ፈልግ

የቺካጎ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብሌዝ ጄ. ኩፒች በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ከምዕመናን ጋር የቺካጎ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብሌዝ ጄ. ኩፒች በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ከምዕመናን ጋር   (2025 Getty Images)

ካርዲናል ኩፒች፥ “ጦርነትን ጨዋታ ማስመሰል የሰላም ጥረቶችን እያዳከመው ይገኛል” ሲሉ ገለጹ

የቺካጎ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብሌዝ ጄ. ኩፒች፥ ‘ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው’ በሚል ከካቶሊክ ሥነ-መለኮታዊ ኅብረት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል። በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በ “ስክሪኖች” አማካይነት ሽምግልና የሚደረግባቸው ግጭቶች የሰውን ሕይወት ወደ መረጃነት የመቀነስ አደጋ እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቺካጎው ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብሌዝ ጄ. ኩፒች ረቡዕ ምሽት በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ከካቶሊክ ሥነ-መለኮታዊ ኅብረት የተሰጣቸውን ‘ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው’ ሽልማት ተቀብለዋል።

ካርዲናል ኩፒች በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዘንድሮ በተከበረው የሆሳዕና በዓል መልዕክታቸው፥ “ኢየሱስ ጦርነት የሚያካሂዱትን ሰዎች ጸሎት አይሰማም፣ አይቀበላቸውም” ማለታቸውን ጠቅሰዋል።

ብዙዎች በፍትሃዊ ጦርነት ፅንሰ-ሃሳብ አስፈላጊነት ላይ በመናገር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስተያየት ምላሽ መስጠታቸው የሚያሳዝን እንደሆነ ተናግረው፥ ይህ ምላሽ ሥነ-ምግባራዊ ግንዛቤ ያለው ሳይሆን እየሆነ ያለው ነገር አሁንም ፍትሃዊ ሊሆን እንደሚችል ለማረጋገጥ እንደ ጥረት መሰማቱን ተናግረዋል።

ካርዲናል ኩፒች “እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የተሳሳተ የመነሻ ነጥብ ነው” ብለው፥ ልናቀርብ የሚገባን የመጀመሪያው ጥያቄ፥ “ይህ ጦርነት ትክክል ሊሆን ይችላልን?” የሚል ሳይሆን “ቅዱስ ወንጌል አሁን ከእኛ ምን ይፈልጋል? በተጨባጭ ሰላም ፈጣሪዎች መሆን ምን ማለት ነው?” የሚል እንደሆነ አስረድተዋል።

የመንፈስ እርጋታ፣ ዘዴኛነት፣ አስተዋይነት እና ክህሎት

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትንም አድርጉ” በሚለው ሐዋርያዊ የማበረታቻ ምክራቸው ሰላምን ለመገንባት፥ የመንፈስ እርጋታ፣ ዘዴኛነት፣ አስተዋይነት እና ክህሎት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ካርዲናል ኩፒች አስታውሰዋል።

“ሰላም አስፈላጊ ነው” ያሉት ካርዲናል ኩፒች፥ “ግጭት ስለሌለበት ሳይሆን በግጭት ለመገዛት ፈቃደኛ ባለመሆን ነው” ብለው፥ በገናናነት አመክንዮ ውስጥ ሆኖ ለግጭት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሙሉ በሙሉ ሰላም ፈላጊ ደቀ መዝሙር በመሆን ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል ዘዴም እንደሚያስፈልግ የገለጹት ካርዲናል ኩፒች፥ “ግጭት በቀላሉ ሊጠፋ የሚችል ሳይሆን መለወጥ ያለበጥ፥ በተግባር ይህ ማለት ጠንካራ እና ታጋሽ የሆነ የውይይት እና የድርድር ሥራ፣ ማንኛውም ዋጋ የሚከፈልለት የስምምነት ስልት ሳይሆን ወደ ፍትህ የሚመራ የሞራል ሂደት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“አስተዋይነት ማለት ለግለሰብ በተለይም ለአስቸጋሪው ሰው ትኩረት መስጠት ማለት ነው” ያሉት ካርዲናል ኩፒች፥ “ስለ ሰው ልጅ ክብር ምንነት በአጭሩ መናገር ቀላል ቢሆንም ነገር ግን በሚያበሳጩን፣ በሚቃወሙን ወይም በሚያቆስሉን ሰዎች ዘንድ ይህንን መገንዘብ እጅግ ከባድ ነው” ብለው፥ “ሆኖም ግን ወንጌል የሚጠራን ለዚህ ተግባር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

እየጨመረ በመጣው የጦርነት "ጨዋታ" ምክንያት አስተዋይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ መምጣቱን ካርዲናል ኩፒች ተናግረው፥ “ግጭቶች በ‘ስክሪኖች’ አማካይነት ወደ ምስሎች እና ስትራቴጂያዊ ረቂቅ መግለጫዎች የሚቀየሩ ከሆነ የሰው ልጅ ሕይወት እንደ ሕይወት ሳይሆን እንደ መረጃ ነጥብ የመታየት አደጋ ላይ ይወድቃል” ሲሉ አስረድተዋል።

ለሰላም ግንባታ የሚያግዝ የመጨረሻው ቅድመ ሁኔታ ክህሎት እንደሆነ የገለጹት ካርዲናል ኩፒች፥ብዙውን ጊዜ የሰላም አስፈላጊነት በምኞት ወይም በስሜት እንደሚገለጽ ተናግረው፥ ነገር ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእጅ ብልሃት ብለው እንደሚጠሩት ገልጸው፥ ክህሎት መማርን፣ መለማመድን እና ማጥራትን እንደሚጠይቅ ተናግረው፥ የሚያስቆጡ ንግግሮችን የመገደብ ችሎታ፣ እውነትን ያለ ጥላቻ የመናገር ድፍረት፣ እምነትን በዕግስት በማሳደግ ለፍትህ ሲሉ የራስን ጥቅም የመተው ፍላጎት እንደሆነ አስረድተዋል።

የሰላም ባሕልን ማስተዋወቅ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅርቡ ወደ አራት የአፍሪካ አገራት ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፥ ሰላምን እና ጦርነትን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ላይ በማሰላሰል፥ ወደ ትክክለኛ የኃይል አጠቃቀም ረቂቅ ክርክር ውስጥ ሳይገቡ የሰላም ባሕል እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረባቸውን ካርዲናል ኩፒች አስታውሰው፥ መሪዎች ወደ ጦርነት ከመግባት ይልቅ ወደ ውይይት እንዲመለሱ እና ይህንን በንድፈ ሐሳብ ሳይሆን የሰውን ልጅ ስቃይ ለማስቀረት ያቀረቡትን ጥሪ መሠረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ካርዲናል ኩፒች በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ቅዱስነታቸው ብዙዎች በሚጠብቁት ደረጃ ለክርክር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ነገር ግን እንደ ሐዋርያዊ እረኛ፥ ኢየሱስ ስለ ብፁዓን የተናገረውን መጥቀሳቸውን በማስታወስ “እኛም እንዲሁ ማድረግ አለብን” ብለዋል።

 

30 Apr 2026, 16:48