ፈልግ

የጋዛ ግጭት ያስከተለው ውድመት የጋዛ ግጭት ያስከተለው ውድመት  

ብፁዕ አቡነ ሾማሊ ጋዛን እና ዌስት ባንክን መርሳት ዬለብንም ማለታቸው ተነገረ

በእየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት የምትከተል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሾማሊ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጋዛ እና ዌስት ባንክ ውስጥ “ሁለት ሚሊዮን ሰዎች አሁንም ድረስ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ” ጠቁመው፥ ለእነዚህ ሰዎች ዘላቂ የሆነ ትኩረት እንዲሰጥ መጠየቃቸው ተገልጿል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. ከ 2021 ዓ.ም. ጀምሮ የኢየሩሳሌም የላቲን መንበረ ፓትርያርክ አስተዳዳሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ዊልያም ሾማሊ ከቫቲካን ዜና ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በአሁኑ ወቅት የሁሉም ሰው ትኩረት በኢራን እና በደቡባዊ ሊባኖስ ላይ ስለሆነ ጋዛ ተረስታለች” ያሉ ሲሆን፥ ነገር ግን በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ አሁንም ድረስ ከባድ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ እና ጉዳዩ እልባት እንዳላገኘ ጠቁመው፥ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁንም ድረስ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እየተከናወነ ባለው ነገር ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ተማጽነዋል።

በሰርጡ ያለው ኢኮኖሚ ሽባ መሆኑን እንዲሁም መድሃኒቶች፣ አንቲባዮቲክስ እና የህክምና መሳሪያዎችን ጨምሮ በርካታ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከፍተኛ እጥረት እንዳለባቸው ያመላከቱት ጳጳሱ፥ በየቀኑ በጋዛ ፍልስጤማውያን እንደሚገደሉ እና የራፋህ መሻገሪያ በሚፈለገው መልኩ አገልግሎት እየሰጠ እንደማይገኝ ጠቁመው፥ “በአከባቢው ምንም ዓይነት ደህንነት እንደሌለ” አስጠንቅቀዋል።

ብፁዕ አቡነ ሾማሊ ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው የአከባቢው መሰረተ ልማት ፈራርሶ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ስለ መልሶ ግንባታው በአሁኑ ወቅት ማንም እንደማያነሳ በቁጭት አስታውሰው፥ አቅሙ ያላቸው እና የሚችሉ ሰዎች ከአካባቢው ሸሽተው እንደወጡ፣ ከእነዚህም ውስጥ አብዛዎቹ ወደ አውስትራሊያ እንደሚሄዱ እና ወደ 50 የሚጠጉ ቤተሰቦች አቀባበል እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።

 በዌስት ባንክ እየተካሄደ ያለ ሰፈራ

የፍልስጤም ግዛት በሆነው ዌስት ባንክ አከባቢ ውጥረቱ ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት ጳጳሱ፥ በዚህ አከባቢ እንደ ትልቅ ችግር እየታየ ያለው የሰፈራ ጉዳይ መሆኑን አንስተው፥ በአሁኑ ወቅት 200 የሚሆኑ ሰፈራዎች እንደተመዘገቡ እና ቁጥሩ እየጨመረ እንደሚሄድ አስረድተዋል።

የእስራኤል ሀሳብ ፍልስጤማውያንን በሦስት አካባቢዎች ብቻ መገደብ፣ መሬቱን ለመያዝ በከተሞች ዙሪያ ሰፈሮችን መገንባት እንዲሁም በይሁዳ እና በሰማርያ ስም ዌስት ባንክን ለመቀላቀል ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

 “እስራኤላዊያን ሰዎች በሂደት ቁጥራቸው እየተመናመነ የሄደውን የፍልስጤም ህዝብ መኖሩን እንዲረሱ ይፈልጋሉ” ያሉት ጳጳሱ፥ “የዚህ ሁሉ ዓላማ የፍልስጤም መንግስት መመስረትን ለመከላከል ነው” ብለዋል።

ለግንባታ የሚሆን መሬት የለም

የእስራኤል መንግስት ፍልስጤማውያን ተገድበው እንዲኖሩ የሚፈልጉባቸው ሶስቱ አካባቢዎች ኬብሮን-ቤተልሄም፣ ራማላህ እና በመጨረሻም ናቡስ እና ጄኒን እንደሆኑ ያስረዱት ጳጳሱ፥ ከዚህም ባሻገር በሰሜናዊ-ደቡብ መሸጋገሪያዎች አከባቢ አዳዲስ የእስራኤላዊያን ሰፈራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመው፥ በዚህም ምክንያት 53 በመቶ የሚሆነው የፍልስጤም ግዛቶች ምንም ዓይነት ግንባታ በተከለከለበት 'ኤሪያ ሲ' ተብሎ በሚታወቀው እና ሙሉ በሙሉ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለው ክልል ውስጥ ስለተካተቱ እና ለግንባታ የሚሆን መሬት ማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ እስራኤል የከተሞችን መስፋፋት መከልከሏን ገልጸው፥ እስራኤላዊያን ሰፋሪዎች ግን በዚህ ክልል በፈለጉት ቦታ ላይ መገንባት እንደተፈቀደላቸው አስረድተዋል።

 ክርስቲያን ማህበረሰቦችም በሰፋሪዎች ኢላማ መደረጋቸው

ብፁዕ አቡነ ሾማሊ የክርስቲያኑ ማህበረሰብ ግጭቱ ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመው፥ ታይቤ መንደር ውስጥ ሰፋሪዎች በፈለጉት ጊዜ እየገቡ ተሽከርካሪዎችን እንደሚያቃጥሉ እና በወይራ መከር ወቅት ገበሬዎች እርሻቸው ላይ እንዳይሰማሩ እንደሚከለክሉ ገልጸዋል።

