የፊሊፒንስ ጳጳሳት በሀገረ ስብከት ደረጃ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የፊሊፒንስ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ (CBCP) ጥር 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተደረገውን ብሔራዊ የጸሎት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቅረፍ የተጠናከረ የቤተክርስቲያን መዋቅራዊ አደረጃጀት እንዲደረግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው ሀገሪቱ ህገወጥ ወታደራዊ ምልመላ፣ የግዳጅ ሥራ፣ ፆታዊ ብዝበዛ እና በተለየ ሁኔታ ህጻናትን የሚያካትት የድህረ ገጽ ጥቃትን ጨምሮ በተለያዩ ሰብዓዊ ብዝበዛዎች እየተሰቃየች እንደሆነች ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በተለይ በከተሞች አካባቢ በርካታ ፊሊፒናውያንን የሚጎዳ “ከባድ እና ቀጣይነት ያለው አሳሳቢ” ተግባር እንደሆነ ገልጸው፥ ይሄንን ችግር ለመቅረፍ በቤተክርስቲያኑ እና በመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ጠንካራ ትብብር እንዲኖር አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ያወጣውን መረጃ የጠቀሰው መግለጫው፥ ጥናቱ እንደሚያመለክተው በፊሊፒንስ ውስጥ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ ከሚሆኑት ውስጥ ትናንሽ ሴት ልጆችን በማስከተል አብዛኛዎቹ አዋቂ ሴቶች መሆናቸውን ያመላከተ ሲሆን፥ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ጉዳዮች የሚከሰቱት በሜትሮ ማኒላ እና በሌሎች የከተማ ማዕከሎች እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የዲጂታል አደጋ
የዲጂታል መድረኮች መስፋፋት ሁኔታውን እንዳባባሰው የጠቆመው መግለጫው፥ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ሃሰተኛ የቀጥታ ድህረ ገጽ ምልመላ ዘዴዎችን በመጠቀም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተስፋዎችን እየሰጡ እንደሚያጭበረብሩ ተገልጿል።
ብፁዓን ጳጳሳቱ ድህነት፣ የትምህርት እጦት፣ የትጥቅ ግጭት እና ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች ለሕገወጥ ዝውውር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመው፥ እነዚህ ሁኔታዎች ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት የሚፈልጉ ሰዎችን በሚያጠምዱ የኦንላይን ቻናሎች ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለዋል።
“ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ማኅበራዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ ከልብ መለወጥን እና የአሰራር ሥርዓትን መለወጥ የሚጠይቅ ጥልቅ የሞራል ስጋት ነው” ያሉት ብፁዓን ጳጳሳቱ፥ ብዝበዛው እንዲቀጥል የሚፈቅዱትን ተጋላጭ እና ፈታኝ መዋቅሮችን ለመጠበቅ ቤተክርስቲያን ያለባትን ሃላፊነት የጠቆሙ ሲሆን፥ ለቤተክርስቲያኗ ሃብት እና ሃዋሪያዊ ተልዕኮ ተስማሚ በሆኑ የሀገረ ስብከቶች ተነሳሽነትን ጨምሮ ሀገራዊ የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጥረቶችን ለመደገፍ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሀገረ ስብከቶች እርምጃ
የፊሊፒንስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የስደተኞች እና አርብቶ አደር ሃዋሪያዊ አገልግሎት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የሆኑት የፖርቶ ፕሪንሰስ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሶቅራጥስ ሜሢዮና በተለየ ሁኔታ በሰጡት መግለጫ ሀገረ ስብከቶች ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቃወሙ የሀገረ ስብከት ኮሚቴዎችን ማቋቋም እና ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበው፥ እነዚህ ኮሚቴዎች በመላ ሀገሪቱ ለሚደረገው ህገወጥ ዝውውር የተቀናጀ ሃዋሪያዊ እና ተቋማዊ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዙም ተናግረዋል።
እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ 12 የሚጠጉ የሀገረ ስብከቱ ኮሚቴዎች መቋቋማቸው የተጠቀሰ ሲሆን፥ ብፁዕ አቡነ ሜሲዮና ከዚህም በተጨማሪ ቁምስናዎች የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ግንዛቤዎችን ከሃዋሪያዊ ሥራ ፕሮግራሞቻቸው ጋር እንዲያዋህዱ በማበረታታት፥ ቁምስናዎቹ “የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የትምህርት እና የጥበቃ ቦታዎች” እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ዓለም አቀፍ ቀን
የፊሊፒንስ ብፁዓን ጳጳሳት ይሄንን ጥሪ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ጠባቂ በሆነው የቅዱስ ጆሴፊን ባኪታ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ እንዲከበር ባሳዩት ተነሳሽነት የተጀመረው እና በየዓመቱ በጎረጎሳዊያኑ የካቲት 8 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የጸሎት ቀን በፊት ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሰውን ልጅ ክብር በእጅጉ የሚጥስ “መቅሰፍት” ሲሉ ደጋግመው መግለፃቸው ይታወሳል።