ፈልግ

 ሬዲዮ ቬሪታስ ኢስያ ያዘጋጀው የፊልም ስራ ውድድር ሬዲዮ ቬሪታስ ኢስያ ያዘጋጀው የፊልም ስራ ውድድር  (©Radio Veritas Asia website)

ራዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ የተባለ የካቶሊክ ሚድያ በወጣት ጋዜጠኞች የተዘጋጀ የመታሰቢያ መጽሃፍ ማስመረቁ ተነገረ

ራዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ የተባለ የካቶሊክ ሚድያ የአጭር የፊልም ውድድር የሽልማት ሥነ-ሥርዓት እና የመታሰቢያ መጽሐፍ ምርቃት ላይ በርካታ የእስያ ግለሰቦችን በማሰባሰብ ትልቅ የድህረ ገጽ ስብሰባ ማዘጋጀቱ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥር 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ራዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ (RVA) የኤዥያ ፊልም ሰሪዎችን፣ የቤተክርስቲያን የሚድያ ባለሙያዎችን፣ የአካባቢ ተሟጋቾችን፣ የሃይማኖት ምሁራንን እና ብፁዓን ጳጳሳትን አንድ ላይ ያሰባሰበ የኦንላይን ዝግጅት ያካሄደ ሲሆን፥ በዚህም ጊዜ የላውዳቶ ሲ እንክብካቤ ለፍጥረት የአጭር ፊልም ውድድር የሽልማት ሥነ ስርዓት እና ‘ድምጾች ለጋራ ቤታችን’ የተሰኘውን የመታሰቢያ መጽሐፍ ምርቃት መርሃ ግብሮች መካሄዳቸው ተገልጿል።

ይህ የአጭር ፊልም ውድድር ከኢስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን የተላከውን ሃዋሪያዊ ደብዳቤ ተከትሎ በራዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ የተጀመረ የአንድ ዓመት ዘመቻ አካል መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ዘመቻ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ የሆነው ‘ላውዳቶ ሲ’ አሥረኛ ዓመት ለማክበር ተብሎ የተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።

መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ የተደረገው ውድድሩ ከኢስያ እና ከአከባቢው ሃገራት የመጡ ዘጋቢዎችን የጋራ ቤታችንን በመንከባከብ እና በእስያ የላውዳቶ ሲ' ተጽእኖ ላይ ያተኮረ ከሶስት እስከ አምስት ደቂቃ እርዝማኔ ያላቸው ኦሪጅናል ፊልሞችን እንዲያቀርቡ መጋበዙ ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት ከ 80 በላይ ፊልም ሰሪዎች ለመወዳደር የተመዘገቡ ሲሆን፥ የውድድሩ ዳኞች በጥንቃቄ የማጣራት ሂደት ማድረጋቸው ተገልጿል።

በዚህ ሂደት ላይ የተሳተፉ ዓለም አቀፍ የዳኞች ቡድን አስር የማፅናኛ ተሸላሚዎችን እና ሶስት የመጨረሻ ደረጃ ሽልማት አሸናፊዎችን ጨምሮ 13 የመጨረሻ እጩዎችን መምረጣቸው ተነግሯል።

የራዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ ፕሮግራም ዳይሬክተር እና የኤዥያ ጳጳሳት ጉባኤ ፌዴሬሽን የማህበራዊ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ዋና ፀሃፊ የሆኑት አባ ጆን ሚ ሼን የመርሃ ግብሩን ተሳታፊዎች በደስታ ተቀብለው ዝግጅቱ ከመርሃ ግብርም በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በንግግራቸው ወቅት ስለ ላውዳቶ ሲ' ራዕይ እና ፍጥረትን መንከባከብ የክርስቲያናዊ ደቀ መዝሙርነት ቁልፍ አካል እንደሆነ አበክረው የተናገሩት አባ ጆን፥ በዚህ አጭር የፊልም ውድድር በመላው ኢስያ የሚገኙ ወጣት የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ለሥነ-ምህዳር ለውጥ ለተደረገው ጥሪ በአዳዲስ ፈጠራ ምላሽ በመስጠታቸው የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸው፥ “ታሪኮቻቸው ህሊናን የሚያነቃቁ፣ ርህራሄን የሚያሳድጉ እና ኃላፊነት ለተሞላበት እርምጃ የሚያነሳሱ ናቸው” በማለት ተናግረዋል።

