ፈልግ

2023.04.18 gesu chiama i discepoli

«ጌታ» የሚለው ማዕረግ ትርጉም ምንድነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ማዕረግ ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔርን ልዑላዊ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ ይህን ማዕረግ ለራሱ ወሰደ፣ መለኮታዊ ሉአላዊነቱንም በተፈጥሮ ላይ፣ በአጋንንት ላይ፣ በኃጢአትና በሞት ላይ ባለው ኃይል /ሥልጣን/ በተለይም በራሱ ትንሥኤ ገለጸ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያናዊ ጸሎቶች እንደሚገልጹት፣ ለእግዚአብሔር አብ የሚገባ ኃይል፣ ክብርና ምስጋና ለኢየሱስም ይገባል፡፡ እግዚአብሔር «ከስም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጥቶታልና» (ፊልጵ. 2፡9)፡፡ እርሱ የዓለምና የታሪክ ጌታ ነው፣ እኛም የግል ነጻነታችንን ሙሉ በሙሉ ማስገዛት ያለብን ለእርሱ ብቻ ነው፡፡

«ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተፀነሰ፣ ከድንግል ማርያም ተወለደ»

የእግዚአብሔር ልጅ ለምን ሰው ሆነ?

ስለ እኛ ስለሰዎች ስለደህንነታችንም የእግዚአብሔር ልጅ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን ውስጥ ተፀነሰ፡፡ ይህንንም ያደረገው እኛን ኃጢአተኞች ከእግዚአብሔር ጋር ሊያስታርቀንና፣ ስለ እግዚአብሔር ወሰን የሌለው ፍቅር ሊያስተምረን፣ የቅድስና ምሳሌ ሊሆነን እና «የመለኮታዊ ባህርይ ተካፋዮች» (2ኛ ጴጥ. 1፡4) ሊያደርገን ነው፡፡

«ሥጋ መልበስ» ማለት ምን ማለት ነው?

የመለኮታዊና የሰብአዊ ባህርያት በቃል አንድ መለኮታዊ  አካል የመሆንን ድንቅ የአንድነት ምስጢር ቤተ ክርስቲያን «እንደ ሰው ሥጋ መልበስ» ብላ ትጠራዋለች፡፡ የእኛን ደኅንነት ይፈጽም ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ «ሥጋ» ሆነ (ዮሐ. 1፡14) እውነተኛም ሰው ሆነ፡፡ በምሥጢረ ሥጋዌ ማመን የክርስቲያናዊ እምነት ዐይነተኛ ምልክት ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና እውነተኛ ሰው የሚባለው በምን መልኩ ነው?

ኢየሱስ በመለኮታዊ አካሉ አንድነት የማይነጣጠል እውነተኛ አምላክና እውነተኛ ሰው ነው፡፡ «የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ ከአብ ጋር ትክክል የሆነ» የእግዚአብሔር ልጅ እውነተኛ ሰው፣ ወንድማችንና አምላክነቱን ሳይተው ጌታችን ሆነ፡፡

በዚህ ረገድ (እ.ኤ.አ. በ451 ዓ.ም. የተካሄደው) የኬልቄዶን ጉባኤ ምን ያስተምራል?

«በሰብአዊነቱ ፍጹም፣ እውነተኛ አምላክና እውነተኛ ሰው፣ እውነተኛ ነፍስና አካል ባለው፣ ከመለኮቱ ከአብ ጋር እኩል በሆነ፣ በሰውነቱ ከእኛ ጋር እኩል በሆነ፣ «ከኃጢአት በቀር በሁሉም ነገር እንደ እኛ በሆነ» (ዕብ. 4፡15) በመለኮቱ ከዘመናት ሁሉ በፊት ከአብ በተወለደ፣ በነዚህ የመጨረሻ ዘመናትም በሰውነቱ ስለ እኛና ስለ ደኅንነታችንም ሥጋ ለብሶ ከእግዚአብሔር እናት ከድንግል ማርያም በተወለደው በአንድያ ልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ» ያለንን እምነት እንድንገልጽ የኬልቄዶን ጉባኤ ያስተምረናል፡፡

ቤተክርስቲያን ምስጢረ ሥጋዌን እንዴት ትገልጸዋለች?

ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና እውነተኛ ሰው እንደሆነ፣ ሁለት ባህርያት ማለትም መለኮታዊና ሰብአዊ ባህርያት እንዳሉት፣ ያለምንም መደናገር በቃልና በአካል ተዋሕደው እንደሚገኙ ቤተክርስቲያን ታምናለች፡፡ ስለዚህ፣ በኢየሱስ ሰብአዊ ባህርይ ያሉ ነገሮች ሁሉ፣ ተአምራቱ፣ ሕማማቱና ሞቱ ጭምር፣ በሰብአዊ ባህርዩ አማካይነት የሚሠራውን መለኮታዊ አካሉን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

«የእግዚአብሔር አንድያ ልጅና ቃል፣ ሕያው፣ ስለ ደኅንነታችን ከቅድስት የአምላክ እናት ከድንግል ማርያም ሥጋ የለበስህ» (.....) የቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል የሆንክ፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተወደስክ ሆይ አድነን (የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቢን ዘንታይን ሥርዓተ አምልኮ)

ሥጋ የለበሰው የእግዚአብሔር ልጅ ሰብአዊ ዕውቀት ያለው ነፍስ አለው?

የእግዚአብሔር ልጅበአስተዋይ ሰብአዊ ነፍስ የተቀሰቀሰ አካል አለው፡፡ ኢየሱስ በሰብአዊ አእምሮው በልምድ ብዙ ነገሮችን ተማረ፤ የእግዚአብሔር ልጅ በሰብአዊነቱ ደግሞ ስለአባቱ ስለ እግዚአብሔር ጥልቅና የቅርብ ዕውቀት ነበረው፡፡ እንደዚሁም የሰዎችን ድብቅ ሐሳብ ይረዳና ሊገልጻቸው የመጣውን ዘላለማዊ ዕቅዶች ሙሉ በሙሉ ያውቅ ነበር፡፡

ሥጋ የለበሰው ቃል ሁለቱ ፈቃዶች እንዴት ተባበሩ?

ኢየሱስ መለኮታዊ ፈቃድና ሰብአዊ ፈቃድ ነበሩት፡፡ በምድራዊ ሕይወቱ ወቅት የእግዚአብሔር ልጅ በመለኮቱ ስለ ደኅንነታችን ከአብና ከወልድ ጋር የወሰነውን ነገር ሁሉ በሰብአዊነቱ ፈቀደ፡፡ የክርስቶስ ሰብአዊ ፈቃድ ያለተቃውሞ ወይም ያለማወላወል መለኮታዊ ፈቃድን ተከተለ፣ በሌላ  አነጋገር፣ ለመለኮታዊ ፈቃድ ተገዛ፡፡ 92. ክርስቶስ እውነተኛ ሰብአዊ አካል ነበረው?

ክርስቶስ የማይታየው አምላክ የሚታይበትን እውነተኛ ሰብአዊ አካል ወሰደ፡፡ ለዚህም ነው ክርስቶስ በቅዱሳት ምስሎች ሊወከልና ሊከበር የሚችለው፡፡

የኢየሱስ ልብ ምንን ያመለክታል?

ኢየሱስ በሰብአዊ ልብ አወቀን፣ ወደደን፡፡ ስለ ደኅንነታችን የተወጋው ልቡ አብንና እያንዳንዳችንን የሚወድበት የዚያ ወሰን የሌለው ፍቅር ምልክት ነው፡፡

«በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተፀነሰ» የሚለው አገላለጽ ትርጉሙ ምንድነው?

የዚህ አገላለጽ ትርጉሙ ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ወልድን በማሕፀንዋ የፀነሰችው ያለ ወንድ ትብብር በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ መልአኩ «መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል» (ሉቃ. 1፡35) ሲል አበሰራት፡፡

«....ከድንግል ማርያም ተወለደ» ማርያም እውነትም የአምላክ እናት የሆነችው ለምንድነው?

ማርያም እውነትም የአምላክ እናት የሆነችው የኢየሱስ እናት ስለሆነች ነው (ዮሐ. 2፡1፣ ዮሐ. 19፡25)፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተፀነሰውና እውነትም ልጅዋ የሆነው የእግዚአብሔር አብ ዘላለማዊ ልጅ ነው፡፡ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

«ያለ አዳም ኃጢአት መፀነስ» ማለት ምን ማለት ነው?

እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ የልጁ እናትትሆን ዘንድ ማርያምን በፈቃዱ መረጣት፡፡ ተልእኮዋን ለመፈጸም እርስዋ ራስዋ የተፀነሰችው ያለ አዳም ኃጢአት ነበር፡፡ ይህም ማለት፣ በእግዚአብሔር ፀጋና የኢየሱስ ክርስቶስን ትሩፋቶች ተስፋ በማድረግዋ ማርያም መጀመሪያ ከተፀነሰችበት ሰዓት ጀምሮ ከመጀመሪያው ኃጢአት ተጠበቀች።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካጸደቁት፣ በአጭሩ ከተጻፈው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ከዋናው ከላቲን ቅጂ ከተተረጎመው መጽሐፍ ከአንቀጽ 446-492 ላይ የተወሰደ።

12 Feb 2026, 14:58