ካርዲናል ፒዛባላ በጌተሰማኒ ባከበሩት የሆሳዕና በዓል ላይ ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት አደረጉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒዛባላ በእስራኤል ፖሊሶች ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ በመከልከላቸው በእየሩሳሌም በሚገኘው መንበረ ጸባዖት ቤተክርስቲያን የሆሳዕና በዓል መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረግ ባለመቻላቸው ምክንያት በጌቴሴማኒ በሚገኘው ባዚሊካ ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ በድህረ ገጽ አማካይነት በቀጥታ መሰራጨቱ ተነግሯል።
‘ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸለየበት በደብረ ዘይት ተራራ ሥር በሚገኘው በአትክልቱ ሥፍራ እኛ ልዩ የሆነ የእርቅና የተስፋ ጸሎት በማድረግ ቅዱሱን የህማማት ሳምንት እንጀምራለን’ ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ሥርዓተ ቅዳሴውን ካሳረጉ በኋላ ወደ እየሩሳሌም ከተማ በመዞር በቅዱስ መስቀሉ የከበረ ቡራኬ የሰጡ ሲሆን፥ በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት ምክንያት የዘንድሮው ክብረ በዓል በቅድስት ሀገር ያለ መንፈሳዊ ነጋዲያን እየተከበረ ቢሆንም፥ ነገር ግን የዓለም ማህበረሰብ ሰላም እንዲሰፍን በአንድነት ፀሎት በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጸው፥ አሁን ያለውን ጊዜ ለማመላከት በኢየሩሳሌም ያዘነውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ምስል አስታውሰዋል።
ዛሬም በድጋሚ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኢየሩሳሌም እንደሚያለቅስ የጠቆሙት ፓትሪያርኩ፥ “የተስፋና የሀዘን፣ የጸጋ እና የመከራ ምልክት ሆና ስለቀረችው ስለዚህች ከተማ ያለቅሳል” ያሉ ሲሆን፥ በማከልም አሁንም ድረስ የሰላም ስጦታን ማወቅ ስለተሳናት ስለዚህች ቅድስት ሀገር ያለቅሳል ብለዋል። ማለቂያ የሌለው የሚመስለው ጦርነት ሰለባ ለሆኑት ሁሉ፤ ለተከፋፈለ ቤተሰብ፣ ለተሰባበረ ተስፋ ያለቅሳል ያሉት ፓትሪያርኩ፥ የኢየሱስ እንባ ግን ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር እና ዓይኖቻችንን እንደሚከፍቱ፣ እንደሚሟገቱልን እና እውነቱን እንደሚገልጡ ገልጸዋል።
ልማዳዊው የሆሳዕና በዓል በጦርነቱ ምክንያት እንደበፊቱ በመንፈሳዊ ጉዞ እና የዘንባባ ዝንጣፊን በመያዝ አለመከበሩን በመጥቀስ፥ ጦርነቱ የተለመዱ የእምነት መገለጫዎችን ቢያስተጓጉልም እውነተኛ እምነት ግን በውጫዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ላይ የተመካ እንዳልሆነ እና በዝምታ እና በችግር ውስጥም ቢሆን በህይወት ሊኖር እንደሚችል አስረድተዋል።
“የተሰቀለው እና ከሙታን ተለይቶ የተነሳው ዛሬም በመካከላችን መሄዱን እንደማያቋርጥ እርግጠኞች ነን” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ መንገዱ በተዘጋ ጊዜ እንኳን እርሱን መከተል ባላቆሙት ሰዎች ልብ ውስጥ ዘወትር እንደሚኖር ገልጸው፥ ከዚህም ባሻገር አሁን ባለንበት ሁኔታ የሚደረግ ማንኛውም ሥርዓተ አምልኮ ይበልጥ ትክክለኛ እንደሚሆን የገለጹ ሲሆን፥ "የሆሣዕና" ጩኸት ወደ ሰማይ ለመውጣት ቅርንጫፎች እንደማይስፈልጉት እና ውጫዊ ስርዓቶች ቢወገዱም እምነት ግን ጸንቶ እንደሚቆይ አስረድተዋል።
ፓትሪያርክ ፒዛባላ በክህደት፣ በሃሰት እና በዓመፅ አማካይነት የሰው ልጅ ውድቀትን የሚያሳየውን የሕማማት ወንጌልን በማስታወስ፥ ይህ ድርጊት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይናወጥ ታማኝነት እና ራስን የመስጠት ፍቅርንም ያሳያል ያሉ ሲሆን፥ ሞት የሚያሸንፍ በሚመስልበት ቅጽበት እውነት እና ፍቅር እንደተገለጠ እንዲሁም ድህነት እንደተፈጸመ ተናግረዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው ሰላም ‘ራሱን ሙሉ በሙሉ ከሰጠ፣ ኃይልም ሆነ ጦር ከማያስፈልገው ከእግዚአብሔር የሚመጣ ሰላም’ እንደሆነ አስረድተው፥ “እሱ የሚሰጠን ሰላም ወደ መስቀሉ ፍሬዎች እንጂ ቅዠት ወደሚመስለው ሰላም አይመራንም” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ፓትሪያርኩ የትንሳኤው ቦታ የቀራኒዮ ስፍራም እንደሆነ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር የተገለጠበት ቦታ አሁንም ድረስ ከመጠን በላይ በጥላቻ መሞላቱን በማስታወስ፥ እዚህ ላይ እምነትን መኖር ማለት በውስጡ የያዘውን ተቃርኖ መቀበል ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒዛባላ በመጨረሻም ሁሉም ሰው የእግዚአብሔር ፍቅር ምስክሮች እንዲሆኑ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ እንዲሰጡ በማበረታታት፥ “ወንድሞች እና እህቶች በዚህች ምድር ሰላምን በመጠባበቅ ላይ ያለን ፍቅር ተስፋ የማይቆርጡ ምስክሮች እንድንሆን ተጠርተናል” ካሉ በኋላ፥ የእምነት ጉዞአችን ዛሬም የተስፋ ጉዞ እንዲሆን፥ ብሎም ህይወታችን አሁን ባለው ጭካኔ የተሞላበት ዓለም ውስጥ እንኳን ጨለማ የበረታ በሚመስልበት ቦታ ሁሉ የክርስቶስን ፍቅር እና ብርሃኑን እንዲያመጣ እንጸልያለን በማለት አጠቃለዋል።