ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች በቺካጎዋ ሬት ፊልድ ከተማ መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች በቺካጎዋ ሬት ፊልድ ከተማ መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት   (2025 Getty Images)

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች ፕረዚዳንት ትራምፕ በለቀቁት የዘረኝነት ቪድዮ ምክንያት ዋይት ሀውስ ይቅርታ እንዲጠይቅ ጥሪ ማድረጋቸው ተነገረ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን እንደ ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳይ ይዘት ያለውን ዘረኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ቪድዮ ገጻቸው ላይ መለጠፋቸውን ተከትሎ የቺካጎው ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች የተሰማቸውን ‘ድንጋጤ’ እና ‘ቁጣ’ የሚገልጽ መግለጫ በጽሁፍ ማቅረባቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቺካጎ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአራት ቀናት በፊት ትሩዝ በተሰኘ የማህበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ በለጠፉት “ዘረኝነት” የተሞላበት ተንቀሳቃሽ ምስል ምክንያት ይቅርታ እንዲጠይቁ ጥሪ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ጥር 28፣ ሐሙስ አመሻሽ ላይ ፕሬዚዳንት ዶናልድ የለቀቁት 'ዘ ላየን ስሊፕስ ቱ ናይት' በሚል ሙዚቃ የታጀበው አጠቃላይ ቪድዮው 62 ሰከንድ ርዝማኔ ያለው ሲሆን፥ በቪድዮው መጨረሻ ላይ ባራክ እና ሚሼል ኦባማን እንደ ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳይ ክፍል ይታያል።

የዋይት ሀውስ የህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ካሮሊን ሌቪት ቪድዮው እንደተለቀቀ መጀመሪያ አከባቢ ተቺዎችን “ሐሰተኛ ቁጣ አታስተጋቡ” በማለት ቢያጣጥሉም፤ ውግዘቱ ሲበረታ ቪድዮው ከትራምፕ ትሩዝ ማህበራዊ ገጽ ላይ ከተለጠፈ ከአስራ ሁለት ሰዓታት በኋላ እንዲጠፋ ተወስኗል።

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በሰጡት መግለጫ “የሰውን ልጅ እንደ እንስሳ፥ ከሰውም ያነሰ አድርጎ መግለጽ አዲስ አይደለም” በማለት ገልጸው፥ ‘ወደ አሜሪካ የገቡት ተከታታይ የስደተኞች ትውልዶች በዚህ መልኩ ዝቅ ተደርገዋል’ ሲሉ አስታውሰዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በጽሁፍ መልክ ባወጡት መግለጫቸው ትራምፕ የለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምስል በዋይት ሀውስ ውስጥ እንዲህ ያለ አይን ያወጣ ዘረኝነት ያለፈ ተግባር ብቻ ሳይሆን አሁንም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ያሳያል ብለዋል።

ይቅርታ መጠየቅ
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “ምንም ስህተት አልሠራሁም፥ የቪድዮውን መጀመሪያ ክፍል ብቻ ካየሁት በኋላ ነው የቢሮዬ ሠራተኞች የለጠፉት፥ ኦባማዎችን በዚያ መንገድ የሚያሳይ ክፍል እንዳለው አላወቅኩም ነበር” በማለት ቢገልጹም፥ ይቅርታ ለመጠየቅ ግን ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተገልጿል።

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በመልዕክታቸው ፕሬዚዳንቱ ይቅርታ እንዲጠይቁ የጠየቁ ሲሆን፥ “ፕሬዝዳንቱ ሆን ብለው አስከፊ የሆነ ዘረኛ ምስሎችን የያዘውን መልዕክት በገፃቸው ላይ እንዲለጠፍ ካጸደቁት፥ ስህተታቸውን አምነው መቀበል እንደሚገባቸው የገለጹ ሲሆን፥ ፕረዚዳንቱ መጀመሪያ ላይ ሳያውቁት ቀርተው ከሆነ ሰራተኞቻቸው በቪድዮው ላይ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ‘የውሸት ቁጣ’ እንደሆነ አድርገው እንዲያስተባብሉ የፈቀዱበትን ምክንያት ማስረዳት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

“ድንጋጤያችን እና ቁጣችን እውነተኛ ነው” ያሉት ካርዲናል ኩፒች፥ ህዝቡን እና በተንቀሳቃሽ ምስሉ የተዋረዱ ሰዎችን በማያሻማ ሁኔታ ይቅርታ ከመጠየቅ በስተቀር ሌላ አማራጭ ነገር እንደሌለ በማስረዳት አጠቃለዋል።

11 Feb 2026, 14:48