ነገር ግን እነዚህ በአሁኑ ወቅት የዕለት ተዕለት ክስተቶች የሆኑ የመብት ጥሰቶች ምሳሌዎች እንጂ በርካታ ችግሮች እንዳሉ የገለጹት ጳጳሱ፥ በሌሎች ቦታዎች እንደ ቢር ዘይት እና አቡድ በመሳሰሉ መንደሮች ውስጥ ፍልስጤማዊያን እንደሚገደሉ የጠቆሙ ሲሆን፥ በዌስት ባንክ እና በኢየሩሳሌም በቁጥር አነስተኛ ማለትም 50,000 ያክል የክርስቲያኑን ማህበረሰብ እንዳለ ገልጸው፥ ሰፋሪዎች ድንጋይ እንደተወረወረባቸው ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግን ጨምሮ ሁከት ለመቀስቀስ የትኛውንም ዓይነት ሰበብ እንደሚጠቀሙ አስታውሰዋል።

ሰሞኑን በቤተልሔም አቅራቢያ በምትገኘው ቤቴ ሳሁር ከተማ ኦሽ ግራብ በሚባል አካባቢ የአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ በሆነ መሬት ላይ አዲስ ሰፈር እንደሚገነባ ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ሾማሊ፥ ይህ ቤተሰብ ሌላው ቀርቶ ወደዚያ አከባቢ መቅረብ እንኳን እንደማይችሉ ጠቁመው፥ ይህ ሁሉ ወደፊት የፍልስጤም መንግሥት እንዳይመሰረት ለመከልከል ታስቦ የሚደረግ ድርጊት እንደሆነ አስረድተዋል።

እየቀነሰ የመጣው የክርስቲያን መገኘት

ብፁዕ አቡነ ሾማሊ ከዚህም በተጨማሪም  በአከባቢው የክርስቲያኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለማቋረጥ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የገለጹ ሲሆን፥ ይህ ሁኔታ ወደፊትም እንደሚቀጥል አሳስበው፥ “ከ4ኛው እስከ 7ኛው መቶ ክፍለ ዘመናት የክርስቲያኑ ማህበረሰብ አብላጫውን ቁጥር የያዘ እንደነበር” አስታውሰው፤ ነገር ግን ከዚያን ጊዜ በኋላ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነስ እንደጀመረ አስረድተዋል።

እ.አ.አ. በ1291 የአክሬው የቅዱስ ዮሐንስ ከተማ በማምሉኮች ቁጥጥር ሥር ከወደቀች በኋላ ኢየሩሳሌም ፓትርያርክ እንዳልነበራት ያስታወሱት ጳጳሱ፥ ቤተክርስቲያኒቷን በሃላፊነት ሲያስተዳድሩ የነበሩት በሮም የሚገኘው ጳጳሳዊ ፍርድ ቤት ካህናት እንደነበሩ ገልጸው፥ ከዚያም እ.አ.አ. በ1847 የላቲን መንበረ ፓትርያርክ እንደገና ሲቋቋም 10 በመቶ ማለትም ወደ 21,000 የሚጠጋ የክርስቲያን ማህበረሰብ እንደነበር ጠቁመው፥ “በቁጥር አነስተኛ የነበርን ቢሆንም፣ በመቶኛ ሲታይ ግን ከፍተኛው ነበር” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በእስራኤል፣ በጋዛ እና በፍልስጤም ያሉ አረብኛ ተናጋሪ ክርስቲያኖች ቁጥር ከ 180,000 የማያንስ እንደሆነ እና ነገር ግን በመቶኛ ሲታይ አነስተኛ እንደሆነ ያስታወሱት ጳጳሱ፤ በዚህ ዘመን ይህ አሃዝ የተገላቢጦሽ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፥ “ምንም ቢሆን አምላክ ቤተክርስቲያን ከቅድስት ሀገር እንድትጠፋ አይፈቅድም፥ ነገር ግን እኛ በቅዱሳን ስፍራ አቅራቢያ የሚገኙ አነስተኛ መንጋ እንሆናለን” በማለት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የትንሳኤ በዓል ይከበራል

ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር ለተደረሰው ስምምነት ምስጋና ይግባውና የሆሳዕና በዓል ዕለት ከተፈጠረው "አለመግባባት" በኋላ በተደረገው ውይይት የደህንነት ገደቦች እንዳለ ሆነው ክርስቲያኖች የትንሳኤን በዓል ማክበር እንደሚችሉ የገለጹት ብፁዕ አቡነ ሾማሊ፥ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በአነስተኛ ቁጥር እንኳን ቢሆን በዓሉን ለማክበር ፈቃድ የጠየቁበትን ደብዳቤ ልከው እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ፖሊስ ለዚያ ደብዳቤ ምላሽ ለመስጠት እንዳሰበ ገልጸው፥ ማንም ሰው ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ሊቃረን እንደማይችል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊከበር የሚገባው እውነታ እንደሆነ አስረድተዋል።

ብፁዕ አቡነ ሾማሊ በመጨረሻም የህማማት ሳምንቱ አከባበር ቢበዛ 10 ሰዎች በሚገኙበት እንደሚከበሩም ጠቁመው፥ በዚህም አግባብ ምዕመናን የቤተክርስቲያኑን በር ከፍተው ከገቡ በኋላ በሩ እንደሚዘጋ እና ሥነ ሥርዓቱ አልቆ ሰዎች ወደየቤታቸው ከሄዱ በኋላ በሩ መልሶ እንደሚዘጋ፣ እንዲሁም ለምስራቅ የአምልኮ ሥርዓቶችም ተመሳሳይ ነገር እንደሚሆን በመግለጽ አጠቃለዋል።

02 Apr 2026, 16:23