የፊሊፒንስ ካቶሊኮች የዐቢይ ጾምን ለመጀመር 'አሽ ወንስዴይ' ወይም አመድ የመቀባት ሥነ ስርዓትን ሲያከብሩ የሚያሳይ የማህደር ምስል የፊሊፒንስ ካቶሊኮች የዐቢይ ጾምን ለመጀመር 'አሽ ወንስዴይ' ወይም አመድ የመቀባት ሥነ ስርዓትን ሲያከብሩ የሚያሳይ የማህደር ምስል   (ANSA)

የፊሊፒንስ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾም እና ረመዳን በተመሳሳይ ቀን በሚጀመርበት በዚህ ዓመት አንድነትን ማጎልበት እንደሚገባ ገለጸች

የሙስሊሙ ማህበረሰብ የፆም ወር የሆነው ረመዳን እና ዐቢይ ጾም በተመሳሳይ ቀን እንደሚጀመር የታወቀ ሲሆን፥ በፊሊፒንስ የሚገኙ የቤተክርስቲያን መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ የፆም ወቅት ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ጸሎትን፣ መተሳሰብን እና የጋራ መግባባትን ለማጠናከር እንደ መልካም አጋጣሚ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ረመዳን እና ዐቢይ ፆም በዚህ ዓመት በተመሳሳይ ቀን በሚጀመሩበት በዚህ አጋጣሚ፥ በፊሊፒንስ የሚገኙ የካቶሊክ እና የሙስሊም ማህበረሰቦች በዚህ ወቅት የጋራ የጸሎት፣ የፆም እና የአምልኮ ወቅት እንዲያሳልፉ መጋበዛቸው ተነግሯል።

ረመዳን ቁርዓን በመልአኩ ጂብሪል አማካኝነት ለነቢዩ መሐመድ የተገለጠበት ወር እንደሆነ እና በሂጅራ አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር ላይ የሚውል፣ ሙስሊሞች ለ29 ወይም 30 ቀናት ከፀሐይ መውጫ እስከ መግቢያ በመጾም፣ በመጸለይና ቁርአንን በመቅራት የሚያሳልፉት ወር እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ ዐብይ ጾም ደግሞ ካቶሊኮችን ጨምሮ አንዳንድ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር፣ ሞት እና ትንሣኤ መታሰቢያ የሚያሳልፉት የፆም ጊዜያት እንደሆነ ይታወቃል።

ረመዳን የሚጀመረው የጨረቃን ሁኔታ የማየቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የካቲት 10 አመሻሽ ላይ ቢሆንም፣ የመጀመሪያው ሙሉ የጾም ቀን የሚጀመረው ግን የካቲት 11 ረቡዕ ዕለት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ካቶሊኮች ‘አሽ ወንስዴይ’ ተብሎ በሚከበረው አመድ በግንባር ላይ የመቀባት ሥነ ስርዓት አድርገው የዐቢይ ጾምን የሚጀምሩበት ቀን እንደሆነም ተነግሯል።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎቹ እንደገለጹት ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች አብረው በሰላም በሚኖሩባቸው ሃገራት፣ ይህ ክስተት ያልተለመደ እና ትርጉም ያለው አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰው፥ “መሐሪ እና ሩህሩህ” ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር በጋራ ለመጸለይ እና በጋራ ለመራመድ የተቀደሰ ጊዜ መሆኑን አመላክተዋል።

በጸጋ የተሞላ ግጥምጥሞሽ 
ከደቡባዊ ፊሊፒንስ የመጡት፣ የፊሊፒንስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የሃይማኖታዊ ውይይት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የሆኑት የኪዳፓዋን ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጆሴ ኮሊን ባጋፎሮ የዚህን መገጣጠም መንፈሳዊ ጠቀሜታ በማጉላት ክስተቱ ጸጋ እንደሆነ ጠቅሰው፥ በእነዚህ ጊዜያቶች ተረጋግተን እራሳችንን እንድናስተውል፣ ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ እና በእምነት አብረን እንድንጓዝ ምክራቸውን ለግሰዋል።

