የታሊታ ኩም እንቅስቃሴ የታሊታ ኩም እንቅስቃሴ  

በታሊታ ኩም የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳዮች አስተባባሪ ‘ሰላም ሰብዓዊ ክብርን በመጠበቅ ይጀምራል’ ማለታቸው ተነገረ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጎረጎሳዊያኑ የካቲት 8 የዓለም የጸሎት እና የአስተንትኖ ቀንን ባከበረችበት ወቅት የታሊታ ኩም ዓለም አቀፍ አስተባባሪ እህት አቢ አቬሊኖ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመዋጋት ረገድ የሚያጋጥሙ ወቅታዊ ፈተናዎችን እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በማንሳት ገለፃ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዛሬ በዓለም ላይ ካሉት በጣም ተስፋፊ እና ብዙም የማይታዩ የጥቃት ዓይነቶች አንዱ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ዓለም አቀፍ ችግር በመላው አህጉራት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሰለባ ማድረጉ እና ይህ ተግባር ከሞላ ጎደል የሚከናወነውም ድምጽ ሳያሰማ፣ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በመላመድ፣ የፍልሰት መስመሮችን በመቆጣጠር እና ከዓለም አቀፉ ኢ-ፍትሃዊነት አሰራር ጋር በመላመድ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በየዓመቱ የሚከበረው የዓለም የፀሎት እና የአስተንትኖ ቀን ይህንን ድብቅ ወንጀል ወደ ብርሃን ለማምጣት ጥረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የሥራ ሳምንት
ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ሮም 12ኛውን የዓለም ቀንን ምክንያት በማድረግ ተከታታይ ስብሰባዎችን፣ ጸሎቶችን እና ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ያስተናገደች ሲሆን፥ ታሊታ ኩምን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እየሠሩ በሚገኙ ሰፋፊ የድርጅቶች ትስስር በተደገፈው በዚህ ሳምንታዊ መርሃ ግብር ‘ሰላም ሰብዓዊ ክብርን በመጠበቅ ይጀምራል’ በሚል ጭብጥ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ በመከላከል እና ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ በማተኮር የተለያዩ ዝግጅቶች መካሄዳቸው ተነግሯል።

የችግሩ ሰለባዎች ተሳትፈዋል
በዚህ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረጉ የዕለት ተዕለት ጥረቶች ላይ ከተሰማሩት ሰዎች መካከል በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ የሚሰራው ዓለም አቀፉ የካቶሊክ እህቶች ትስስር የሆነው የታሊታ ኩም አስተባባሪ የሆኑት እህት አቢ አቬሊኖ ሲሆኑ፥ እህት አቢ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቆይታ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዴት እየተቀየረ እንደሆነ፣ ችግሩን መከላከል ለምን አጣዳፊ እንደሆነ፣ እንዲሁም ስደትን እና ብዝበዛን በመከላከል ሂደት ውስጥ ሰብዓዊ ክብርን መጠበቅ ወሳኝ የሆነበትን ምክንያት በማንሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“በልቤ ፊሊፒናዊ ነኝ፤ ሕይወቴ ግን የተቀረጸው በተለያዩ ባህሎች መካከል በመኖር ነው” ያሉት የፊሊፒንስ ተወላጅ የሆኑት እህት አቢ፥ ቤተሰባቸው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በመሰደዳቸው ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ የኖሩት አሜሪካ ውስጥ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ በጃፓን በነበራቸው የሚስዮናዊነት ሥራ በፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጥረቶች ላይ በተለይም አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህፃናት በሆኑበት ከስደተኞች እና ፍልሰተኞች ጋር በመስራት የተሳትፎዋቸው ጅማሮ ማድረጋቸውን አስታውሰው፥ ተሞክሯቸውን በማዳመጥ ስደት እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ምን ያህል የተሳሰሩ እንደሆኑ ማስተዋላቸውን አብራርተዋል።

ይህ ተሞክሮ በአሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ በሚበልጡ ሃገራት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ወደሚገኘው ወደ ታሊታ ኩም እንደመራቸው እና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ያለው ግንዛቤ እየጨመረ ቢመጣም ችግሩ በራሱ እያደገ መሄዱን ገልጸው፥ “በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሰዎችን ክብር እንደ ሚጥስ ይገነዘባሉ” ያሉ ሲሆን፥ ነገር ግን ብዙ ጉዳዮች አሁንም ድረስ መደበቃቸውን እና የምናያቸው ቁጥሮች ሙሉ እውነታውን እንደማያንጸባርቁ ገልጸዋል።

