የደቡቡ ዓለም ብጹዓን ጳጳሳት ፍትሃዊ የኃይል ሽግግር ለማፋጠን ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከአፍሪካ፣ ከእስያ እና ከላቲን አሜሪካ የመጡ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፥ መንግሥታት የቅሪተ አካል ነዳጅ እድገትን ለማስቆም እና ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረገውን ፍትሃዊ ሽግግር ለመምራት ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲያፀድቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ጥሪው የደቡቡን ዓለም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሚወክሉ አህጉራዊ ብጹዓን ጳጳሳት በአውሮፓ እና በኦሽንያ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር በመተባበር ባዘጋጁት “የደቡቡ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት የጋራ መኖሪያ ምድራችን” በሚለው ማኒፌስቶ ውስጥ መካተቱ ታውቋል።
“LiCAS” ለተሰኘ የዜና አገልግሎት በተላከው ሠነድ ላይ እንደተገለጸው፥ ብጹዓን ጳጳሳቱ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ እና በእስያ ያሉ ማኅበረሰቦች የአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ ያልሆኑ የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ውጤቶች እያጋጠሟቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጡ የአካባቢ ቀውስ ማስከተል ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የምርት እና የፍጆታ ዘይቤዎችን የሚገድል የኢኮኖሚ ውጤት መሆኑን ማኒፌስቶው ገልጾ፥ ይህም ሰብዓዊ ክብርን እና ሰላምን አደጋ ላይ በመጣል ሰፊ ቀውስ እንደሚፈጥር አስታውቋል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ የዓለም ሙቀት መጨመርን ከቅሪተ አካል ነዳጆች ቀጣይነት ጋር የሚያገናኘውን ሳይንሳዊ ማስረጃ ጠቁመው፥ ሠነዱ የድንጋይ ከሰል፣ የዘይት እና የጋዝ መቃጠል በቅርቡ ለሚከሰት ውድቀት ዋና ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮን መሠረት በማድረግ ባቀረቡት ጥሪ፥ መንግሥታት ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን ከጉዳት እያዳኑ የቅሪተ አካል ነዳጆችን ለማስወገድ አስገዳጅ ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ እንዲቀበሉ አሳስበዋል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ ለድሆች በሚሰጠው ምርጫ እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ውስጥ በተገለጸው የፍጥረት እንክብካቤ በመመራት ለፍትሃዊ ሽግግር የማያቋርጥ ድጋፍ እንዳላቸው አስታውቀው፥ መንግሥታት የቅሪተ አካል ነዳጅ መስፋፋት ለመግታት የሚያግዝ አሳሪ የሥነ-ምግባር እና የፖለቲካ ግዴታን እንዲወጡ የሚያስገድድ ስምምነት እንዲያፀድቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ማኒፌስቶው የፓሪስን ስምምነት የሚያሟላ የቅሪተ አካል ነዳጅ ስምምነት የሚያቀርብ ሲሆን፥ ይህም የቅሪተ አካል ነዳጅ ምርትን በቀጥታ በማስቀረት የፓሪስን ስምምነት ተፈጻሚ እንደሚያደርግ ታውቋል። በተጨማሪም አዲስ የድንጋይ ከሰል፣ የነዳጅ እና የጋዝ ፍለጋ እና ምርት እንዲቆም፣ አሁን ያሉትን የቅሪተ አካል ነዳጅ ሥራዎችን እንዲያስወግድ እና ሠራተኞችን እና ማህበረሰቦችን የሚጠብቅ ዓለም አቀፍ ፍትሃዊ ሽግግር እንዲኖር ይጠይቃል።
የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የቅሪተ አካል ነዳጅ መስፋፋት ጂኦፖለቲካዊ ውጥረትን እንደሚያባብስ አስጠንቅቀው፥ ኃይለኛ የነዳጅ እና የጋዝ መስፋፋትን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች ለግጭት እና ለፔትሮ-ኢምፔሪያሊዝም ዓይነቶች አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
በፊሊፒንስ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በቅሪተ አካል ነዳጆች እና በግጭቶች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ያላትን ስጋት ገልጻለች። ካሪታስ ፊሊፒንስ የካቲት 4/2018 ዓ. ም. ባወጣው ሐዋርያዊ መግለጫ በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ጦርነት እየጨመረ የመጣው ቀውስ ከዓለም አቀፍ የኢነርጂ ሥርዓት ጋር ለተያያዙ ጥልቅ መዋቅራዊ ችግሮች እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቋል።
የቤተ ክርስቲያኗ ማኅበራዊ ተግባር አካል የሆነው ይህ ድርጅት እንዳመለከተው፥ ግጭቱ የቅሪተ አካል የነዳጅ ኢኮኖሚ ጂኦፖሊቲካዊ ግጭትን ማባባሱን እንደ ቀጠለ ገልጾ፥ እንደ ሆርሙዝ ሰርጥ ያሉ ስትራቴጂያዊ የነዳጅ ሃይል መተላለፊያ ኮሪደሮች የወታደራዊ ኃይል፣ የኢኮኖሚ ጥቅም እና በነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆኑ የውድድር ቦታዎች ሆነዋል” ሲል ተናግሯል። ካሪታስ ፊሊፒንስ አክሎም “የነዳጅ ሃይል በጦርነት ሲጠመድ ውጤቶቹ በዓለም ዙሪያ በተለይም እንደ ፊሊፒንስ ላሉ ተጋላጭ ኢኮኖሚዎች ዘንድ ይስፋፋሉ” ሲል አስጠንቅቋል።
ቡድኑ አገሪቱ “ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ የድንጋይ ከሰል፣ ዘይት እና ጋዝ ላይ በአደገኛ ሁኔታ ጥገኛ ሆና ትቀጥላለች” ብሎ፥ ይህም አገራዊ መረጋጋትን ከቁጥጥራችን በላይ ከሆኑ ግጭቶች ጋር የሚያገናኝ እና ሕዝባችንን አስደንጋጭ ለሆነ ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ገበያ የሚያጋልጥ እና ጥገኛ የሚያደርጋት ነው” ሲል ተናግሯል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ ወደፊት የሚደረጉ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ድርድሮችን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ መንግሥታት የቅሪተ አካል የነዳጅ ምርት ቅነሳ ዕቅዶችን ከብሔራዊ የአየር ንብረት ግዴታዎች ጋር እንዲያዋህዱ እና ሥርዓታማ የኃይል ሽግግር ለማድረግ ዓለም አቀፍ ትብብርን እንዲደግፉ አሳስበዋል።
ማኒፌስቶው በመጨረሻም በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድነትና የጋራ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ በማቅረብ፥ ብጹዓን ጳጳሳቱ የምድሪቱን እና የድሆችን ጩኸት በማዳመጥ፣ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ የጋራ መኖሪያ ምድርን ከጥፋት ለመጠበቅ በሰሜን እና በደቡብ መካከል በሚደረገው ታሪካዊ ጥምረት ውስጥ እንዲሳተፉ ለመጋበዝ ዝግጁዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።