59ኛው የዓለም የሰላም ቀን ተከብሯል  59ኛው የዓለም የሰላም ቀን ተከብሯል  

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ የሰላም ቀንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ለሰላም ግንባታ የተሃድሶ አቀራረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል

በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለመለወጥ፣ በማኅበረሰቦች ውስጥ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች እና እስራት ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም በአካባቢ እና በሀገረ ስብከት ደረጃ ያለውን የመከፋፈል ቁስሎችን ለመፈወስ የተሃድሶ ዘዴዎችን እንደ ተግባራዊ መሣሪያ እየተጠቀመች ነው ሲሉ የካቶሊክ ሞቢላይዚንግ ኔትዎርክ ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በእያንዳንዱ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የዓለም የሰላም ቀንን የምታከብር ሲሆን፥ ይህም በዓለም ዙሪያ ያለውን ጥልቅ የሰላም ፍላጎት በማስታወስ እና ሰብአዊ ክብርን ለማስከበር ቤተክርስቲያኗ በምታደርገው ጥረት ለሰላም ግንባታ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ተገልጿል።

ይህ ቀን ብዙዎች አዳዲስ ግቦችን የሚያወጡበት ወይም ውሳኔ የሚያደርጉበት በዓመቱ መጀመሪያ ላይ መከበሩ ጠቃሚ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ አንድ ሰው ለዓመቱ ምንም ዓይነት የግል ግቦች ወይም ምኞቶች ቢያስቀምጥ፣ ቤተክርስቲያኒቷ ለሰላም ግንባታ የጋራ ቁርጠኝነት እንዲኖረን ጥሪዋን ታቀርባለች ተብሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በዚህ ዓመት በተከበረው 59ኛው የዓለም የሰላም ቀን “ሰላም ትጥቅ ለፈቱትም እየፈቱ ለሚገኙትም ለሁላችሁም ይሁን” በሚል ርዕስ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ቅዱስ አባታችን በዚህ መልዕክታቸው የጴጥሮስ ተተኪ ሆነው በተመረጡበት ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በረንዳ ላይ ሆነው ያሰሙትን የመጀመሪያ ቃል የሚያስተጋባ እንደሆነም ተነግሯል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በዓመፅ ጨለማ ውስጥ እንኳን ብርሃንን ስለሚያበራው ጽናት ምስክር ተናግረው፥ ይህ መድረሻ ሳይሆን ነገር ግን ቁርጠኛ ጉዞ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንዲሁም የማዳመጥ እና ትርጉም ያለው ውይይት አስፈላጊነትን እንደሚያስታውሰን የገለጹ ሲሆን፥ ይህ ቀጣይነት ያለው የሰላም ስራ እንደሆነ እና የፍትሃዊ ተሃድሶ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅዱስ አባታችን በሠላም ግንባታ እና በተሃድሶ ልማዶች መካከል ያለውን መሠረታዊ ግኑኙነቶችን ሲገልጹ፥ “በሲቪል ማህበረሰቦች ውስጥ እራስን ማወቅን፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ማህበራት ዓይነቶችን፣ የሰላማዊ ተሳትፎ እና የተሃድሶ ፍትህ ልምዶችን በጥቃቅን እና በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ አለብን” በማለት አብራርተዋል።

የተሐድሶ ፍትህ እያንዳንዱ ሰው በተፈጥሮ ክብር እንዳለው እና በእነሱ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ሂደቶች እና ስርዓቶች አካል የመሆን መብት እንዳለው በመገንዘብ ከካቶሊክ ማህበራዊ አስተምህሮዎች ጋር እንደሚጣጣም ያስታወሱት ብፁዕነታቸው፥ ጉዳቱን ለመጠገን እና የተበላሹ ግንኙነቶችን መልሶ የመገንባት መንገዶችን በማቅረብ፥ የተሃድሶ ፍትህ ሰዎች እና ማህበረሰቦች የጥቃት ቁስሎችን እንዲፈውሱ እና ካቶሊኮች እምነታቸውን እንዲኖሩ ለመርዳት ያስችላል ብለዋል።

የተሃድሶ ፍትህ ልምምዶች ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የጐጂውን ድርጊት ተፅእኖ እንዲረዱ እና ነገሮችን ለማስተካከል አስፈላጊውን ነገር እንዲያደርጉ እድሎችን እንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን፥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማስታረቅ መንገድ ምሳሌ የሚሆን የፍትህ አቀራረብ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

በእርግጥም በመካከላችን በተለይም ከባድ ጉዳቶችን ተከትሎ ሰላምን ለማጎልበት የተሃድሶ ፍትህ አንዱ ተጨባጭ መንገድ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ካቶሊኮች እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ይህንን የፍትህ ራዕይ በአብያተ ክርስቲያናችን፣ በአገልግሎታችን እና በማህበረሰባችን ውስጥ ሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ የራሳቸውን ሚና መጫወት እንደሚችሉ እና በዚህ ጥልቅ ክፍፍል፣ መገለል እና አድልዎ በነገሠበት በአሁኑ ወቅት ይህ መልዕክት እና የድርጊት ጥሪ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል።

የተሃድሶ ፍትህን መለማመድ
የካቶሊክ ማህበረሰቦች ታሪካዊ ኢፍትሃዊነትን ለመለወጥ፣ በማህበረሰቦች ውስጥ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች እና እስራት ምላሽ ለመስጠት እና በአካባቢ እና በሀገረ ስብከት ደረጃ ያለውን የመከፋፈል ቁስሎችን ለመፈወስ እንደ ተግባራዊ መሳሪያ ሆኖ አሜሪካ ውስጥ የተሃድሶ ልምዶችን በተለያዩ መንገዶች እየተቀበሉ እንደሆነ የተመላከተ ሲሆን፥ ጉዳቱን ወደነበረበት መመለስ በተሻለ ሁኔታ በተለያዩ አገላለጾች እና መጠኖች የሚመጡ እውነተኛ ምሳሌዎችን መረዳት እንደሚቻል ተገልጿል።

