በሊባኖስ በእሥራኤል ድብደባ የደረሰ አደጋ በሊባኖስ በእሥራኤል ድብደባ የደረሰ አደጋ 

የማልታ ሉዓላዊ ማህበር በሊባኖስ ለተከሰተው የመፈናቀል ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ጥረት አደረገ ነው

እስራኤላውያን በሊባኖስ ላይ እያደረሱት ባለው ጥቃት ምክንያት ከ500,000 በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ቀድሞውንም ከባድ የነበረውን ሰብዓዊ ቀውስ ይበልጥ እንዳባባሰው ተገልጿል። በሊባኖስ የማልታ ሉዓላዊ ማህበር ሥር የሚተዳደሩ አንዳንድ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማዕከላት ከባድ ጥርጣሬ እና ጭንቀት ውስጥ የገቡ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች የህክምና እንክብካቤን፣ የመጠለያ እርዳታ እና የስነ-ልቦና ድጋፍን ለመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተነግሯል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤላውያን እና አሜሪካ በኢራን ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እንዲሁም የኢራን ሃይሎች የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተጠናከሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ በሚንቀሳቀሰው የሄዝቦላህ ታጣቂ ቡድን ላይ ጦርነቱ ከተጀመረ የመጀመሪያዎቹ ስምንት ቀናት ውስጥ ባደረገችው ጥቃት 300 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸው እና 1000 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው እንዲሁም ከ500,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸው ተገልጿል።

ህዝቡን ለመደገፍ ከሚሰሩ ግብረሰናይ ኤጀንሲዎች መካከል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሃዋሪያዊ ጉባኤ የሆነው ማልታ ሉዓላዊ ማህበር አንዱ ሲሆን፥ በሊባኖስ የማህበሩ የልማት እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኦማይማ ፋራህ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ማህበሩ ከሚያግዛቸው ሰዎች መካከል በግጭቱ ምክንያት ስጋት እና ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ፣ ብሎም በዚህ መከራ ውስጥ የማለፍ ጥርጣሬ ውስጥ የገቡ ሰዎችን እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው በሚገኙበት ሁኔታ ላይ አሁን በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት የእርዳታ ሰራተኞች ብርቱ ትግል እያደረጉ መሆናቸውንም ጭምር ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

“ዛሬ ሊባኖስ በአስቸጋሪው ጦርነት ምክንያት በድጋሚ ከፍተኛ የመፈናቀል ቀውስ ውስጥ ገብታለች” ያሉት ወይዘሮ ፋራህ፥ አሁን ያለው ሁኔታ እ.አ.አ. በ 2024 ከተፈጠረው ግጭት በኋላ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተከሰተ መሆኑን ጠቁመው፥ ባለፈው ሐሙስ አመሻሽ ላይ ነዋሪዎች በደቡባዊ ሊባኖስ ከሚገኙት መንደሮች በተጨማሪ የቤይሩት ደቡባዊ ከተማ ዳርቻዎችን ለቀው እንዲወጡ ጥሪ መደረጉን ተከትሎ ሁኔታው ​​በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን አመላክተዋል።

“አንድ ወይም ሁለት ሰፈሮችን ብቻ ሳይሆን ህዝቡ አካባቢውን በአጠቃላይ ለቆ እንዲወጣ ጥሪ ሲደረግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” በማለት ስጋታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ፥ በዚህም ምክንያት ወደ 500,000 የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቁመው፥ በርካቶቹ ወዴት መሄድ እንዳለባቸው ባለማወቃቸው በድንገት ጎዳና ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል።  