የማጭበርበር ስልቶች
የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ዘዴዎች በከፍተኛ ሁኔታ መለወጣቸውን የጠቆሙት እህት አቢ፥ በአሁኑ ወቅት ኢላማ የሚደረጉት በጣም ድሆች ወይም አነስተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ፥ ከዚህም ይልቅ በዛሬው ጊዜ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በደንብ የተማሩ እና ብዙ ቋንቋዎችን መናገር በሚችሉ ወጣቶች ላይ እንደሚያነጣጥሩ ገልጸው፥ የሥራ ምልመላ ብዙውን ጊዜ ህጋዊ እና ሙያዊ በሚመስሉ መልኩ በድህረ ገጽ አማካይነት እንደሚካሄድ እና የሥራ ስምምነት ሰነዶችን፣ ቪዛዎችን እና ግልጽ መስፈርቶችን ስለሚያሳዩ በርካታ ተጎጂዎች ለትክክለኛ ሥራዎች ያመለከቱ ሆኖ እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

ከታሊታ ኩም ልምድ በመነሳት አብዛኛው ምልመላዎች የሚደረጉት ፊሊፒንስን ጨምሮ በተለይ በአፍሪካ እና በኢስያ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ አንዳንድ የችግሩ ሰለባዎች በድህረ ገጽ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች ተታለው ከስፍራ ስፍራ እንደሚዘዋወሩ እና ብዙ ጊዜ እነዚህ ተግባራት በማይናማር፣ በካምቦዲያ እና በታይላንድ አዋሳኝ አካባቢዎች እንደሚፈጸሙ ተገልጿል።

ከእነዚህም ውስጥ አንዳንድ ሰለባዎች ታይላንድ ውስጥ እንደሚሠሩ የተነገራቸው ቢሆንም፥ ነገር ግን በመጨረሻ እራሳቸውን የሚያገኙት በሌላ አከባቢ እንደሆነ እና እዚያ ከደረሱ በኋላ መውጣት እንደማይችሉ የገለጹት እህት አቢ፥ እዚያም ሰለባዎቹ የቅጥር እና የማጓጓዣ ወጪያቸውን ለመመለስ በግዳጅ ለመስራት እንደሚገደዱ እንዲሁም ስልጠና እንደሚወስዱ፣ በተለያየ ቦታ እንደሚመደቡ እና ውጤት እንዲያመጡ ጫና እንደሚደረግባቸው ጠቁመው፥ ይህ የተደራጀ ወንጀል እንደሆነ እና የዘመናዊ ባርነት መገለጫ መሆኑን አመላክተዋል።

ቅድመ-መከላከል
በተለይ ግጭት በተከሰተባቸው ክልሎች ሰለባዎቹን መታደግ ከባድ እንደሆነ የገለጹት እህት አቢ፥ የአንዳንድ አካባቢዎች መዳረሻ እጅግ በጣም የተገደበ በመሆኑ እና ብዙውን ጊዜ እርዳታ ማድረግ የሚቻለው አንድ ሰው ድንበር ላይ ከደረሰ ብቻ እንደሆነ ጠቁመው፥ ታሊታ ኩም ለማምለጥ የቻሉትን ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን እና በእነዚህ ድንበሮች ላይ ከሚገኙ ተባባሪዎች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ቅድመ መከላከል የታሊታ ኩም ማዕከላዊ ተግባር መሆኑን ጠቁመው፥ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ከመከሰቱ በፊት አስቀድመው ለማቆም እየሰሩ እንደሚገኝ እና በተለይም በስደት ዙሪያ ትምህርት እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ቁልፍ ተግባራት እንደሆኑ አመላክተው፥ ‘ስደት ሰብዓዊ መብት ቢሆንም፥ ነገር ግን ሰዎች መብቶቻቸውን ማወቅ እና የሚያስከትለውን አደጋ መረዳት አለባቸው’ ብለዋል።

አንድ የሚያውቁት ካህን ለመሰደድ እየተዘጋጀች ላለችው የቤተሰብ አባል የቀረበላትን ሥራ በቅድሚያ እንድታረጋግጥ የጠየቁበትን ሁኔታ ያስታወሱት አስተባባሪዋ፥ በእሳቸው ተቋም በኩል በተደረገ ምርመራ ኩባንያው በትክክል አለመኖሩን እንደደረሱበት እና ይህ ቀላል ምርመራ አደገኛ ሊሆን የሚችል ሁኔታን እንዳስቀረ አስረድተዋል።

እንደ እህት አቢ ገለጻ፣ በርካታ ተጎጂዎች በሕገ ወጥ መልኩ እየተዘዋወሩ መሆናቸውን እንደማይገነዘቡ እና ብዙውን ጊዜ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ የሚያምኗቸው ሰዎች እንደሆኑ ገልጸው፥ አንዳንድ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች እንደሚናገሩት ዘመድ ወይም የሚያውቋቸው ሰዎች ይሄንን ይፈጽማሉ ብለው እንደማያስቡ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ተጎጂዎች ለራሳቸው ህልውና እንደ ቅድመ ሁኔታ ሌሎችን ለመመልመል እንደሚገደዱ ገልጸዋል።