“በእነዚህ የተቀደሱ ወቅቶች ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የጸሎት፣ የጾም፣ የንስሐ እና የልግስና ጊዜን ያሳልፋሉ” ያሉት ጳጳሱ፥ ልባችንን ወደ መሐሪው አምላካችን መልሰን እንደ ወንድማማች እና እህትማማች መኖራችችን እንቀጥላለን ያሉ ሲሆን፥ “ቅዱሳን መጻህፍቶቻችን ወደ ሰላም እንደሚጠሩን ጠቁመው፥ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ቁጥር 9 ላይ ያለውን “የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው” የሚለውን እና ቁርዓን ላይ የተጠቀሰውን እግዚአብሔር ‘ሁሉንም ሰው ወደ ሰላም ይጋብዛል’ የሚለውን ጥቅስ በማስታወስ ተናግረዋል።

ጾም፣ ርኅራኄ እና አገልግሎት
ብፁዕ አቡነ ባጋፎሮ ረመዳን እና ዐቢይ ጾም ትሁፊታዊ የጸሎት፣ የንስሐ፣ የጾም እና የልግስና ወቅቶች እንደሆነ ገልጸው፥ ልብን የሚያድሱ እንዲሁም እንደ ወንድም እና እህት እንድንኖር ጥሪ የሚያደርጉልን ናቸው ብለዋል።

“ጾም የስቃይን ስሜት እንድንረዳ ልባችንን የሚከፍት እና ርህራሄ እንዲኖረን ያደርጋል” ያሉት ጳጳሱ፥ እግዚአብሔርን መውደዳችን የሚረጋገጠው ባልንጀራችንን እንደራሳችን ስንወድ፥ በተለይ ድሆችን እና የተረሱትን ስንወድ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሰላም፣ ፍጥረት እና ወንድማማችነት
ብፁዕ አቡነ ባጋፎሮ ሰላም ከእግዚአብሔር፣ ከሌሎች ሰዎች እና ከፍጥረታት ጋር ባለን ትክክለኛ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፥ ሰላም ከጦርነት አለመኖርም በላይ እንደሆነ ጠቅሰው፥ “የምድር ጩኸት እና የድሆች ጩኸት አንድ ናቸው ብለዋል።
ይህም በመሆኑ ምክንያት አካባቢን መንከባከብ ለሰላምና ለማህበራዊ መግባባት የመስራት ወሳኝ ገጽታ መሆኑን አስረድተው፥ “የሰው ልጅ ወንድማማችነትን እና ማህበራዊ ወዳጅነትን” ለሰላማዊ አብሮ የመኖር መሰረት አድርጎ የሚያበረታታውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክት በሆነው ‘ፍራቴሊ ቱቲ’ ላይ ያስተማሩትን ትምህርት አስታውሰዋል።

ብፁዕ አቡነ ባጋፎሮ አክለውም ብፁዕነታቸው አንድ ላይ ለመኖር የተፈጠርን እንጂ እርስ በርሳችን እንድንጣላ የተፈጠርን አለመሆኑን እያሳሰቡን እንደሆነ ጠቁመው፥ ማንኛውም ሰው ሊገለል ወይም ወደ ኋላ እንዲቀር አልተፈጠረም ብለዋል።

በ ‘አላይ ካፕዋ’ በኩል የተገለጸ እምነት
ብፁዕ አቡነ ባጋፎሮ በፊሊፒንስ ማህበረሰብ ዘንድ በዐቢይ ጾም ወቅት የሚፈጸመውን ‘አላይ ካፕዋ’ ተብሎ የሚጠራውን ለሌሎች የመስጠት ልማድን በመጥቀስ የጸሎት እና የመሥዋዕትን ማኅበራዊ ገጽታ አጉልተው፥ በዚህ ልማድ ውስጥ “ጸሎት አገልግሎት እንደሚሆን እና መስዋዕትነት ደግሞ በድህነት፣ በግጭት፣ በአደጋ እና በስነ ምህዳር ለውጥ ለተጎዱ ማህበረሰቦች ተስፋ እንደሚሆን አብራርተዋል።

በዚህ መልኩ ዐቢይ ጾም እና ረመዳን የግል መንፈሳዊ ጉዞዎች ብቻ ሳይሆኑ ለአደጋ የተጋለጡትን ለማንሳት የጋራ ቃል ኪዳን ይሆናሉ ብለዋል።

12 Feb 2026, 14:24