2026.01.12 VENEZUELA

የቬነዙዌላ ብጹዓን ጳጳሳት ትምህርት ቤቶች የሰላም እና የፍትህ ቦታ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳሰቡ

በቅርቡ በቬነዙዌላ የተከሰተውን አለመረጋጋት እና የፖለቲካ ለውጦችን ተከትሎ የአገሪቱ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ልጆችን እና መምህራን በፍትህ፣ በሰላም እና በዲሞክራሲ ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ ለመገንባት ተስፋ በማድረግ አዲሱን የትምህርት ዓመት እንዲጀምሩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቬነዙዌላ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አቡነ ካርሎስ ሄንሪኬ ኩሪኤል ሄሬራ፥ ሁሉም ልጆች፣ ጎረምሶች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የትምህርት ማኅበረሰብ አባላት በአገሪቱ ውስጥ መግባባትን ለማስፈን የጥናት እና የትምህርት መሣሪያዎችን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

በዚህ አዲስ የትምህርት ዓመት ወደ ትምህርት ቤቶቻችን ስንመለስ የቬነዙዌላ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን ለእያንዳንዱ መምህር፣ ተማሪ፣ ቤተሰብ እና ብሔራዊ የትምህርት ማኅበረሰብ በተስፋ የተሞላ ሰላምታ ለመላክ ይፈልጋል” ሲሉ አቡነ ካርሎስ ሄንሪኬ ኩሪኤል ሄሬራ ገልጸዋል።

አቡነ ካርሎስ ሄንሪኬ አክለውም፥ “የቬነዙዌላ ብጹዓን ጳጳሳት ትምህርት ቤቶች ሰላም እና ፍትህ የሚጠናከርባቸው ቦታዎች እንዲሆን ይፈልጋሉ” ብለው፥ ችግሮች ቢኖሩም ትምህርት ቤቶች ለፍትህ እሴቶች ባላቸው ቁርጠኝነት እና ህልውናችንን በሚመራ ነፃነት የእምነት ዘር የሚዘሩበት እጅግ የተቀደሰ ቦታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ብጹዕ አቡነ ካርሎስ ሄንሪኬ፥ ተማሪዎች እና መምህራን በሚወስዷቸው እያንዳንዱ እርምጃ እግዚአብሔር አብሮአቸው እንደሚጓዝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በተከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ላይ የተገለጠው ብርሃን በልባቸው እንዲበራ እና የትምህርት ዓመት ደስታ በወንጌላዊ ታማኝነት ለማገልገል ያላችሁን ብርታት እንዲያድስ” በማለት ጸሎት አቅርበዋል።

ብጹዕ አቡነ ካርሎስ ሄንሪኬ በጸሎታቸው፥ ቅዱስ ሆሴ ግሪጎሪዮ ሄርናንዴዝ ጥበብን እና የአገልግሎት ትህትናን እንዲሰጠን፣ እናት ካርመን ሬንዲልስ ማርቲኔዝም ሕይወትን በሚለውጥ ርህራሄ ማስተማርን እንድታስተምረን” ሲሉ ጸልየዋል።

ሰላምን ለመገንባት የቀረበ ጥሪ

የቬነዙዌላ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፥ ልጆች እና መምህራን በአገሪቱ ውስጥ ሰላምን ለመገንባት የሚያገለግሉ መሣሪያዎች እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ብጹዕ አቡነ ካርሎስ ሄንሪኬ በመጨረሻም፥ “የትምህርት ዓመት መጀመሪያ እርስ በርስ ለመደማመጥ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመረዳት፣ ለቬነዙዌላ መግባባትን እና ሰላምን ለመጠየቅ እና ትምህርት ቤቶቻችንን ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህ እና ለሰላም ግንባታ አስተማማኝ ቦታ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት የምናድስበት ሥፍራ ይሁኑ” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

13 Jan 2026, 15:53