ዘላቂ ጉዳት
እህት አቢ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ላይ ያለው ተጽእኖ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ እንደሆነ ጠቁመው፥ ‘ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል፥ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን እና የደህንነት ስሜትን እንደሚነካ የገለጹ ሲሆን፥ ከጉዳቱ ለማገገም ጊዜን፣ ድጋፍን እና አስተማማኝ የሆነ ሥራን ማግኘት እንደሚጠይቅ እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ከሌለ ሰዎች ለአደጋ እንደሚጋለጡ አሳስበዋል።

ይህም በመሆኑ አንዳንድ የጥቃቱ ሰለባ የነበሩ ሰዎች ስለ ልምዳቸው በይፋ መናገርን እንደሚመርጡ እና ሌሎች ተመሳሳይ መከራ እንዳይደርስባቸው ለመከላከል እንደሚፈልጉ ያመለከቱት እህት አቢ፥ ምስክርነታቸው በተለይ ለወጣቶች ጠቃሚ እንደሆነ፥ ቀድመው የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ መሆናቸውን ያልገለፁትን ሰዎችን ማግኘታቸውን በማስታወስ፥ ብዙ ሰዎች ‘ይህ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መሆኑን አላውቅም ነበር’ እንደሚሉ ገልጸው፥ በኋላ ላይ መብቶቻቸው እንደተወሰደባቸው መረዳት ሲጀምሩ ምን እንደተፈጠረ እንደሚገነዘቡ እና ይህ የግንዛቤ ማነስ ቅድመ መከላከልን የበለጠ አጣዳፊ ጉዳይ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያት ታሊታ ኩም በየደረጃው ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ የጠቆሙት እህት አቢ፥ የተለያዩ ገዳማዊያት እህቶች በትምህርት ቤቶች፣ ደብሮች እና ማህበረሰቦች ውስጥ በዚህ ዙሪያ እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ግንዛቤ መጀመር ያለበት ከታች ስለሆነ በህፃናት ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ እንደሚገኝ እንዲሁም ወጣቶች በጣም ተጋላጭ እና ሀይለኛ የለውጥ ወኪሎች በመሆናቸው እና እየሆነ ያለውን ነገር ስለሚረዱ እርስ በርሳቸው ይጠባበቃሉ ብለዋል።

የሰብዓዊ እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም
በስደት ዙሪያ ባሉ ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ክርክሮች እና በጠንካራ የስደተኛ ህጎች ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት እህት አቢ፥ ለሰብዓዊ ክብር ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት ጠቅሰው፥ ስደት አብዛኛውን ጊዜ እንደ ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ እንደሚወሰድ፥ ነገር ግን በመሠረቱ የሰብዓዊ ጉዳይ እንደሆነ ያስረዱ ሲሆን፥ የራሳቸውን ቤተሰብ የስደት ልምድ እና በአሁኑ ወቅት በበርካታ ስደተኞች ዘንድ ያለውን የፍርሃት ስሜት ገልጸው፥ በማግለል ወይም በቅጣት ላይ የተመሰረቱ ፖሊሲዎች ተጋላጭነትን እንደሚጨምሩ እና የስደትን ወይም የሕገወጥ ዝውውር መንስኤዎችን እንደማይመለከቱ ጠቁመዋል።

ሰላም ሰብዓዊ ክብርን በማስጠበቅ ይጀምራል
የዘንድሮውን የዓለም ቀን መልዕክት በማስታወስ “ሰላም ሰብዓዊ ክብርን በመጠበቅ ይጀምራል” ያሉት እህት አቢ፥ ሰብዓዊ ክብር ካልተጠበቀ ሰላምን ማስጠበቅ እንደማይቻል እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከዓለም አቀፍ ጉዳዮች መለየት እንደማይቻል ገልጸዋል። ድህነት፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ አደጋዎች፣ ግጭቶች እና የግዳጅ ስደት በአጠቃላይ ተጋላጭነትን እንደሚጨምሩ አስታውሰው፥ ሰዎች ቤታቸውን በቀላሉ እንደማይለቁ እና ሆኖም ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ለመሰደድ ሲገደዱ ለሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።

ይህም በመሆኑ ምክንያት የታሊታ ኩም ሥራዎች ከማዳን እና ግንዛቤ ከማስጨበጥ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደሚደረጉ የጥብቅና እና የትብብር ሥራዎች እንደሚዘልቁ የገለጹት እህት አቢ፥ በመጨረሻም ትስስሩ በአገር ውስጥ እየሰራ ቢገኝም፥ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጃን በማጋራት እና በድንበር በኩል ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ያስታወሱ ሲሆን፥ ይሄንን ሥራ አንድ ቡድን ብቻውን ሊያደርገው የሚችለው ነገር እንዳልሆነ ጠቅሰው፥ “በተቋማት፣ በመንግሥታት፣ በማኅበረሰቦች እና በግለሰቦች መካከል የጋራ ኃላፊነት እና መተባበርን ይጠይቃል” በማለት አጠቃለዋል።

09 Feb 2026, 13:27