እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ፍንዳታው ከተከሰተ በኋላ  የታየው ጭስ። እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ፍንዳታው ከተከሰተ በኋላ የታየው ጭስ። 

ካርዲናል ኩፒች ጦርነቱ ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት “የሕሊና ጥሪ” የሚል መግለጫ ማውጣታቸው ተገለጸ

የቺካጎ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች አስከፊው ጦርነት በየቦታው እየተስፋፋ በመጣበት እና እንደ ቪዲዮ ጨዋታ እየታየ ባለበት በአሁኑ ወቅት “የሕሊና ጥሪ” ያቀረቡ ሲሆን፥ ጦርነት የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ አይተን እንዳላየን ሆነን በቆየን ቁጥር “እግዚአብሔር የሰጠንን እጅግ ውድ ስጦታ የሆነውን ሰብአዊነታችንን እናጣለን” በማለት አስጠንቅቀዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቺካጎ ሊቀ ጳጳስ አሜሪካ ከኢራን ጋር ከጀመረችው ግጭት ጋር በተያያዘ በሰው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት አስመልክቶ “የሕሊና ጥሪ” በሚል ርዕስ ባወጡት መግለጫ ጦርነቱን በሚመለከት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እየታየ ስላለው “ትክክለኛ ያልሆነ” አካሄድ በመጥቀስ በቁጭት ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች በቅርቡ የተፈጸሙትን የቦምብ ጥቃቶች በመጥቀስ “ከ1,000 በላይ ኢራናውያን ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት ለቀናት በዩናይትድ ስቴትስ እና በእስራኤል በተፈጸሙ የሚሳኤል ጥቃቶች አማካይነት መሞታቸውን አስታውሰው፥ ከዚህም ባሻገር ይፋዊው የዋይት ሀውስ የኤክስ ገጽ ሐሙስ ምሽት “አሜሪካዊው የፍትህ መንገድ” በሚል ርዕስ በኢራን ላይ እያደረጉት ያለውን ጦርነት የሚያሳይ ቪዲዮ ከአንድ ታዋቂ ፊልም ላይ ከተወሰደ ትዕይንት ጋር በማቀናጀት የተሰራ ቪዲዮ መለጠፉን ጠቅሰው፥ “እውነተኛ ጦርነትን እና እውነተኛ ስቃይን” እንደ ቪዲዮ ጨዋታ ማየታቸው በጣም ያሳምማል” ብለዋል።

የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት በተጀመረበት ቀን ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸው መጥፎ አጋጣሚ የሆነባቸውን በርካታ ህፃናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ እናቶች እና አባቶች፣ ሴት ልጆች እና ወንዶች መሞታቸውን የጠቆሙት ካርዲናሉ፥ በሌላ በኩል 6 የአሜሪካ ወታደሮች መሞታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ በጦርነቱ ምክንያት የሞቱት ሰዎች በዚህ ማህበራዊ ሚዲያ ልጥፍ ምክንያት ሰብዓዊ ክብራቸው እንደተገፈፈ ጭምር የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች፥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ሌሎች በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች ደግሞ በፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በጦር ሜዳ እና በመኖሪያ ክፍል መካከል ያለው ርቀት

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በመግለጫቸው ግጭትን አስመልክቶ ህዝባዊ ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ሚና የጠቀሱ ሲሆን፥ “በጦር ሜዳ እና በመኖሪያ ክፍል መካከል ያለው ርቀት በእጅጉ መቀነሱን” አመላክተው፥ እየገጠመን ያለው የሞራል ቀውስ ከጦርነቱ በላይ መሆኑን፥ ከዚህም በተጨማሪ የጦርነቱ ታዛቢዎች ግጭትን እንደ አንድ የስፖርት ወይም የቪዲዮ ጨዋታ እንዲመለከት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ አክለውም በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኞች እንኳን ሳይቀሩ ጦርነቱን ሲገልጹ “ጨዋታ” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ እንደሚስተዋል ጠቁመው፥ ይህ “የእውነተኛ ሰዎችን ሰብዓዊነት የሚገፈፍ” የቃላት ምርጫ እንደሆነ አስረድተዋል።

እየተከሰተ ያለው ነገር “ጥልቅ የሞራል ውድቀትን” ያሳያል ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች፥ “አንድ መርሳት የሌለብን ነገር ‘መምታት ወይም ማጥቃት’ በተፋላሚ ወገን ላይ ነጥቦችን ማስቆጠር ሳይሆን፥ መዝናኛን እና ትርፍን ከሰው ልጆች ስቃይ ስናስቀድም ስቃዩን ችላ ያልነው እና ሀዘን ውስጥ የሚገኘውን ቤተሰብ ለከፍተኛ ጉዳት መዳረግ ነው በማለት ገልጸዋል።

ለጦርነት ጉዳቶች ስሜት ማጣት

የኢራንን ህዝብ ስቃይ ለአሜሪካ ህዝብ መዝናኛ እንደ መነሻ ነጥብ አድርጎ በሚመለከተው የአሜሪካ መንግስት አመለካከት ያላቸውን ሃዘን የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ “ይህ በሰራዊታችን አጥፊ ኃይል ስንደሰት ሰብአዊነታችንን እንድናጣ እና ፍንዳታዎችን ‘የመመልከት’ ሱስ ያሲዘናል” ያሉ ሲሆን፥ አክለውም ‘ለትክክለኛው የጦርነት ጉዳቶች ቸልተኛ ስንሆን የዚህ ልማድ ዋጋ እምብዛም ልብ የማንለው ጉዳይ ይሆናል’ ብለዋል።

“ጦርነት የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ እያወቅን እንዳላወቅን እየሆን በሄድን መጠን አምላክ የሰጠንን እጅግ ውድ ስጦታ ማለትም ሰብአዊነታችንን ለአደጋ እያጋለጥን እንሄዳለን” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በመጨረሻም፥ “የአሜሪካ ሕዝብ ከዚህ የተሻለ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ እየሆነ ያለው ነገር መዝናኛ ሳይሆን ጦርነት እንደሆነ እና ኢራን የህዝቦች ሀገር እንጂ ሌሎች እኛን ለማዝናናት የሚጫወቱት ‘የቪዲዮ ጌም’ እንዳልሆነ ማወቅ አለብን በማለት አጠቃለዋል።

 

10 Mar 2026, 07:39