ጥቅምት ወር ላይ ‘የዘላለማዊ አምልኮ ፍራንቺስካውያን እህቶች’ ማህበር የኦጂብዌ ብሔር አካል ወደሆነው የላክ ዱ ፍላምቤው ጎሳ መሬት ላይ የተመለሱ ሲሆን፥ መሬቱ ወደ ተወላጁ ማህበረሰብ የተመለሰው እህቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የጎሳ መሪዎችን ካነጋገሩ ከሁለት ዓመታት በኋላ እንደሆነ እንዲሁም የሕንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የተጫወተውን ሚና ጨምሮ የጉባኤውን ታሪክ ለመረዳት ከጉባኤው የአምስት ዓመት ጉዞ በኋላ እንደሆነ ተነግሯል።

የላክ ዱ ፍላምቤው ጎሳ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ከ3,400 በላይ አባላት ያሉት በፌዴራል ደረጃ እውቅና ያለው ጎሳ ሲሆን፥ ይህ ጎሳ እ.አ.አ. በ 1854 ዓ.ም. በተካሄደ ስምምነት የተቋቋመ እንደሆነ እና ከ 1745 ጀምሮ ይህንን አካባቢ ተቆጣጥሮ መቆየቱ ይነገራል። እነዚህ ጎሳዎች በቶርችስ ሪዞርት ካሲኖ ሐይቅ አከባቢ እንደሚንቀሳቀሱ እና በሉዓላዊነት፣ በተፈጥሮ ሀብቶች እና በማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ እንደሚያተኩሩ ይነገራል።

የጎሳው ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆን ዲ እንደተናገሩት ይህ ጉዳይ መሬትን ከማደስ በላይ እንደሆነ ገልጸው፥ ሚዛንን፣ ክብርን እና የቀድሞ አባቶቻቸው ይሄዱበት ከነበሩት ቦታዎች ጋር ያላቸውን የተቀደሰ ግንኙነት ወደነበረበት መመለስ እንደሆነ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባሉ በርካታ ከተሞች ውስጥ የካቶሊክ አቢያተ ክርስቲያናት “አንድ ቁምስና አንድ እስረኛ” በሚል ፕሮግራም ከማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ ወደ ማህበረሰባቸው የተቀላቀሉ ሰዎችን ለማገዝ እና ግንኙነቶችን ለመፍጠር የተሃድሶ ፍትህ ሞዴል እንደሚጠቀሙ የተነገረ ሲሆን፥ በሁለት ዓመታት ጉዞ ውስጥ ካህናትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች የተካተቱበት ቡድን ከአንድ ቁምስና ውስጥ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት ከማረሚያ ቤት ከወጣ አንድ ግለሰብ ጋር የተለያዩ ግንኙነቶችን እንደሚገነቡ ተነግሯል።

በሀገረ ስብከቱ እና በቁምስና ደረጃ አንዳንዶች በመንፈስ የሚመሩ ውይይቶች ተሳታፊዎቹ በግልፅ የሚካፈሉበት እና በጥልቅ የሚያዳምጡበት የጥበብ ሂደት የሚባል የተሃድሶ ልምምድ የሚያካሂዱ ሲሆን፥ ሂደቱ የሲኖዶሳዊነት ዓላማዎችን ብቻ የሚያካትት ሳይሆን፥ ካቶሊኮች አስቸጋሪ ርዕሰ ጉዳዮችን እና የፍትሕ መጓደል ጉዳዮችን “ያለ ምንም መሳሪያ እና ትጥቅ” መግባባት እና የበለጠ ሰላም የተሞላበት ግንኙነት እንዲፈጥሩ የሚጋብዝ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲኖዶሳዊነትን በዚህ አካሄድ ስትተገብር እንደነበርም ተገልጿል።

ሲኖዶሳዊነትም ሆነ የተሃድሶ ፍትሕ ልምምዶች በቁስሎች እና በመከፋፈል መካከል አብሮ የመጓዝ ራዕይን እና ሂደትን የሚያጠቃልል ሲሆን፥ ሁለቱም ዓላማቸው ጥልቅ የሆነ ማዳመጥን፣ ትክክለኛ ውይይትን እና መሰረታዊ እውነትን የመናገር ኃይልን በመጠቀም ወደ ሕብረት መጓዝን፥ በመጨረሻም የፈውስ መንገድን ለማብራት እንደሆነ ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለሰላም እና ለሲኖዶሳዊ አቀራረብ ያላቸው ጠንካራ ቁርጠኝነት በጣም የሚያበረታታ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህ አግባብ ቤተክርስቲያናችን እንዲሁም እያንዳንዳችን የተሃድሶ ልምምዶችን እና አቀራረቦችን ወደ ቁምስናዎቻችን፣ አገልግሎታችን እና ማህበረሰባችን ማምጣት እንችላለን የተባለ ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያናችን ሰላም እንዲሰፍን ልዩነቶችን የምናስተካክልበት እና ትስስሮችን የምናጠናክርበትን መንገድ ትፈልጋለች ተብሏል።

* የካቶሊክ ሞቢላይዚንግ ኔትወርክ የሞት ቅጣትን ለማስቆም እና የተሃድሶ ፍትህ የፈውስ ልምዶችን ለማራመድ የሚሰራ የአሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ድርጅት እንደሆነ ይታወቃል።

03 Feb 2026, 13:45