በኬንያ የሚገኙ ገዳማዊያት እህቶች ቤተሰቦችን የማደራጀት እና ልብን በፍቅር የማዳን ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
‘የማርያም ሴት ልጆች ጉብኝት’ የተሰኘው እና በኬንያ የሚገኘው የሀገረ ስብከት ጉባኤ የተሰበሩ ልቦችን ለመፈወስ እና ተስፋ ለሌላቸው ሰዎች ተስፋን ለመመለስ ህይወታቸውን በመስጠት መጠነ ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፥ እህት ጃኩሊን ጊትሪ እንደ ገዳማዊት እህት ሆነው እንዲያገለግሉ በተላኩበት ሰዎች ፊት በሚያቀርቡት አገልግሎት የርህራሄ እና የጽናት ምልክት ሆነው መቆማቸው ተገልጿል።
አገልግሎታቸው
እ.አ.አ. በ 2020 ዓ.ም. በኬንያ በሚገኘው የኪሱሙ ሃገረ ስብከት ውስጥ በርህራሄ ላይ የተመሰረተ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ማህበራቸው የቤተሰብ መንፈሳዊ ተሃድሶ ላይ የሚያተኩር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት በርካታ ቤተሰቦች ከብዙ ተግዳሮቶች ጋር እየታገሉ መሆናቸውን በመረዳት፥ በተለይም ለፍቺ እና በቤተሰብ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ የተወሳሰቡ የጭንቀት ችግሮች ጋር እየታገሉ መሆናቸውን በመረዳት በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሚገኝ ተገልጿል።
“አብዛኛዎቹ ችግሮች በመንፈሳዊ ባዶነት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ደርሰንበታል” ያሉት እህት ጃኩሊን፥ በዚህም መሰረት ቤተሰቦችን ከሥረ መሰረቱ ለማገልገል የተጠሩ ሆነው እንደሚሰማቸው ገልጸው፥ ጉባኤያቸው በምክር፣ በማህበራዊ እና በሃዋሪያዊ ሥራዎች ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ተልዕኮ እና ጥሪ
የምክር እና መንፈሳዊ መመሪያ በመስጠት እንዲሁም ያለመታከት በመስራት በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት በጭንቀት ውስጥ የሚገኙ ከሁሉም የሕይወት ዘርፎች የተውጣጡ ሰዎች ጋር በመገናኘት የተለያዩ አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ የተናገሩት እህት ጃኩሊን፥ ከዚህም በተጨማሪ ለወጣቶች እና አልፎ ተርፎም እገዛ የሚያስፈልጋቸው ገዳማዊያት እህቶች እና ካህናት ክብራቸውን እና ውስጣዊ ሰላማቸውን መልሰው እንዲያገኙ በአገልግሎታቸው ጥረት እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።
በርካታ ሰዎች የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን ይዘው እንደሚመጡ እና አንዳንዶቹን መርዳት ከባድ እንደሆነ የጠቆሙት እህት ጃኩሊን፥ በዚህም ምክንያት ጸሎት እንደሚያደርጉ እና እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እንደተቀበለ ገልጸው፥ ተልዕኮዋቸውን በተሳካ ሁኔታ አጠናክረው ለመቀጠል በግል እና በቡድን የማማከር ዕውቀታቸውን ለማዳበር የድህረ ምረቃ ትምህርት ለመማር መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
አብሮ መጓዝ እና መልሶ ማቋቋም
አገልግሎታቸው የበርካታ ሰዎችን ህይወት የነካ መሆኑ እና የእራሳቸውም ህይወት እንደተቀየረ የሚናገሩት ሲስተር ጃኩሊን፥ በህይወታቸው ላይ ጥልቅ ምልክት ጥለው ያለፉትን ሁለት ክስተቶች መቼም እንደማይረሱት የገለጹ ሲሆን፥ በአገልግሎታቸው ወቅት አንዲት እናት በባለቤቷ ከፍተኛ ስቃይ እንደሚደርስባት እና በኋላ ላይ ነፍሰ ጡር እያለች ከባሏ ጋር ተፋታ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሆና ወደ እርሳቸው የመጣችበትን አጋጣሚ አስታውሰው፥ ምንም አይነት ችግሮች ቢያጋጥማትም እሷን በማበረታታት እና የህይወትን ትርጉም እንድታገኝ በመርዳት ከሴቲቱ ጋር እንደተጓዙ ገልጸዋል።
