ፈልግ

ኢየሱስ እና ኒቆዲሞስ ኢየሱስ እና ኒቆዲሞስ  

የየካቲት 08/2018 ዓ.ም ሰንበት ዘወረደ መልዕክቶች እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት፡

1.    ዕብ 13፥7-16

2.   ያዕ 4፥6-17

3.   ሐዋ. 25፥13-27

4.   ዮሐ 3፥10-24

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም። ስለ ምድራዊው ነገር ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል። ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”

መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ መሰከረ

ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋር ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም። በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ፣ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር። ይህም የሆነው ዮሐንስ ከመታሰሩ በፊት ነበር።

የእለቱ አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘወረደ የተሰኘውን ሰንበት እናከብራለን። ዛሬም እንደ ወትሮው ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት እያንዳንዳችንን ይጐበኘናል፤ ያስተምረናል።

በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው መልዕክቱ  እንዲህ ይላል “የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሯችሁን የቀድሞ አባቶቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፈር እየተመለከታችሁ በእምነታችሁ ምሰሉዋቸው” ይላል።

የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሩን ማናቸው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ ቅን በነበሩ ሰዎች አማካኝነት በነ ሙሴ በነ አሮን እንዲሁም ከዛም በኋላ በተለያዩ ነቢያት አማካኝነት ሕዝቡን ያስተምር ነበር። ነገር ግን ይህ ሁሉ ትምህርትና ተግሳጽ የሰውን ልብ ሙሉ በሙሉ ሊገዛው ባለመቻሉ በስተመጨረሻ አምላክ ራሱ ሰው በመሆን አስተማረ ከሱም በኋላ እንዲያስተምሩ ሐዋርያቶችን አዘጋጀ በዓለምም ሁሉ እየተዘዋወሩ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ላካቸው።

ዛሬ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን አስተማሪዎች አስቡ የደረሱበትንም ቦታ በማሰብ የሚላችሁን ስሙ መንገዳቸውንም ተከተሉ በእምነታችሁም ምሰሉአቸው ይለናል። እነዚህ የቀድሞ አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዛዦች ነበሩ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ለአምላካቸው ለፈጣሪያቸው ይሰጡ ነበር በመሆኑም እግዚአብሔርን አከበሩ እርሱም አከበራቸው። እግዚአበሔር ስለ እነርሱ መሰከረ እኔ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ የሕያዋን አምላክ ነኝ አለ።

ስለዚህ እነዚህ አባቶቻችን የደረሱበትን ቦታ በማሰብ እናንተም በእምነታችሁ የእነርሱን አብነት ተከተሉ ይለናል። እነርሱ እግዚአበሔር ባመላከታቸው መንገድ ስለተጓዙ እምነታቸውን ጠብቀው ስለኖሩ ስማቸው በሰማይም ሆነ በምድር ሕያው ሆኖ ይኖራል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ነው እነርሱን ምሰሉ የሚለን እኛም እንደነሱ በሰማይም ሆነ በምድር ሕያው ሆነን እንድንኖር ነው።  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ አባቶች ከመፈጠራቸው በፊት ነበር ዛሬም ከኛ ጋር አለ ወደፊትም ይኖራል። በዕብራውያን መልእክት ቁ. 8 ላይ ሲነበብ እንደሰማነው “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘለዓለም ያው ነው ይለናል።”

እንግዲህ ይህ ጥንትም የነበረ ዛሬም ያለ አምላክ እምነታችን ጠንካራ እንዲሆን  በሰው አምሳል ተፈጥሮ አስተማረን። የእርሱንም ትምሕርት ይዘው እንዲቀጥሉ ሐዋርያቶችን ወደ ዓለም ሁሉ ላከ የእነርሱንም ትምህርትና እምነት እንድንከተል እኛንም በጸጋው ሞላን። ታዲያ ዛሬ እኛ ይህንን ትምሕርት እና የእነዚህን ቅዱሳኖች አብነት በመከተል ላይ እንገኛለን ወይስ ደግሞ በራሳችን ስሜትና ፍላጎት ብቻ በመመራት በዓለም ላይ እየተቅበዘበዝን እንገኛለን? ልባችን በእግዚአበሔር ላይ ካልፀና በምንም መልኩ የተረጋጋ ሕይወት ሊኖረን አይችልም እውነተኛ ውስጣዊና ውጫዊ ሰላም ሊኖረን አይችልም  በዚሁ ተመሳሳይ መልዕክት ቁ.9 ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል  “ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ ልባችሁ በጸጋ ቢፀና መልካም ነው ይለናል።”

ይህንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ሐዋርያቶችና አባቶች በደማቸው የመሰከሩለትን በአንድ ዓለት ላይ የተመሰረተን እምነት ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘወትር ለልጆቿ ታስተምራለች። ይህ እምነታችን እንዳያድግ ብሎም ፍሬ እንዳያፈራ በመንገዳችን ላይ ብዙ መሰናክል ይኖራል። ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ ሰይጣን እምነታችን ጽኑ እንዳይሆን በብዙ መልኩ ይፈትነናል ይላል።

እኛም እግዚአብሔርን በተከፈለ ልብ የምንቀርብና በተከፈለ ልብ የምንታዘዝ ከሆነ በሰይጣን ፈተናዎች በቀላሉ እንታለላለን በፈተናውም እንወድቃለን። እነዚህ አባቶቻችን እንዳስተማሩን በትሕትና በሙሉ ልብ ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን እምነታችንም የፀና ከሆነ በጸጋው ይሞላናል። ጸጋውም በእግዚአብሔር መንገድ ውስጥ እንድንመላለስ ያደርገናል።  የሰይጣንን ሥራ እንድንክድና በእምነታቸንም ጠንክረን እንድንቆም ያግዘናል።

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ይለናል “ትሑት የሆነውንና ለንሰሃ የተዘጋጀውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” (መዝ. 51) ይላል።

የዛሬው ወንጌል መጽሐፍ ቅዱሳችን በሙሉ ሊል የሚፈልገውን እውነት ጭብጥ አድርጎ የያዘ እውነትን ያካፍለናል። ይህን ለመግለጽ ከሚጠቀምባቸውም ወሳኝ ቃላት መካከልም “ዓለም” ፣ “ፍርድ” ፣ “የእግዚአብሔር ፍቅር” የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህ ቃላት ብዙ ጊዜ ግልጽ ሆነው በቀላሉ የማይረዱን ስለሆኑ በዕለታዊ ሕይወታችን ከክንዋኔዎች ጋር አስታርቀን ለመኖሩ ይከብደናል። ስለዚህ በወንጌሉ ይዘት መሠረት መልእክታቸውን ለማየትና ለክርስትናችን ምን ሊፈይዱ እንደሚችሉ እናስተንትን።

ዮሐ.1፥10 ላይ “…ዓለምም የተፈጠረው በርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም” ይላል። ዓለም ሲል የማይያዝ የማይጨበጥ ነገርን ለመጥቀስ ወይም ደግሞ ግኡዝ የሆኑትን ፍጥረታት ለማመልከት ሳይሆን በዓለም ኖረን ወደ ደኅንነት እንደርስ ዘንድ የተፈጠርን የሰው ልጆችን ለማለት ነው። ለዘለዓለማዊነት ሳይሆን ለጊዜያዊ ነገር የሚሮጥ፣ ራሱን ለተፈጠረበት ዘለዓለማዊነት የማይሠራ ወይም የማይገራ ሁሉ “ዓለም” በሚለው ጠቅላላ መጠሪያ ይካተታል። ክርስቶስን አውቀዋለሁ ወይ ብለን እናስብ። ብዙ ብዙ ነገር እናውቅ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ለማወቅ እናቅድ ይሆናል፤ ሆኖም ግን ክርስቶስን ለማወቅ ውሳኔውም ፍላጎቱም ከሌለን “ዓለም” የተባለው ክፍል መሆናችን ነው።