ትርምስ እና ፍርሃት

ወይዘሮ ፋራህ ቤተሰቦች የቦምብ ጥቃትን ለመሸሽ በሚያደርጉት ጥረት የሚፈጠረውን ትርምስ ማየታቸውን እና ጥቃቱ በሚጀመርበት ወቅት መንገዶቹ ለበርካታ ሰዓታት እንደሚዘጉ በመጥቀስ ‘በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ በጣም አስደንጋጭ ነው’ ያሉ ሲሆን፥ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ በርካታ ቤተሰቦች አሁንም ድረስ በመኪናዎቻቸው ውስጥ እንደሚተኙ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎች በቀደሙት ግጭቶች ወቅት ባጋጠሟቸው አስቸጋሪ ተሞክሮዎች ምክንያት ወደ መጠለያ ለመግባት ፈቃደኞች እንዳልሆኑ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ጥገኝነት የጠየቁ በርካታ ሰዎች ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ነበሩበት መጠለያዎች መመለሳቸውን አስረድተዋል።

የችግሩ ተደጋጋሚነት በአከባቢው ላይ ለሚሰሩ የሰብአዊነት ቡድኖች ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን የገለጹት ፋራህ፥ ከሁለት ዓመት በፊት የተፈናቀሉትን እና ዛሬ በድጋሚ የተፈናቀሉትን ተመሳሳይ ፊቶችን፣ ተመሳሳይ ቤተሰቦችን እና ተመሳሳይ ህፃናትን ማየት ልብን የሚያሞቅ፥በተመሳሳይ ሁኔታ ልብን የሚሰብር ነገር መሆኑን ገልጸዋል።

“ይህ ሁኔታ በድጋሚ ለምን ተከሰተ?”

“በህዝቡ ላይ የሚደርሰው ስሜታዊ ጉዳት በግልጽ ይታያል” ያሉት ፋራህ፥ የአከባቢው ህዝብ በርካታ ጥያቄዎች፣ ሃዘኖች እና ቁጣ እንዳለው ጠቁመው፥ ህዝቡ ዘወትር ‘ይህ ሁኔታ በድጋሚ ለምን ተከሰተ?’ የሚል ጥያቄ እንደሚጠይቅ በማስታወስ፥ “ሊባኖሳዊያን​​ይህን ያህል ስቃይ እና በደል አይገባቸውም” ብለዋል።

የማልታ ሉዓላዊ ማህበር አገልግሎት በሊባኖስ

እ.አ.አ. በ 2024 ዓ.ም. በአከባቢው በተከሰተው ግጭት ወቅት በሊባኖስ የሚገኘው የማልታ ሉዓላዊ ማህበር በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 80 መጠለያዎች ውስጥ በርካታ የሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፥ አሁን በድጋሚ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በአከባቢው የሚገኙ ቡድኖቹ እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት በድጋሚ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተነግሯል።

“መጠለያዎቹ በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በህዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተመደቡልን እንደመሆናቸው መጠን ሰራተኞቻችንን እና ቡድኖቻችንን እንደገና በማሰማራት ላይ እንገኛለን” ያሉት ፋራህ፥ ከድርጅቱ ጥንካሬዎች መካከል አንዱ በመላ ሀገሪቱ በተቋቋመባቸው ስፍራዎች ላይ መገኘት መቻሉ እንደሆነ ጠቁመው፥ በአሁኑ ወቅት ተቋማቸው ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ፣ እንዲሁም በበካ እና በቤሩት አቅራቢያ በአጠቃላይ በሊባኖስ ዙሪያ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ወይዘሮ ፋራህ ከዚህም ባሻገር ወደ 60 የሚጠጉ የተቋሙ ፕሮጀክቶች እና ፕሮግራሞች ለዚህ ትልቅ ቀውስ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጠንካራ መሰረት እንደሚሆናቸው ገልጸው፥ ተቋማቸው በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ የማህበረሰብ ጤና ማዕከላት እና ተንቀሳቃሽ የህክምና ክፍሎች በመደበኛነት በድንበር አቅራቢያ ያሉ አካባቢዎችን ጨምሮ ወደ 40 ለሚጠጉ መንደሮች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውሰው፥ ነገር ግን እየተካሄደ ያለው የቦምብ ጥቃት እና ውድመት ቡድኖቻቸው ሥራቸውን ለማቋረጥ እንዳስገደዳቸው አሳስበዋል።