“እንደገና ራሷን ችላ እስከምትቆም ድረስ አብረን ተጉዘናል” ያሉት እህት ጃኩሊን፥ በአሁኑ ወቅት ይህች እናት መንትያ ልጆች እንዳገኘች እና በጣም ደስተኛ እንደሆነች፣ እንዲሁም ሥራ አግኝታ ሶስት ልጆቿን መንከባከብ መቻሏን በማየታቸው ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ሌላኛው ጉዳይ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብታ ስለነበረች አንዲት ገዳማዊት እህት እንደሆነ ያስታወሱት እህት ጃኩሊን፥ ገዳማዊያቱ ባደረጉላት እንክብካቤ ቀስ ብላ እንዳገገመች እና በአሁኑ ወቅት በጣም ንቁ ሆና እያገለገለች እንደሆነ ጠቁመዋል።
“ሰዎች መጥፎ እንዳልሆኑ ተምሬያለሁ” ያሉት እህት ጃኩሊን፥ እንደነዚህ ያሉ ታሪኮች ሰዎች በፍቅር እና በትዕግስት ሲታከሙ መፈወስ እንደሚቻል ያመላክታሉ ያሉ ሲሆን፥ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የአስተዳደጋቸው፣ የልማዳቸው ወይም የአካባቢያቸው ሰለባ እንደሚሆኑና ይህም በሰዎች ላይ እንድፈርድ ሳይሆን እንድጸልይ አስተምሮኛል በማለት አብራርተዋል።
ግብአቶች እና ግላዊነት
እህት ጃኩሊን በአገልግሎታቸው ደስተኛ ቢሆኑም፥ እጅግ በጣም ብዙ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟቸው አስታውሰው፥ አንዳንድ ጉዳዮች የቅርብ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው እና የደንበኞቻቸውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የሚያስችል እና በቅርብ ክትትል ለማድረግ ማቆያ ቤት ማጣታቸውን የጠቆሙ ሲሆን፥ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ብዙ ጊዜ እንደሚከሰቱ እና እነዚህን ሁኔታዎችን ማስተናገድ ባለመቻላቸው የሚሰማቸውን ሃዘን እና ጭንቀት አመላክተዋል።
የእርሳቸው ህልም ከስሜታዊ ወይም ስነልቦናዊ ቁስሎች ጋር የሚታገሉ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ እና አጠቃላይ እንክብካቤ የሚያገኙበት አስተማማኝ የሆነ የቤተሰብ ማገገሚያ ማዕከልን መገንባት እንደሆነ የተናገሩት እህት ጃኩሊን፥ ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ ለቤተሰቦች የስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቁመው፥ በርካታ ሰዎች ምንም ዓይነት የመከላከል እና ቅድመ ጥንቃቄ ግንዛቤዎች ስለሌላቸው በመንፈስ ጭንቀት ውስጥ እንደሚወድቁ እና እንደ አንድ ጉባኤ ድልድይ በመሆን ይህንን መለወጥ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
እህት ጃኩሊን በአገልግሎታቸው ውስጥ ከካህናት፣ ከገዳማዊያት እህቶች እና ከምእመናን ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ገልጸው፥ ሚስጥራዊነትን እና መከባበርን ለማረጋገጥ ለእያንዳንዱ ቡድን የተወሰኑ ቀናትን እንደሚያዘጋጁ እና ጉባኤያቸው በአሁኑ ጊዜ ሁለት የሰለጠኑ አማካሪዎች እንዳለው ጠቁመው፥ ከእነዚህ ባለሙያዎች ጋር በመሆን አንዳንድ ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ሆነው ሴሚናሮችን፣ ወርክሾፖችን እና የአንድ ለአንድ ክፍለ ጊዜዎችን እንደሚሰጡ ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የምክር አገልግሎት ለመስጠት በተለምዶ ‘ኮንቴይነር’ የሚባለውን አነስተኛ ቤት እንደሚጠቀሙ ገልጸው፥ ነገር ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር የተሻለ ቦታ እንደሚሰጣቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በአገልግሎት እና በትብብር ማደግ
“አገልግሎቴ የበለጠ አዛኝ ልብ እንዲኖረኝ እና የሰዎችን ህመም እንድመለከት ዓይኖቼን ከፈተልኝ” ያሉት እህት ጃኩሊን፥ ሁሉም ሰው ከተረዳ እና ከተደመጠ ርህሩህ የመሆን አቅም እንዳለው ማየታቸውን ገልጸው፥ ገዳማዊያት የሥራ ባልደረቦቻቸው እና ካህናት ሰዎችን የማዳመጥ ልማዱ እንዲኖራቸው በመማጸን፥ “የትም ብንሆን ካህናት፣ ገዳማዊያት ወንድሞች ወይም እህቶች ምክርን መቀበል አለብን” ያሉ ሲሆን፥ የሙያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመገኘት አገልግሎት እንደሆነ ጠቅሰው፥ ሰዎች እየተጎዱ ስለሆነ በችግሮቻቸው ወቅት ከእነሱ ጋር የሚጓዝ ሰው ያስፈልጋቸዋል በማለት አጠቃለዋል።