ፈልግ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሞናኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሞናኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት  

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በሞናኮ የሚያደርጉት ጉብኝት የተደበቁ የድህነት ዓይነቶችን ለማወቅ ይረዳል ተባለ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሞናኮ ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ብሎ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዶሚኒክ-ማሪ ዴቪድ የአገሪቱን ሁኔታ በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዶሚኒክ-ማሪ ዴቪድ የትንሿ አገራቸውን መንፈሳዊ ድክመቶችን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ ሃብት ብዙውን ጊዜ ጥልቅ ብቸኝነትን እና የሕይወት ትርጉም ማጣት ቀውስን ሊደብቅ እንደሚችል ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሞናኮ የሚያደርጉትን የአንድ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት ቅዳሜ መጋቢት 19/2018 ዓ. ም. ጠዋት እንደሚጀምሩ ታውቋል።

የሞናኮ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዶሚኒክ-ማሪ ዴቪድ በፈረንሳይ ውስጥ የምትገኝ እና ከበርካታ ጎብኚዎች በምታገኘው ሃብት የበለጸገች ትንሿን የአውሮፓ አገር በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ይህ ሃብቷ ብቸኝነቷን እና ጭንቀቷን እንደሚደብቅባት ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዴቪድ ከዜና አገልግሎቱ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በቅንጦት ከተማ ውስጥ ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ተልዕኮ ግንዛቤያቸውን አቅርበዋል።

አቡነ ዴቪድ ከስድስት ዓመታት በፊት የትንሿ ግዛት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲመጡ እጅግ በጣም የተለያዩ እውነታዎች አብረው መኖራቸው እንደተመለከቱት ገልጸው፥ በሞናኮ ውስጥ ወደ 150 የሚጠጉ አገራት ዜጎች መኖራቸውን ተናግረው፥ “ብዙውን ጊዜ የቅንጦት ከተማ ብቻ ተደርጋ ብትወሰድም እንደ እውነቱ ከሆነ ሃብቷ ከተለያዩ መነሻዎች እና ከተወሰነ ማኅበራዊ ውህደቶች የተገኘ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ብዙ ሰዎች እዚያው ባይኖሩም ወደ ሞናኮ እየመጡ እንደሚሠሩ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ፥ ይህም ለአገራቸው እና ለቤተ ክርስቲያናቸው ሃብት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚህች ትንሽ አገር የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመላው ዓለም መልዕክት የሚያስተላልፉበት በመሆኑ አስፈላጊ ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል አስረድተዋል።

“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ተልዕኮው ወንጌልን ወደ ሥፍራው ማምጣት፣ እምነትን ማጠናከር፣ ሰላምን እና ሰብዓዊ ክብርን የሚመለከት መልዕክት ማሰራጨት ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ፥ “በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከትንሿ አገራችን ድንበር አልፎ ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ጭምር ይደርሳል” ብለዋል።

“የድህነት ዓይነት በርካታ እና እጅግ ጥልቅ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ፥ በከፊል በመገናኛ ብዙኃን ከሚሰራጩት የተዛቡ አመለካከቶች እና ምስሎች ባሻገር በቅርብ ዓመታት ውስጥ ስለ ሞናኮ ማኅበረሰብ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸው፥ እውነታውን ለማወቅ ያገዟቸውን ሰዎች አመስግነዋል።

አንዳንድ ጊዜ የተደበቀ እና ለማየት የሚያስቸግር ቁሳዊ ድህነት መኖሩን የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ፥በከተማዋ ዙሪያ ሥራ ያላቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸውን እና ይህም ለአገሪቱ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረው፥ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እራሳቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚያገኙ በተለይም የመኖሪያ ቤት እጥረት ወይም የኑሮ ውድነት እንደሚያጋጥማቸው ገልጸው፥ ሀገረ ስብከታቸውን ጨምሮ ብዙ ማኅበራት ለእነዚህ ሁኔታዎች ትኩረት እንደሚሰጡ አስረድተው፥ ከእነዚህ ቁሳዊ ችግሮች ጎን ለጎን ሌሎች የድህነት ዓይነቶች፣ ብቸኝነት እና የሕይወት ትርጉም ማጣት ችግር እንዳለም ጠቅሰዋል።

አንድ ሰው ከፍተኛ ቁሳዊ ጭንቀት ከሌለው ሌሎች ጥያቄዎች እንደሚነሱ ተናግረው፥ በብቸኝነት የሚሰቃዩ ሰዎችን ማግኘት አዲስ እንዳልሆነ፥ በልጆቻቸው አስተዳደግ እና በቤተሰብ መለያየት ግራ የተጋቡ ወላጆችን እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ተግባራቸውም ለእነዚህ የተደበቁ ድህነቶች ትኩረት መስጠት፣ እርስ በርስ መተሳሰብ እና በተጨባጭ የማይታዩ ቢሆኑም እውነተኛ እና የሚታመኑ የደካማነት ሁኔታዎችን እንዴት መለየት እንደሚቻል ማወቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

