የየካቲት 29/2018 ዓ.ም 2ኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የዕለቱ ንባባት
1. ዘጸዐት 12፡1-4
2. መዝሙር 32
3. 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡8-10
4. ማቴ፡ 17፡1-9
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
የኢየሱስ መልክ መለወጥ
ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን ይዞአቸው ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትፈቅድስ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ደግሞ ለኤልያስ የሚሆን ሦስት ዳሶችን በዚህ እንሥራ” አለው። እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ እነሆ ከደመናው ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የተወደደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀመዛሙርቱ ይህንን ሰምተው በፊታቸው ወደቁ፤ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም መጥቶ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፥ አትፍሩ” አላቸው። ዐይኖቻቸውን በገለጡ ጊዜ ግን ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም።
ከተራራው እየወረዱ ሳሉ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ብሎ አዘዛቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ ጻፎች ‘ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል’ ለምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ኤልያስ በእርግጥ ይመጣል፤ ሁሉንም ያስተካክላል፤ ነገር ግን ኤልያስ ከዚህ በፊት መጥቷል እላችኋለሁ፤ ነገር ግን የፈለጉትን ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበላል” አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አወቁ።
ኢየሱስ ጋኔን ያደረበትን ልጅ እንደ ፈወሰ
ወደ ሕዝቡም በመጡ ጊዜ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ! ልጄን ማርልኝ፥ በሚጥል በሽታ ክፉኛ ይሣቀያል፤ ብዙ ጊዜ በእሳት ላይ ብዙ ጊዜ ደግሞ በውሃ ውስጥ ይወድቃልና። ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “የማያምንና ጠማማ ትውልድ ሆይ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት” ኢየሱስም ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፤ ልጁም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ከዚህ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀርበው “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” አሉት።
የእለቱ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
"የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እሕቶቼ እንደምን ከረማችሁ!
በዚህ የዐብይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት እሑድ እለት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል የኢየሱስ መልክ በቅጽበት መቀየርን ይተርክልናል። ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ከእርሱ ጋር ይዞ ወደ ተራራው ወሰዳቸው እና እርሱ ተወዳጅ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ተገለጠላቸው (ማቴ. 17፡1-9)።
በዚህ ትዕይንት ላይ ለአፍታ ቆም ብለን እራሳችንን እንጠይቅ፡- ይህ ውበት ምንን ያካትታል? ደቀ መዛሙርቱ ምን አዩ? ልዩ ውጤት አዩ ወይ? በፍጹም እንዲህ አይደለም። የእግዚአብሔር ቅድስና ብርሃን በፊቱ እና በኢየሱስ ልብስ ላይ ሲያበራ ያዩታል፣ ፍጹም የአብ ምስል እንደ ሆነ ይመለከታሉ። የእግዚአብሔር ግርማ ፣ የእግዚአብሔር ውበት ይገለጣል። እግዚአብሔር ግን ፍቅር ነው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ በክርስቶስ በሥጋ የተገለጠውን መለኮታዊ ፍቅር ውበት እና ግርማ በአይናቸው ይመለከቱ ነበር። የገነት ቅድመ-ቅምሻ ነበራቸው። ለደቀ መዛሙርቱ ምንኛ የሚያስገርም ነገር ነው! እንዴት እንደሚያምር ሳያውቁ ለረጅም ጊዜ በዓይኖቻቸው ፊት የፍቅር ፊት ነበራቸው! አሁን ብቻ እንደዚህ ባለው ደስታ ፣ በታላቅ ደስታ ይገነዘባሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በዚህ ተሞክሮ አማካኝነት ኢየሱስ እነሱን እያነጻቸው ለበለጠ አስፈላጊ እርምጃ እያዘጋጃቸው ነው። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ በእውነቱ፣ በመስቀል ላይ ሲሰቀል እና ፊቱ ሲታወክ ያንኑ ውበት ማወቅ አለባቸው። ጴጥሮስ ለመረዳት እየታገለ፡ አንድ ጊዜ ቆም ብሎ ትዕይንቱን “ለአፍታ ይመለከት” ነበር፣ እዚያው ይቆይ እና ይህን አስደናቂ ተሞክሮ ለማራዘም ይፈልጋል። ኢየሱስ ግን አልፈቀደም። በእርግጥም ብርሃኑ ወደ “አስማታዊ ጊዜ” ሊቀንስ አይችልም! በዚህ መንገድ ሐሰት፣ ሰው ሰራሽ፣ ወደ ሚያልፈው ስሜት ጭጋግ የሚሟሟ ነገር ይሆናል። በተቃራኒው፣ ክርስቶስ በምድረ በዳ ላሉ ሰዎች እንደ እሳት ዓምድ መንገዳችንን የሚመራ ብርሃን ነው (ዘፀ 13፡21)። የኢየሱስ ውበት ደቀ መዛሙርቱን ከህይወት እውነታ አያርቃቸውም፣ ነገር ግን እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ እስከ መስቀል ድረስ እንዲከተሉት ጥንካሬን ይሰጣቸዋል። የክርስቶስ ውበት ከእርሱ አልተለየም። ሁሌም ወደፊት ያመጣሃል። እንድትደበቅ አያደርግም። ወደፊት ሂድ ይልሃል!
