ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ የተላለፈ የኀዘን መግለጫ
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚፈጸመውን የዜጎች ግድያ እና ንብረት መውደም የተሰማትን ሀዘን እየገለጽን በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአርሲ ዞን በተደጋጋሚ በንፁኃን ላይ በተፈጸመው ኢሰብዓዊ ተግባር እጅግ አዝነናል።
ይህ ሆን ብሎ የንጹሃንን ሕይወት ማጥፋት በእግዚአብሔር ፊት ከባድ ኃጢአት እና በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠረ ለእያንዳንዱ ሰው የተሰጠውን ቅዱስ ክብር መጣስ ነው (ዘፍ 1:27)። እንዲህ ዓይነቱ መከላከያ በሌላቸው ንጹሃን ሰዎች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት ጥቃት በሃይማኖት፣ በጎሳ ወይም በፖለቲካዊ አቅም ልንከላከል አንችልም።
ቤተክርስቲያናችን ይህን አይነቱን ኢሰብዓዊ ተግባር አጥብቃ ታወግዛለች፥ በመሆኑም የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ መንግስት አስቀድሞ አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቤተክርስቲያናችን ጥሪዋን ታቀርባለች።
በተለይ በእነዚህ ጥቃቶች የሚወዷቸውን ሰዎች ላጡ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሀዘናችንን እየገለጽን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና በጎ ፍቃድ ካላቸው ሰዎች ሁሉ ጋር በመተባበር በንጹኃን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም አይነት ጥቃት ታወግዛለች።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥላቻን እንዲቃወሙ እና እነዚህን አሳዛኝ ክስተቶችን በመጠቀም በማህበረሰባችን መካከል ክፍፍል እንዲፈጠር ለማድረግ የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ እንዲቃወሙ እናሳስባለን። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስተምረው :-
“ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ 5፡9)።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በዚህ እጅግ አሳዛኝ ተግባር ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ዘለዓለማዊ እረፍትን ያገኙ ዘንድ እየጸለይን የተሰማንን ታላቅ ሀዘን እንገልጻለን።
ለተጎዱ ቤተሰቦች መጽናናትን፣ እና ለኢትዮጵያ ሃገራችን እንዲሁም ለመላው አለም ሰላምን እንዲያወርድልን በልዑል እግዚአብሔር አብ ስም እንጸልያለን።
ቸሩ መድኃኔዓለም ጾማችንን ባርኮ ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም ያድርሰን !
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት