ፈልግ

የ 2026 ለክርስቲያን አንድነት የጸሎት ሳምንት የ 2026 ለክርስቲያን አንድነት የጸሎት ሳምንት 

በክርስቲያናዊ አንድነት የጸሎት ሳምንት ላይ ‘አንድነት ማለት መደጋገፍ እንጂ የበታችነት ስሜት አይደለም' መባሉ ተነገረ

ስለ ክርስቲያናዊ አንድነት ለመጸለይ በተሰጠው ሳምንት ውስጥ በአርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አቢያተ ክርስቲያናት ህብረት ክፍል ዳይሬክተር ‘እውነተኛ አንድነት ማለት መደጋገፍ እንጂ የበታችነት ስሜት አይደለም’ ሲሉ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከመቶ አሥራ ስምንት ዓመታት በፊት በህይወቱ የመጨረሻ ዘመን ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተመለሰው የአንግሊካን ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ መስራች ‘ለክርስቲያናዊ አንድነት የጸሎት ሳምንት’ የሚለውን አሠራር ያስተዋወቀ ሲሆን፥ ከአንድ ዓመት በኋላ አባ ፖል ዋትሰን ይህንን ተነሳሽነት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ፒዮስ 10ኛ ቡራኬ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

የዘንድሮው ለክርስቲያናዊ አንድነት የጸሎት ሳምንት የአርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ካሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር እንደተዘጋጀ ተነግሯል።

በአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክርስቲያናዊ ህብረት ክፍል ዳይሬክተር አባ ጋሬጂን ሃምበርድዙምያን ከቫቲካን ዜና ባልደረባ አውግስቲን አስታ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ወደ አስፈላጊው ነገር የምንመለስበት ጊዜ” እንዴት እንደሆነ ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል።

ወደ መሰረታዊ ነገሮች መመለስ
አባ ሃምባርዱዙምያን እንደገለጹት የዚህ ሳምንት ፍሬ ሃሳብ “በአንድነት መጸለይ እና የእግዚአብሔርን ቃል አብረን መስማት፥ በአጠቃላይ የአንድ የክርስቶስ አካል መሆናችንን ማስታወስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ዳይሬክተሩ ይህ ማለት ለልዩነት ቦታ የለም ማለት እንዳልሆነ አጽንዖት ሰጥተው፥ ይልቁንም ለአንድነት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ይሄንንም በምሳሌ ሲያስረዱ፥ የራሳቸው ክርስቲያናዊ ማንነት ያላቸው እና የራሳቸው ብሔራዊ ዳራ ያላቸውን የአርመንንና ሌሎች የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናትን ሁኔታ አንስተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ አባ ሃምባርድዙምያን ዓለም አቀፉ የክርስቲያን ማህበረሰብ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚችል በአጽንዖት ገልጸዋል።

በመከራ ጊዜ ጸንቶ መገኘት
ዳይሬክተሩ የአርመንን ታሪክ በማስታወስ “አንድነት በፈተና የሚጠናከር” መሆኑን የሚያስተምር ጥሩ ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰው፥ በአርመን ያለችውን የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን በእምነት፣ በተስፋ እና በኅብረት እንዴት መጽናት እንዳለባት የተማረች እንደሆነች የገለጹ ሲሆን፥ እንዲህ ዓይነቱ ጽናት ለዓለም አቀፉ የክርስቲያን ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል እና የጋራ ክርስቲያናዊ ምሥክርነት መስጠት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

አባ ሃምባርድዙምያን አክለውም ይህ የጋራ ምስክርነት በተለይ በግጭት፣ በፍትህ እጦት እና ብዙዎች የሕይወትን ትርጉም ባጡበት የአሁኗ ዓለማችን በእጅጉ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ክርስቲያኖች በጸሎት መሰባሰብ ብዙ ሰዎች የህይወት ትርጉም እና ዓላማ እንዲኖራቸው ሊረዳቸው እንደሚችል አስታውሰዋል።

አንድነት ማለት በትክክል ምን ማለት ነው?
ካህኑ አንድነት ማለት የመሸነፍ እና የበታችነት ስሜት ሳይሆን እርስ በርስ መደጋገፍ ማለት እንደሆነ ያመላከቱ ሲሆን፥ ክርስቲያናዊ አንድነት እርስ በርስ በሚደጋገፉ እኩል በሆኑ ክርስቲያኖች መካከል ሊኖር እንደሚችል ገልጸው፥ ነገር ግን የዚህ ዓይነት አንድነት ሊፈጠር የሚችለው በቁርጠኝነት ብቻ እንደሆነ እና ይህም “አማራጭ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።

ለአንድነት የተደረጉ ተነሳሽነቶች 
ካህኑ እንደገለጹት በዚህ ለጸሎት እና ለአንድነት በተሰጠው ሳምንት እንደ ዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ካሉ ድርጅቶች ጋር ወንድማማችነት ፍቅር ያለው ትብብር ማድረግ አንዱ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህ ማለት “ከእያንዳንዱ ክርስቲያናዊ ቤተ ክርስቲያን ግንዛቤ ጋር የሚቃረን አንድ ዓይነት ወጥነት ለመፍጠር መሞከር” እንዳልሆነ አበክረው በመግለጽ፥ ግቡ የእያንዳንዱን አብያተ ክርስቲያናት ልዩ ገጽታዎች ማስወገድ ወይም ችላ ማለት መሆን የለበትም ብለዋል።

ይልቁንም አባ ሃምባርድዙምያን “በተለይ የዘመናዊውን ዓለም ተግዳሮቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ወንድማማችነት እና የፍቅር መንፈስ ማጠናከር እና መቀጠል” የሚቻልባቸውን መንገዶች ጠቁመዋል።

እንደ የክርስቲያን አንድነት የጸሎት ሳምንት ያሉ ተነሳሽነቶች አብያተ ክርስቲያናት እንዲሰባሰቡ እና እንዲያድጉ እድል እንደሚሰጡ የገለጹት ካህኑ፥ ክርስቲያን ወንድሞች እና እህቶች በአንድ ወግ ማለትም አንዳንድ ጊዜ የጋራ የሆነ ጸሎት በሌላቸው አውድ ውስጥ እንዴት አንድ ሆነው እንደሚጸልዩ ማየታቸው በጣም የሚያጽናና እንደነበር ጠቁመው፥ ነገር ግን ሁሉንም እንደ አንድ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አንድ የሚያደርጋቸውና የሚያስተሳስራቸው ጥልቅ ስሜትና መንፈሳዊነት መኖሩን ገልጸዋል።

23 Jan 2026, 14:53