በሞናኮ ውስጥ እንደ ካሪታስ ሞናኮ፣ የቅዱስ ቪንሰንት ደ ጳውሎስ ማኅበር፣ የእመቤታችን ማርያም ማኅበርተኞች እና በችግር ውስጥ የሚገኙ ልጆችን፣ አቅመ ደካማ ቤተሰቦችን፣ አረጋውያንን እና የታመሙትን የሚንከባከቡ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ወይም ሲቪል ማኅበራት መኖራቸውን ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ ገልጸው፥ ይህ ትኩረት በቤተ ክርስቲያኗ ተግባር ውስጥ እንደሚንጸባረቅ እና ዓላማው እርስ በርስ መተሳሰብን፣ ጥሩ ኑሮ መኖርን እና የተወሰነ ደህንነት በሚሰጥ ሀገር ውስጥ የመኖር መብትን አለመገደብ እንደሆነ ገልጸው፥ በሞናኮ ውስጥ ተልዕኳቸው ለሰዎች የበለጠ ትኩረት መስጠት እና ለተቸገሩ ሰዎች ወንጌልን የመመስከር ዕድልን እንዳያመልጥ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

“ቤተ ክርስቲያን በቁምስናዎች፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ወይም በጳጳስ በኩል መልዕክቷን ስታስተላልፍ አድማጮቿን አትመርጥም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ፥ በአገሪቱ ሕይወት ውስጥ ባሉ አንዳንድ አስፈላጊ ወቅቶች ለሁሉም ሰው የመናገር ዕድል መኖሩን ገልጸው፥ “የአንድ ቃል፣ የስብከት ወይም የምስክርነት ፍሬን መለካት አስቸጋሪ በመሆኑ የሚያዳምጡትን መጠየቅ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ሆኖም የተወሰኑ መልዕክቶች ከጊዜ በኋላ የሰዎችን ልብ መድረስ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምላሾችን ማግኘት እንደሚቻል ገልጸው፥ ዓላማቸው የግለሰብን ልብ በጥልቀት መንካት እንደሆነ በማስረዳት፥ “እያንዳንዱ ሰው በሞናኮ ውስጥ ሊኖረው ከሚችለው የተለያዩ ሚናዎች እና ኃላፊነቶች ባሻገር አስፈላጊው ነገር በግለሰቡ ውስጣዊ ፈተና ውስጥ መግባት እና የሌሎችን ሕይወት ማንቃት፣ መለወጥ እና ማቅናት ለሚችል ቃል ራስን መክፈት ነው” ብለዋል።

“እንደሚታወቀው በሞናኮ የካቶሊክ ሃይማኖት የመንግሥት ሃይማኖት ነው” ሲሉ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ፥ ብጹዓን ጳጳሳት እና መላው ቤተ ክርስቲያን ከሁሉም በላይ ከቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ስለሚያገኙት መንፈሳዊ ተሞክሮ እና እምነት በመነጋገር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በተለይም በብሔራዊ በዓላት ወይም በሌሎች ዝግጅቶች ወቅት የካቶሊክ እምነት የባህል ማንነት ወይም ታሪካዊ ቅርስ ብቻ ሳይሆን የአኗኗር ዘይቤያቸውን፣ ምርጫዎቻቸውን እና ግንዛቤያቸውን የሚነካ ኃላፊነት መሆኑን ለማስታወስ እንደሚሞክሩ አስረድተዋል።

“ይህ አመለካከት ለአንዳንድ ሰዎች አዲስ ሊሆን ይችላል” ሲሉ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ፥ ራስን ካቶሊክ ብሎ መጥራትም ሆነ በዚህ መኩራራት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነገር ግን ዓለምን በምንመለከተው መንገድ በሌሎች ላይ በተለይም በድሆች እና በሕይወታችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት መረዳት አለብን” ብለው፥ ወንጌል እንደሚለን፥ እምነት ውጤት እንዳለው እና ከሕይወት ጋር እውነተኛ አንድነት እንዲኖር መጠየቁ አንድን ሰው ሊያስገርም የሚችለው በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

“ሁለት የወንጌል ምሳሌዎችን አስታውሳለሁ” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ዴቪድ፥ የመጀመሪያው የጠፋው በግ ምሳሌ እንደሆነ ገልጸው፥ ኃይላችንን ሁሉ ማለትም ካህናትን፣ ምዕመናን፣ ቁምስናዎችን እና መንፈሳዊ ማኅበራትን በማንቀሳቀስ የምሥራቹ ቃል ከቤተ ክርስቲያን የራቁ ለሚመስሉት ወይም መምጣት ለማይችሉ ሰዎች እንዲዳረስ ማድረግ ነው” ብለዋል።

ሁለተኛው ምሳሌ፥ የዘኬዎስ ታሪክ እንደሆነ፥ ዘኬዎስ ሃብታም እና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያለው ሰው ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ስም የሌለው ሰው ቤት መግባትን እንደመረጠ በማስታወስ፥ ይህንንም ያደረገው ዘኬዎስ የወንጌልን ውበት እና ደስታ እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሆነ አስረድተው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀድሞውኑ መኖሯን ለዘኬዎስ የገለጸው፥ ወደ ሕይወቱ እና ወደ ልቡ ውስጥ በወዳጅነት በመግባት በመሆኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሞናኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝትም ለአገሩ ሕዝብ ታላቅ ጸጋ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት የሞናኮ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዶሚኒክ-ማሪ ዴቪድ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

25 Mar 2026, 16:46