ለቬትናም ወጣቶች አዲስ የወንጌላዊ ደቀ መዝሙርነት ጥሪ ቀረበ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቬትናም የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሃኖይ ሀገረ ስብከት ወደ 5,000 የሚጠጉ ወጣቶችን ያሳተፈውን ጉባኤ መጋቢት 13/2018 ዓ. ም. በማዘጋጀት ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቶች ከምቾት ወጥተው የተልዕኮ ሕይወትን እንዲቀበሉ አሳስበዋል።
በቱ ቻው ቁምስና የተካሄደው ጉባኤው በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ከሚገኙ ልዩ ልዩ ቁምስናዎች እና የሚስዮን ጣቢያዎች የተወጣጡ ተሳታፊዎችን በማሰባሰብ “ወደ እግዚአብሔር ቤት መጥታችሁ ኑሩ” በሚል መሪ ቃል የወጣቶች ስልጠና መርሃ ግብር አሥረኛ ዓመቱን አክብሯል።
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አባ ጆሴፍ ሉኦንግ ታህህ ቱንግ፥ ወጣቶች በሕይወታቸው አቅጣጫ ላይ እንዲያስቡበት በማሳሰብ “ወዴት እሄዳለሁ? ወደ ማን መሄድ እመርጣለሁ?” ብለው ራሳቸውን እንዲጠይቁ አሳስበዋል።
ወጣቶች በጊዜያዊ እሴቶች እና በአጭር ጊዜ ደስታ በተሞላ ዓለም ተታልለው ዓላማቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል፣ ከምቾት ለመውጣት እና ተጨባጭ መስዋዕትነት ለመክፈል ድፍረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ጉባኤው በወጣቶች በሚመሩ ሕያው እና ቀስቃሽ ተግባራት የተጀመረ ሲሆን፥ ቀጥሎም የስልጠና ክፍለ ጊዜ እና የጋራ ጸሎት ቀርበዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በቀጠልም በኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ ላይ በማሰላሰል እና የእግዚአብሔር ፍቅር ግንዛቤያቸውን በሚገባ በማሳደግ በመስቀል መንገድ ጸሎት ላይ ተሳትፈዋል።
የሃኖይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆሴፍ በመልዕክታቸው፥ “ወደ እግዚአብሔር ቤት መጥታችሁ ኑሩ” የሚለው ጥሪ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለ ዘላቂ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ “ወጣቶች ወደ ጉባኤው የመጡት ጊዜያዊ ስሜት ፍለጋ ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ዘላቂ ግንኙነት ለመመሥረት ነው” ብለዋል።
ከእግዚአብሔር ጋር መቆየት ወጣቶችን ወደ እምነት ምስክርነት እንደሚለውጥ ተናግረው፥ በቤተሰቦቻቸው፣ በቁምስናዎቻቸው እና በሥራ ቦታዎቻቸው “ሕያው ወንጌል” እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በጉባኤው ላይ 10ኛ ዓመቱን የሚያስታውሱ ባሕላዊ ዝግጅቶች እና በቬትናም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የወጣቶችን እምነት እና ጉልበት የሚገልጹ ትርኢቶች ቀርበዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መስዋዕተ ቅዳሴን ተሳትፈው የቅዱስ ቁርባን ቡራኬን ከተቀበሉ በኋላ ጉባኤው ተጥናቅቋል።