የቫቲካን የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤትን ወክለው ዶክተር ናታሳ ጎቬካር የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ዲጂታል ሚዲያ በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅት ራዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ የላውዳቶ ሲ መንፈስ በህይወት እንዲኖር ስላደረገው አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሰው ልጅ ፍጥረትን እንደሚጠብቅ እና በተፈጥሮም እንደሚጠበቅ ያስታወሱት ዶክተር ናታሳ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የዓለም የመገናኛ ቀንን አስመልክተው ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ፥ በዲጅታሉ ዓለም ስክሪኖች ላይ ከመጠን በላይ መታመን ሰዎችን ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያቋርጥ በማስጠንቀቅ እውነተኛን የሰው ፊት እና ድምጽ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

“የጋራ ቤት” የመታሰቢያ መጽሐፍ
ከመርሃ ግብሮቹ ውስጥ ዋነኛው የነበረው ‘ድምጾች ለጋራ ቤታችን፡ ላውዳቶ ሲ በኢስያ’ የተሰኘው የመታሰቢያ መጽሐፍ ገለፃ እና ይፋዊ ምርቃት የነበረ ሲሆን፥ የካሪታስ ፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ብፁዕ አቡነ ጌራርዶ አልሚናዛ መጽሐፉን በይፋ ማስመረቃቸው ተነግሯል።

ብፁዕ አቡነ አልሚናዛ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገቡት ድምጾች ላውዳቶ ሲ በኢስያ ላይ ስላሳደረው ተጽእኖ ምስክር ብቻ ሳይሆን የጋራ ቤታችንን የመንከባከብ አስፈላጊነትንም ያስታውሳሉ ያሉ ሲሆን፥ ቤተክርስቲያን ለሥነ-ምህዳር ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ እንደማትሰጥ ጠቅሰው፥ መጽሐፉ ግንዛቤን እንደሚያሳድግ እና ሰዎች ተባብረው እንዲሰሩ እንደሚያበረታታ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በማሌዥያ የኩቺንግ ሊቀ ጳጳስ እና የወንጌል ስርጭት ፅህፈት ቤት ሊቀ መንበር የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ሳይሞን ፖህ ለወጣት ፊልም ሰሪዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ወጣቶቹ የቤተክርስቲያንን “አሁናዊ” ሁኔታ እንደሚወክሉ የገለጹ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ ‘ለጋራ ቤታችን ድምጾች’ ለሚለው መጽሃፍ አንድ አንቀጽ ማበርከታቸውን ጠቁመው፥ በላውዳቶ ሲ ውስጥ ቁልፍ ጉዳይ የሆነውን የአባቶችን ጥበብ መጠበቅ እና ማካፈል አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ገልጸዋል።

ዝግጅቱ የተጠናቀቀው ሽልማቱን ያሸነፉ ሶስቱ ምርጥ ፊልሞችን በማሳወቅ እና በማሳየት ሲሆን፥ የራዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አባ ፌልማር ፊኤል ከታይላንድ “ፍቅር በድርጊት” የተሰኘው ፊልም አንደኛ መውጣቱን ገልጸው የተሸለመ ሲሆን፥ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ሦስቱም ፊልሞች ከታዩ በኋላ የፊልም ሰሪዎቹ አጫጭር መልዕክቶች ተደምጠዋል።

አባ ፌልማር በመዝጊያ ንግግራቸው ላይ ፊልም ሰሪዎቹ፣ ዳኞች፣ የመጽሐፉ አበርካቾች፣ ብፁዓን ጳጳሳት እና አጋሮች በጋራ በመስራታቸው አመስግነው፥ የኢስያ ሥነ-ምህዳራዊ ተልዕኮን ለእግዚአብሔር አደራ በመስጠት ዝግጅቱን በጸሎት እና ቡራኬ አጠቃለዋል።

ይህ ድርብ አከባበር ራዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ ላውዳቶ ሲ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ “የጋራ ቤታችንን” መንከባከብ እንደሚገባ ጥሪ ካደረገ ከአሥር ዓመታት በኋላ የእስያ ድምጾችን ለመደገፍ እና በእምነት ላይ የተመሰረተ የአካባቢ እንክብካቤን ለማበረታታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ተብሏል።

02 Feb 2026, 14:26