የቅድስት ምድር ተንከባካቢ ማኅበር ስለ ሰላም የሚደረግ ጸሎት እንደማያቋርጥ አስታወቀ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ማኅበሩ በመግለጫው “በደህንነት ምክንያት በኢየሩሳሌም በሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ መካነ መቃብር ባዚሊካ ውስጥ መጸለይ ቢከለከልም በቅዱስ ሥፍራዎች የሚደረጉ ጸሎቶች፣ ክብረ በዓላት፣ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች እና የዕለት ተዕለት ዑደቶች በሙሉ ቀንም ሆነ ሌሊት አልተቋረጡም” ሲል አስታውቋል።
በጋራ ጸሎት ዓመፅን መቃወም
“የዓለም ቤዛ በተወለደበት ምድር ውስጥ ለዘመናት መገኘታችን እና በየቀኑ የሚቀርበው ጸሎት ለመላው ቤተ ክርስቲያን እና ለሰው ልጅ ጥቅም ነው” ሲል መግለጫው አክሏል።
“በተለይም አሁን እየኖርናቸው እና በጸሎት በመትጋት የምናሳልፋቸው አስደናቂ ጊዜያት የእያንዳንዱን ምዕመን እምነት፣ ተስፋ እና ጸሎት ለማሳየት የሚጥሩ በመሆናቸው በእነዚህ ቅዱስ ሥፍራዎች መካከል የሰላም እና የእርቅ ጸሎት ይቀጥላል” ሲል መግለጫው አስታውቋል።
“በሕማማት ሳምንት የሚቀርብ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ይኖራል ወይ?” ለሚለው ጥያቄ “እርግጠኛ ሆኖ በዚህ ጊዜ መናገር አይቻልም” ሲል የቅድስት ምድር ተንከባካቢ ፍራንችስኮስዊ ማኅበር ገልጿል።
ተንከባካቢ ማኅበሩ የኢየሱስ ክርስቶስ መካነ መቃብር ሥፍራ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት እና ኃላፊነት ካላቸው ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር የማያቋርጥ ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።
“ምዕመናን በሙሉ ጦርነት እና ዓመፅ እንዲቆም በጸሎት እንዲተባበሩ” ሲል የጋበዘው ማኅበሩ፥ በጸሎት መተባበር የውይይት፣ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ መፍትሄዎችን በድፍረት እና በኃላፊነት መፈለግ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሚያስችል ብቸኛው መንገድ እንደሆነ አስረድቷል።