በእንደዚህ ዓይነት የእርሱን አቅጣጫ ባልተከተለ ሕይወት እንኖር ዘንድ እርሱ አይፈልግምና ክርስቶስ ስለ ደቀመዛሙርቱ ሲናገር “እኔ የምጸልየው ለእነርሱ ነው፤…ለዓለም አልጸልይም።” አለ። ለእርሱ ያለንን ፍላጎትና ፈቃድ ጭክን አድርገን ከቆለፍን ክርስቶስ ሊሰብረው ስለማይፈልግ አይጸልይልንም። በራሳችን ላይ ከፈረድን እግዚአብሔር አይፈርድብንም፤ ይህ ማለት ግን አይወደንም ማለት አይደለም። ስለሚወደን ፈቃዳችንንና ነጻነታችንን አይጋፋም።

በዮሐ 3፥16 ላይ “እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንድ ልጁን ሰጠ፤ ስለዚህ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም።” ይላል። የነፍሳችን ኀላፊነት በእጃችን ነው፤ እሱ እኛ ላይ ካልፈረደ ራሳችን ላይ የምንፈርደው እኛው ነን ማለት ነው። በርግጥ የመጨረሻ እጣ ፈንታችን በርሱ ቢሆንም፤ በየደቂቃዋ፣ በየዕለቷ የምንከተላት ፈቃዳችን ለፍጻሜያችን ወሳኝ ናት።

ይህ የዮሐንስ ወንጌል ም.3፥16 መላ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ጠቅልሎ ይዟልና “የመጽሐፍ ቅዱስ እምብርት” ወይም ማዕከላዊ ነጥብ ለማለት ያስችላል። ለምን ካልን ከላይ እንደተመለከትነው በአንድ በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር፤ ከፍቅሩም የተነሣ ልጁን ለኛ መላኩንና ለዚህ የምንሰጠው ምላሽ ውጤትን ማለትም የዘለዓለም ሕይወትን ውርሻ ስለሚያስረዳ ነው። ይህ እውነት ዕለታዊ ሕይወታችንን ሊመራ ይገባል። በእግዚአብሔር “እጅግ” የተወደድን ነን፤ በሰው መወደድ የመጨረሻ ሙላት በእግዚአብሔር መወደዳችን ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር በሰው መወደዳችንን አያጓድልብንም፤ ይልቁንም ሙሉ ያደርግልናል። የእግዚአብሔርን ፍቅር ሳንለማመደውና ሳንመልስ ስለሰው ፍቅር ብናወራ ሁሌም ጎዶሎና ከንቱ ነገር ብቻ መሆኑን ለማወቅ ምናልባት ትንሽ የጊዜ ሂደት ብቻ ነው የሚያስፈልገን። ስለዚህ ነፍሳችን ብሎም መላ ማንነታችንን የሚሞላው ይህ የላቀ የአምላክ ፍቅር ነውና ዛሬ “እጅግ እወድሃለሁ/እወድሻለሁ” ለሚለው ቃሉ መልስ እንስጠው።

የዛሬው ወንጌላችን ቁ.19-21 ላይ “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ይላል። ብርሃን -- ጨለማ ፣ ክፋት -- እውነት የሚሉት ሃሳቦችም በትይዩነት ቀርበዋል። ሁለቱ ነገሮች በአንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም። ብርሃን ወይም ጨለማ፣ ክፋት ወይም እውነት። 14፥6 ላይ ክርስቶስ እኔ እውነት ነኝ ይላልና “እውነት” ለዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ ነው። ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ ምክንያቱም ሥራቸው ክፉ ስለሆነ ነው ይላል። እንግዲህ ይህ ምርጫ ነው ወሳኝ ለውጥ የሚያመጣው ወይም ሕይወታችን ላይ እንድንፈርድ የሚያደርገን። ክርስቶስ እኔ ባለሁበት በኩል በብርሃኑና በእውነቱ ወገን ኑ ይለናል። የእግዚአብሔር ቃል እወጃ፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ግብ ሁሉ ለዚህ ነውና በምስጢራቱ አንጽቶና መግቦ ከርሱ ጋር እንራመድ ዘንድ ሊያበረታን ወደ ሚጠብቀን ኢየሱስ እንሂድ።

ይህንን ለማድረግ እና በክርስትና እምነታችን በብርሃኑ ለመመላለስ እንድንችል ዘወትር የዓለም ብርሃን እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋንና በረከትን ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ታማልደን። 

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

 

 

 

14 Feb 2026, 22:24