ብፁዕ ካርዲናል ቲሞቲ ራድክሊፍ - የማህደር ምስል ብፁዕ ካርዲናል ቲሞቲ ራድክሊፍ - የማህደር ምስል   (AFP or licensors)

ብፁዕ ካርዲናል ራድክሊፍ ‘በጦርነት ጊዜ ክርስቲያኖች የተስፋ ሰዎች እንዲሆኑ ተጠርተዋል’ ማለታቸው ተነገረ

የዶሚኒካን ማህበር አባል የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ቲሞቲ ራድክሊፍ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ በዩክሬን ስላደረጉት ቀጣይነት ያለው ጉብኝት እንዲሁም የጸሎት አስፈላጊነት እና በግጭት ጊዜ ክርስቲያናዊ ተስፋን አስመልክቶ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብፁዕ ካርዲናል ቲሞቲ ራድክሊፍ በዩክሬን አካባቢ ለሚገኙ አቢያተ ክርስትያናት እንዲሁም ‘ኦርደር ኦፍ ፕሪቸርስ’ ተብሎ ለሚጠራው ጉባኤ ያላቸውን ድጋፍ እና አጋርነት ለመግለጽ በጦርነት የተመሰቃቀለውን ሃገር እየጎበኙ እንደሆነ ተነግሯል።

የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በዩክሬን ዋና ከተማው ኪየቭ የደረሱት ብፁዕ ካርዲናል ቲሞቲ በኪየቭ የዚቶሚር ሃገረ ስብከት ጳጳስ ከሆኑት ብፁዕ አቡነ ቪታሊ ጋር ተገናኝተው በጋራ በጦርነቱ ወቅት ለሞቱት ወታደሮች የተዘጋጀውን ጊዜያዊ መታሰቢያ የጎበኙ ሲሆን፥ በተጨማሪም ከየካቲት 21 እስከ 22 ድረስ የቆየውን ሱባኤ ሥነ ስርዓት በመምራት እና በመስበክ ከቆዩ በኋላ ቀሪውን ሁለት ሳምንታት በሚኖራቸው ቆይታ የዶሚኒካን ወንድሞቻቸውን በመጎብኘት እንደሚያሳልፉ ተነግሯል።

