተቀይሮ ሌላ መስመር እንደያዘ ሁሉም ሰው ይገነዘባል ብለዋል።

“አለመግባባቶችን ለመፍታት የኃይል አጠቃቀምን እንደ ወሳኝ መንገድ እያየን ነው” ያሉት ብፁዕ ካዲናል ፒዛባላ፥ “ጦርነት ሴይጣናዊ ተግባር ማስፈጸሚያ ሆኗል” በማለት ገልጸዋል።

የግጭት ውጤቶች
በቃላት እና በምስሎች በታጀበው በዚህ ጦርነት ትክክለኛ ዜናውን ከፕሮፓጋንዳ ለመለየት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት የኢየሩሳሌም ፓትርያርኩ፥ ይህ ትርምስ የሚያስከትለውን መዘዝ በጥላቻ እና አለመተማመን የተመረዙ ግንኙነቶችን በማዳበር እና በማህበራዊ ሚዲያ ስልተ ቀመር በተጠናከረ መልኩ ወደ እርስ በርስ መጠላለፍ እና የማንነት ቀውሶች መሸጋገሩን ጽፈዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ግጭቱ ሌላኛው ከሚያስከትላቸው አሉታዊ ተጽእኖዎች መካከል የሃይማኖት ተቋማት ውይይቶችን የሚያዳክም መሆኑን ገልጸው፥ “የጸሎት ቦታዎች ሊሆኑ የሚገባቸው ቅዱሳን ቦታዎች ማንነትን በተመለከተ የጦር አውድማ እየሆኑ መምጣታቸውን ያመላከቱ ሲሆን፥ “ይህ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ ማንሳት የዘመናችን ትልቁ ኃጢአት ነው ብዬ አምናለሁ” በማለት አክለዋል።

የቅድስት ከተማ ምስል
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትሪያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በቅድስት ከተማ ስላለው ሁኔታ ሲያስረዱ በኢየሩሳሌም የምትገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንኳን የተከሰተውን ችግር አስመልክታ ድምጿን በሐቀኝነት፣ በግልጽ እና በድፍረት ማሰማቷን ያስታወሱ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ይህ በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፥ በዚህ በጣም ፈታኝ በሆነ ወቅት አንዳንድ ጊዜ ጥንቃቄን መርጠን እና ተቋማዊ ሕልውናን ፈልገን ትንቢታዊ ምስክራችንን መስዋዕት አድርገን እናውቃለን ወይ ብለን እንጠይቃለን ያሉት ፓትሪያርኩ፥ “ይህ በየዕለቱ የሚያስጨንቀኝ እና ለመመለስ ቀላል ያልሆነ ጥያቄ ሆኖ ይሰማኛል” ብለዋል።

የእየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በፃፉት ሃዋሪያዊ ደብዳቤ ላይ አንድ ሰው እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም ያለው መልካም ፈቃድ ምን እንደሆነ መጠየቅ እንዳለበት ጠቁመው፥ እየሩሳሌም የፖለቲካ ድንበሮች ወይም ቴክኒካል አደረጃጀት ጉዳይ ብቻ ሳትሆን የከተማዋ እና የመላው ቅድስት ምድር እጅግ አስፈላጊ ባህሪ የሆነው ዋናው ማንነቷ የእግዚአብሔር የመገለጥ ቦታ እንዲሁም የተለያዩ እምነቶች መነሻ እና መገኛ ሥፍራ መሆኗ እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህንን የቅድስት ሀገርን “ወሳኝ” ገጽታ የሆነውን በውስጡ ያሉ ማህበረሰቦች ሃይማኖታዊ እና መንፈሳዊ አሻራ ችላ ማለት “ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የተከሰቱት አብሮ የመኖር ስምምነቶች ውድቀት ዋነኛው ምክንያት” እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸዋል።

በአከባቢው ያለው የሃዋሪያዊ ሥራ እንድምታ
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በአከባቢው ስላለው የሃዋሪያዊ አገልግሎት ደረጃ ሲያስረዱ ለመስዋዕተ ቅዳሴ እና ለጸሎት ቀዳሚ ሥፍራ እንደሚሰጥ አመላክተው፥ መጪው ትውልድ የጥላቻ እና የቂም በቀል ስሜትን ሳያዳብር ያለፈው ታሪክ በትክክል እና በእውነት ለትውልድ የሚተላለፍበት አብሮ የመኖር እና መከባበር ውስጥ የቤተሰብ ሚና ትምህርታዊ ተምሳሌት እንደመሆኑ መሰረታዊ እንደሆነ ገልጸዋል።

የክርስቲያን ትምህርት ቤቶች ህፃናት ከቂም በቀል ነፃ በሆነ ዓይን ታሪክን እንደገና እንዲያነቡ የሚማሩበት “የአዲስ የሰው ልጅ ወርክሾፖች” ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ፥ ሁሉንም የሰው ልጆች እኩል የሚቀበሉት ሆስፒታሎች እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ውይይቶች እና ፈውስ የሚገኙባቸው ቦታዎች ስለሆኑ መደገፍ አለባቸው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ፓትርያርኩ ሕያው ትውስታ ያላቸው አረጋውያን፣ ትንቢት የተነገረላቸው ወጣቶች፣ እንዲሁም ለማህበረሰቡ ታማኝ የማጣቀሻ ነጥቦች እና አብሮ የመኖር ምሳሌዎች የሆኑት ካህናት እና ገዳማዊያ በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፥ በማከልም በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይትም “እጅግ አስፈላጊ” ሆኖ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ደቀ መዛሙርቱ ከዕርገት በኋላ እንዳደረጉት
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ለእምነት ቦታ በመስጠት “ከጥቃት ባህል ጋር የሚጋጭ ማንኛውንም ነገር አለመቀበል” አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ ይሄንን ሁሉ ማድረግ የሚቻለውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር እንደሆነ እና ብቻችንን አለመሆናችንን አውቀን በመተባበር እንደሆነ አስረድተው፥ ‘በየቁምስናችን፣ በምዕመናን እንቅስቃሴዎች፣ በሥራ ቡድኖቻችን እና በቤተ ክህነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ አምላክ ይረዳናል’ ብለዋል።

“የሚደግፈን የራሳችን ጥንካሬ ሳይሆን ከወንጌል የምናገኘው ደስታ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በመጨረሻም፥ “ወደ ኢየሩሳሌም በደስታ እንመለስ” ካሉ በኋላ "ወደ ህይወታችን በጥልቅ የፍቅር ስሜት መመለስ እንደሚገባ እና የእግዚአብሔር መገለጥ ከተማ ለሆነችው ኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ህልም በልባችን መያዝ እንዳለብን ብሎም ህልማችን ደረጃ በደረጃ፣ ቀን በቀን፣ ህይወታችን እንዲሆን መፍቀድ እንደሚገባ በመምከር አጠቃለዋል።

29 Apr 2026, 14:07