ወንድሞች እና እህቶች፣ ይህ ወንጌል ለእኛም መንገድ ዱካ ይሆንልናል። የሚናገረውንና የሚያደርገውን ሁሉ ለመረዳት ቀላል በማይሆንበት ጊዜም እንኳ ከኢየሱስ ጋር መኖር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምረናል። እንደውም ከርሱ ጋር በመቆየታችን ነው የመስቀል ምልክት ሲሸከምም የሚሰጠንን የፍቅር ውበት በፊቱ ላይ ለይተን ማወቅ የምንችለው። እናም በየቀኑ ከጎናችን በሚሄዱ ሰዎች ፊት ላይ አንድ አይነት ውበት ማየት የምንማረው በእሱ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው - ቤተሰብ ፣ ጓደኞች ፣ የስራ ባልደረቦች በጣም በተለያዩ መንገዶች ይንከባከቡን ይሆናል። ስንት ብሩህ ፊት፣ ስንት ፈገግታ፣ ስንት መጨማደድ፣ ስንት እንባ እና ጠባሳ በዙሪያችን ያለውን ፍቅር ይገልጣል! እነሱን ለማወቅ እና ልባችንን በእነሱ መሙላትን እንማር። ከዚያም የተቀበልነውን ብርሃን ለሌሎች ለማድረስ እንነሳ፣ በተጨባጭ የፍቅር ተግባራት (1ዮሐ. 3፡18)፣ ወደ ዕለታዊ ሥራችን የበለጠ በልግስና በመግባት፣ በመውደድ፣ በማገልገል እና በይቅርታ የበለጠ ትጋት እና ፍላጎት ማዳበር ይኖርብናል። የእግዚአብሔርን ድንቆች ማሰላሰል፣ የእግዚአብሔርን ፊት፣ የጌታን ፊት ማሰላሰል፣ ወደ ሌሎች አገልግሎት ሊያንቀሳቅሰን ይገባል።
እራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡ የእግዚአብሔርን ፍቅር ብርሃን በህይወታችን እንዳለ እንዴት ማወቅ እንችላለን? በሚወዱን ሰዎች ፊት ላይ በደስታ እና በአመስጋኝነት እናውቀዋለን? ልባችንን የሚሞላውን እና ለፍቅር እና ለአገልግሎት የሚከፍተውን የዚህ ብርሃን ምልክቶችን በዙሪያችን እንመለከታለን? ወይስ እኛን የሚያራርቁን እና በራሳችን ላይ የሚዘጋብንን የጣዖት የትቢያ እሳት እንመርጣለን? ታላቁ የጌታ ብርሃን እና ሐሰተኛው፣ ሰው ሰራሽ የጣዖት ብርሃን። የቱን እመርጣለሁ? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ የገባናል።
በሁለተኛ ደረጃ በእዚህ በሁለተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማቴ 17፡1-9) የኢየሱስ መልክ በቅጽበት መቀየርን የሚገልጽ ነው። ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ጴጥሮስን ፣ ያዕቆብን እና ዮሐንስን ይዞ እግዚአብሔር ቅርባችን እንደ ሆነ መገለጫ ወደ ሆነው ወደ እንድ ከፍ ያለ ተራራ ላይ የወጣ ሲሆን የእርሱን ስቃይ፣ ሞት እና ከሙታን መነሳት ምስጢር ደቀመዛሙርቱ ሙሉ በሙሉ መረዳት ይችሉ ዘንድ አስቦ ያደርገው ተግባር ነው። በእርግጥ ኢየሱስ እሱን ስለሚጠብቀው ስቃይ፣ ሞት እና ትንሣኤ ለእነርሱ ይነግራቸው ጀመር፣ ነገር ግን ያንን ተስፋ ሊቀበሉ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ወደ ተራራው አናት ላይ ሲደርስ በሦስቱ ደቀመዛሙርቶቹ ፊት በጸሎት መትጋት በጀመረበት ወቅት የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን መልኩን ተለውጦ “ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባራቂ ሆነ” (ማቴ 17;2)።