ከፍላጎቶች ጋር መላመድ

“በአሁኑ ወቅት ተደራሽ ባልሆኑ መንደሮች ወይም የተፈናቀሉ ሰዎች ወደሚሰባሰቡባቸው አካባቢዎች ሰራተኞችን እንደገና ማሰማራት አለብን” ያሉት ወይዘሮ ፋራህ፥ በፍላጎቶች መሰረት ያለማቋረጥ መላመድ እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ ምንም እንኳን ተግዳሮቶች ቢኖሩትም የሰራተኞች እና የበጎ ፈቃደኞች ቁርጠኝነት መኖሩን ጎላ አድርገው በመግለጽ፥ ቡድኖቻቸው በሊባኖስ የሚገኘው የማልታ ሉዓላዊ ማህበር ድሆችን እና ህሙማንን ለማገልገል እንዲሁም እምነት ለመጠበቅ ላለው ተልዕኮ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስምረውበታል።

“ጠንክረን የምንንጓዝበት፣ በተልዕኳችን አምነን የምንቀጥልበት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ለመጡት ፍላጎቶች ምላሽ የምንሰጥበት ጊዜ አሁን ነው” ያሉት ፋራህ፥ በአሁኑ ወቅት በሊባኖስ ወደ 500,000 የሚጠጉ ዜጎች ‘የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች’ ተብለው መመዝገባቸውን፥ ነገር ግን ያልተመዘገቡ በርካቶች መኖራቸውን ጠቁመው፥ ከእነዚህም ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ወደ 117,000 የሚጠጉ ሰዎች በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፥ ሌሎች ደግሞ የአከባቢው ባለ ሥልጣናት ደህንነታቸው የተጠበቀ አካባቢዎች መሆናቸውን ባረጋገጡባቸው ስፍራዎች ወይም ከዘመዶቻቸው እና ጓደኞቻቸው ጋር መጠለላቸውን አስረድተዋል።

የጤና እንክብካቤ

ወይዘሮ ፋራህ እንደተናገሩት በተፈናቀሉ ማህበረሰቦች ዘንድ ያለው ፍላጎት ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህም ምክንያት የሰብአዊ ቡድኖች የህክምና ምክር አገልግሎትን፣ በተለይም ሥር የሰደደ ሕመም ላለባቸው ታካሚዎች አስፈላጊ መድሃኒቶችን፣ እንዲሁም የአእምሮ ጤና እና የስነ-ልቦና ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ተቋማቸው የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን፣ የህፃናት የስነ-ልቦና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እና የክረምት አልባሳትን እያሰራጨ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ህፃናት በዚህ ቀውስ በጣም ከተጎዱት መካከል አንዱ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ምግብ እና መጠለያ

ድርጅቱ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ለሚታገሉ ቤተሰቦች ትኩስ ምግቦችን እና የተለያዩ የምግብ እሽጎችን በማቅረብ ረገድ ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፥ በርካታ ማረፊያዎች ወደ ጊዜያዊ መጠለያነት የተለወጡ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ገልጸው፥ እያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ቢያንስ ከ10 እስከ 12 የሚሆኑ ሰዎች ወለሉ ላይ እንደሚተኙ እና ቤተሰቦች መታጠቢያ ቤቶችን እና የማብሰያ ቦታዎችን ስለሚጋሩ የንፅህና አጠባበቅ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።

እርግጠኛ አለመሆን

ለበርካታ ሊባኖሳዊያን ​ትልቁ ተግዳሮት እርግጠኛ ያለመሆን ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ፋራህ፥ ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ መሆኑን እና በጣም አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ ሰዎች የግጭቱን መጨረሻ ማየት አለመቻላቸው እንደሆነ ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት በተፈናቀሉ ቤተሰቦች እና እነሱን በሚያስተናግዱ ማህበረሰቦች ላይ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ እና ቁጣ መፍጠሩን በማመላከት አጠቃለዋል።

 

11 Mar 2026, 15:58