ብፁዕ ካርዲናል ቲሞቲ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የጉዟቸውን የመጀመሪያ ቀናት በማስታወስ በአከባቢው እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን ተስፋ የማጣት ስሜትን እና ስቃይን ለማሸነፍ ክርስቲያኖች እንዲጸልዩ እና ተስፋ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የጦርነት ቀጠናው ውስጥ ከሚገኙ ህዝቦች ጋር መገናኘት እና አብሮ መሆናቸው እጅግ ደስተኛ እንዳደረጋቸው የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ራድክሊፍ ከሰላሳ ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሃገሪቱን መጎብኘታቸውን አስታውሰው፥ አሁን የተደረገላቸውን ግብዣ በደስታ ተቀብለው ወደስፍራው መምጣታቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ዬትኛውንም መከራ የበዛበትን ሃገር ሲጎበኙ ሁሌም አንድ ነገር እንደሚማሩ ጠቅሰው፥ በዚህም ምክንያት ከምንም ነገር በላይ ከወንድሞቻቸው እና ከእህቶቻቸው ጋር ለመሆን እዚህ እንደመጡ፥ ከእነሱም በርካታ ነገር መማር እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ወደ ስፍራው ይዘው የመጡት ዋነኛው መልዕክት ካለ የተጠየቁት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ አንድ ሰው የሆነን ቦታ ሲጎበኝ ሁሌም አንድ የተዘጋጀ መልዕክት ይዞ ይመጣል ማለት እንዳልሆነ፥ ከዚህም ይልቅ ያለውን ችግር ለመስማትም ጭምር እንደሚመጣ ጠቁመው፥ አንድ ሰው ከመናገሩ በፊት መጀመሪያ ሰዎች የሚሉትን ነገር ማዳመጥ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህም በመሆኑ ምክንያት ለመስማት እንጂ ለመናገር እንዳልመጡ ገልጸው፥ ይህ ደግሞ የሲኖዶሳዊነት ማዕከል እንደሆነ እና ወደ ስፍራው የመጡት ለማዳመጥ ከሚመጡ ሰዎች ውስጥ አንደኛው በመሆን፥ እግዚአብሔርን ለመስማት፣ እንዲሁም እርስ በርሳችን ለመደማመጥ ነው ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ራድክሊፍ ኪየቭ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ የመሩት የሱባኤ መርሃ ግብር ‘አባታችን’ በሚል ጭብጥ የተመራ መሆኑን እና ይሄንን ጭብጥ ለምን እንደመረጡት ተጠይቀው፥ በመከራ እና በጦርነት ጊዜ ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ጠቁመው፥ በዚህም ምክንያት ‘አባታችን’ ከጸሎቶች ሁሉ የሚበልጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ጸሎት በመሆኑ ይሄንን ጭብጥ መመረጣቸውን አብራርተዋል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመከራዉን ጽዋ ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ እና በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ የሚመጣውን መከራ በማየት እንደጸለየ ያስታወሱት ካርዲናሉ፥ በዚህም ምክንያት እያንዳንዳችን፣ በተለይም መከራ ሲያጋጥመን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ጸሎት ታላቅ ስጦታ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጦርነቱ በአዲስ ምዕራፍ መጀመሩን፣ እንዲሁም በዩክሬን እና በቅድስት ምድር ኢየሩሳሌም ስላለው ሁኔታ ያላቸውን አስተያየት የተጠየቁት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ በዚህ ወቅት በብዙ ቦታዎች ጦርነት የሚካሄድበት ጊዜ በመሆኑ በእርግጥ በየቦታው ግፍ እየበዛ መምጣቱን ጠቁመው፥ በአውሮፓ ወይም በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ ሳይሆን ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ በአፍሪካ ሃገራትም ጭምር ግጭቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ይህም በመሆኑ ምክንያት ጦርነት የማይቀር ነገር ቢሆንም ሰላም ሊኖር እንደሚችል ከመቼውም ጊዜ በላይ ክርስቲያናዊ ምስክርነት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ካርዲናሉ፥ “በጦርነት ጊዜ የተስፋ ሰዎች እንድንሆን ተጠርተናል” ካሉ በኋላ፥ ዛሬ የክርስቲያኖች ዋና መልዕክት ተስፋ መሆኑን ጠቅሰው፥ የቅዱስ ቁርባን አምልኮአችን የተመሰረተው በመጨረሻው እራት ወቅት፣ ሞት እና ብጥብጥ ብቻ በነበሩበት እና ምንም ተስፋ ያልነበረ በሚመስልበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰው፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን የሰጠው ያኔ እንደነበር እና ይህ የእኛ ታላቁ የተስፋ ቁርባን መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ ስለዚህም ለዩክሬን ሕዝብ ወይም ጦርነት በተስፋፋበት አከባቢ ሁሉ የሚያስተላልፉት ብቸኛው መልዕክት ይህ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ተስፋችንን በጌታ ላይ ማድረግ እንደሚገባና ይህ ሲሆን በመጨረሻም ሰላም እንደሚሰፍን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ራድክሊፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተናገራቸው የመጨረሻዎቹ ሰባት ቃላቶች ላይ የሚያተኩር “ሰባቱ የመጨረሻ ቃላት” የሚል መፅሃፍህ በዩክሬንኛ ማሳተማቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ ይሄንን አስመልክተው ያላቸውን ሃሳብ እንዲያጋሩ የተጠየቁት ካርዲናሉ ይህ በይዘቱ አነስተኛ የሆነው መጽሐፍ እርስ በርስ ለመደማመጥ መማርን ከሚያስተምረው ከሲኖዶሳዊ ጭብጥ ጋር በቅርበት የተያያዘ መሆኑን ገልጸው፥ ግጭቶች በሚበዙበት ጊዜ ጆሮዎቻችንን ለመዝጋት ፈተናው ቢበዛም፥ ነገር ግን መስማት እንዳለብን አስታውሰዋል።

“ሰው እንደመሆናችን መጠን በማህበረሰባችን ውስጥ በተለይ የሃሳብ ልዩነት ሲኖረን እርስ በርሳችን እንደማመጣለን” ያሉት ካርዲናሉ፥ እርስ በርሳችን በትክክል መማማር የምንችለው የሃሳብ ልዩነት ሲኖር እንደሆነ ገልጸው፥ ዓለማችን ሰዎች በእውነት ለማሰብ ወይም ለሌሎች ራሳቸውን ግልጽ ለማድረግ በማይሞክሩባቸው መፈክሮች መሞላቷን በማመላከት፥ ከዚህ ይልቅ የእግዚአብሔር ጥሪ አእምሯችንን እና ልባችንን እንድንከፍት ይጋብዘናል ብለዋል።

በዚህ ምክንያት በጦርነት ጊዜ የሲኖዶሱ መንገድ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የጠቆሙት ካርዲናሉ፥ ጥር ወር ላይ በሮም በተካሄደው ጉባኤ ወቅት ሁሉም ካርዲናሎች አንድ ላይ ተሰባስበው እንደነበር አስታውሰው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የሚፈልጉት የመጀመሪያው ነገር ብፁዕነታቸው እኛን እንዲሰሙን ከተፈለገ መጀመሪያ እርስ በርሳችን መደማመጥ እንድንችል መሆኑን ገልጸው፥ ይህም በዓመፅ ለተሞላው ዓለም የቤተክርስቲያን ታላቅ ስጦታ መሆኑን ያመለከቱ ሲሆን፥ በጆሮአችን እና በአእምሯችን ብቻ ሳይሆን በምናባችንም መስማት እንዳለብን እና ሌሎች ለምን ከእኛ የተለየ እንደሚያስቡ መገመት እንችላለን ወይ? የሚለውን ጥያቄ ራሳችንን መጠየቅ ይገባል በማለት አጠቃለዋል።

04 Mar 2026, 13:51