በእዚህ ተአምራዊ እና አስደናቂ የኢየሱስ ፊት የተቀየረበት ሁኔታ ሦስቱ ደቀመዛሙርት አንጸባራቂ ክብር ባለው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ ተጠርተዋል። ስለሆነም የሰው ልጅ አጠቃላይ ሁኔታ ገጽታውን ተገቢ በሆነ መልኩ እንደማይገልፅ በመገንዘብ ስለጌታቸው ያላቸው እውቀት ለየት ባለ ሁኔታ በእነሱ ፊት የኢየሱስ ሕይወት እና መለኮታዊ ገጽታ ተገለጠ። እናም “ከሰማይ የምወደው ልጄ ይህ ነው […] እሱን ስሙት”(ማቴ 17; 5) የሚል ድምጽ ተሰማ። በእዚህ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ነበር ሰማያዊው አባቱ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ቀን ደቀመዛሙርቱ እርሱን እንዲያዳምጡ እና እንዲከተሉት ስለእርሱ የመሰከረው እና እነርሱን የጋበዘው በእዚህ መልኩ ነው።
ከአሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ውስጥ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መርጦ ወደ ተራራ የወጣበት አጋጣሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ስለ ኢየሱስ ተአምራዊ የሆነው መልክ መለወጥ የመመሥከር ልዩ መብት ሰጣቸው። ነገር ግን ለምንድነው እነዚህን ሦስቱን ደቀመዛሙርት ብቻ የመረጠው? ለምንድነው እጅግ ቅዱስ ስለሆኑ ነው? በፍጹም! ጴጥሮስ ኢየሱስ ሞት በተፈረደበት ወቅት ይክደዋል፣ ሁለቱ ወንድማማቾች ያዕቆብ እና ዮሐንስ በመንግሥቱ የመጀመሪያ ስፍራ እንዲሰጣቸው ተተይቁዋል (ማቴ 20፡ 20-23)። ሆኖም ኢየሱስ እንደኛ መስፈርት አይደለም ምርጫውን የሚያካሂደው፣ ነገር ግን በእርሱ የፍቅር እቅድ መሰረት ነው። የኢየሱስ ፍቅር ምንም ልኬት የለውም ፣ ፍቅር ነው ፣ እናም በእዚያ ፍቅር እቅድ ይመርጣል። ነፃ ፣ ቅድመ-ሁኔታ የሌለው፣ በነፃ ተነሳሽነት፣ በምላሹ ምንም ነገር የማይጠይቅ መለኮታዊ ፍቅር ነው። እናም እነዚያን ሦስቱን ደቀመዛሙርት እንደጠራ ፣ በተመሳሳይም ዛሬ ስለእርሱ እንዲመሰክሩ የተወሰኑ ሰዎችን ወደ እርሱ ይጠራል። የኢየሱስ ምስክር መሆን የማይገባን ስጦታ ነው፣ እኛ ብቁ እንዳልሆንን ይሰማናል፣ ነገር ግን በእዚህ ስሜት ተገፋፍተን አቅም የለንም በሚል ሰበብ ወደ ኋላ መመለስ አይገባንም።
እኛ ወደ ታቦር ተራራ አልሄድንም፣ እንደ ፀሐይ የሚያብራውን የኢየሱስ ፊት በዐይናችን አላየንም። ሆኖም ፣ የመዳን ቃል ለእኛም ተሰጥቷል ፣ እምነትም ተሰጥቶናል፣ እናም እኛ በተለያዩ መንገዶች ከኢየሱስ ጋር የመገናኘት ደስታ አግኝተናል። እኛንም ቢሆን ኢየሱስ “ተነሡ አትፍሩ” (ማቴ 17፡7) ይለናል። በራስ ወዳድነት እና በስግብግብነት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ብርሃን በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ይበልጡኑ ያበራል። እኛ ብዙውን ጊዜ - ለመጸለይ ጊዜ የለኝም ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት ለማከናወን ፣ ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አልችልም… እንላለን። ነገር ግን የተቀበልነው ጥምቀት እና ማረጋገጫ እኛ በተቻለን አቅም ምስክርነት መስጠት እንደ ሚገባን መርሳት የለብንም። ነገር ግን ይህንን የምናደርገው በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ታግዘን ነው።
በእዚህ በዐብይ ጾም ወቅት ራሳችንን ተገዢ ለማደርግ እና በለውጥ ጎዳና ላይ ለመጓዝ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መቀበል እንችል ዘንድ በአማላጅነቷ እንድትረዳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልንማጸናት ይገባል።
የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት) ቫቲካን