የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ 

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት በጋሞ ዞን በተከሰተው አደጋ የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን በመጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ. ም. በተከሰተው አሰቃቂ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ ምክንያት የበርካታ ወገኖች ሕይወት በማለፉ እና ብዙ ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው በመፈናቀላቸው በእጅጉ ማዘናቸውን ገለጹ።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሶዶ ሀገረ ስብከት እና የጳጳሳት ጉባኤ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው ቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ማቅረብ መጀመሯን ገልጸዋል። ሆኖም ከአደጋው አስከፊነት አንጻር የመላው ኢትዮጵያውያን እና በጎ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ ለዚህም በፍጥነት እንዲረባረቡ ጠይቀዋል። “ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” (ሮሜ 12፥15) በማለት የሚያስተምረውን የእግዚአብሔር ቃል በማስታወስ “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከወገኖቻችን ጎን እንቁም!” ሲሉ አሳስበዋል።

በኢ. ፌ. ዴ. ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተገለጸው፥ “ለሦስት ቀናት በሚቆይ ብሔራዊ የሐዘን ጊዜ ከወገኖቻችን ጋር በመሆን፣ መስዋዕተ ቅዳሴን በማቅረብ እና ለተጎጂዎች የሚደረግ ሰብዓዊ ድጋፍ በፍጥነት እንዲዳረስ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና ለመላው ኢትዮጵያውያን የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡትን እግዚአብሔር አምላክ በምሕረቱ እንዲቀበላቸው፣ ዘለዓለማዊ እረፍትን እንዲሰጣቸው፣ ለተጎጂዎች ቤተሰቦችም እውነተኛ መጽናናትን እንዲሰጣቸው በመለመን እና እንዲሁም ቸሩ መድኃኔዓለም ኢትዮጵያን እንዲጠብቅ በጸሎት ጠይቋል።

16 Mar 2026, 16:47