ሦስት የአሜሪካ ብፁዓን ካርዲናሎች ‘የሃገሪቱ የውጭ ፖሊሲ የሰውን ክብርና የሃይማኖት ነፃነት ማክበር አለበት ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሦስቱ የአሜሪካ ብፁዓን ካርዲናሎች የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በሚመለከት ሰኞ ዕለት ልዩ የሆነ የጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን፥ የብፁዓን ካርዲናሎቹ መግለጫ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከአስር ቀናት በፊት ከቅድስት መንበር ዕውቅና ለተሰጣቸው የዲፕሎማቲክ ቡድኖች ካደረጉት ንግግር ላይ በርካታ ጭብጦችን ማንሳታቸው ተገልጿል።
መግለጫው የቺካጎ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች፣ የዋሽንግተን ሊቀ ጳጳስ በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሮበርት ማኬልሮይ እና የኒውዮርክ ሊቀ ጳጳስ በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆሴፍ ቶቢን የተፈረመበት ሲሆን፥ ብፁዓን ካርዲናሎቹ ዩናይትድ ስቴትስ በ 2026 ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ ሃገሪቷ በዓለም ላይ በምታደርጋቸው እርምጃዎች የሞራል መሠረቷ ወደ ጥልቅ እና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን አመላክተዋል።
ብፁዓን ካርዲናሎቹ በቅርቡ በቬንዙዌላ፣ ዩክሬን እና ግሪንላንድ የተከሰቱት ክስተቶች “ስለ ወታደራዊ ኃይል አጠቃቀም እና ስለ ሰላም ትርጉም መሠረታዊ ጥያቄዎችን ያስነሳሉ” ያሉ ሲሆን፥ የሃገራት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሉዓላዊ መብት አጉልተው በመግለጽ፥ ይህ መርህ አሁን ባለው የግጭት ጂኦፖለቲካ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደካማ መስሎ እንደሚታይ አስረድተዋል።
ሰላም ለሰው ልጅ ደህንነት ወሳኝ ነገር ቢሆንም፥ ለፍትሃዊ እና ለዘላቂ ሰላም የተደረጉ ጥረቶች ለወገናዊነት፣ አክራሪነት እና ለአጥፊ ፖሊሲዎች ተዳርገዋል ሲሉ ሦስቱ ካርዲናሎች የገለጹ ሲሆን፥ ሃገሪቷ በዓለም ዙሪያ ክፋትን በመጋፈጥ፣ በህይወት የመኖር መብትን እና ሰብአዊ ክብርን በማስጠበቅ እንዲሁም የሃይማኖት ነፃነትን በመደገፍ ረገድ ያላት የሞራል ሚና ፈተና ውስጥ መግባቱን አሳስበዋል።
ብፁዓን ካርዲናሎቹ ከዚህ ሁኔታ አንጻር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ዓለማችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ በማስመልከት ያደረጉት ንግግር ለዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ‘እውነተኛ የሞራል መሠረት’ እና ለአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ መልካም መንገድ እንደሚያቀርብ ገልጸው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ ለዲፕሎማቶቹ ባደረጉት ንግግር የባለብዙ ወገንተኝነት አሰራርን ድክመት እና ዲፕሎማሲው በተቃዋሚ ወገኖች መካከል ውይይት እና ስምምነትን ባለመፈለጉ የደረሰበትን ውድቀት በመጠቆም ማዘናቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው ‘ጦርነት እንደ ፋሽን ዳግመኛ መመለሱን እና ለጦርነት ያለው ከፍተኛ ፍላጎት ወይም ቅንዓት እየተስፋፋ መምጣቱን’ የጠቆሙ ሲሆን፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመሰረተው እና ሀገራት ሃይልን ተጠቅመው የሌሎችን ድንበር እንዳይጥሱ የሚከለክለው መርህ ሙሉ በሙሉ መጣሱን ገልጸው፥ ሰላም ከአሁን በኋላ እንደ ስጦታ እና በራሱ የሚፈለግ መልካም ነገር እንደማይታይ፥ ይልቁንም በአሁኑ ወቅት ሰላም የሚፈለገው የራስን የበላይነት ለማረጋገጥ እንደ ቅድመ ሁኔታ በጦር መሳሪያዎች አማካይነት እንደሆነ አስታውሰዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች፣ ማኬልሮይ እና ቶቢን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስለ ካቶሊክ አስተምህሮ የሰጡትን ማጣቀሻ አስታውሰው፥ ብፁዕነታቸው እነዚህ መብቶች ለሌሎች ሰብዓዊ መብቶች በጣም አስፈላጊ መሠረት ሆነው ስለሚያገለግሉ በሕይወት የመኖር መብትን መጠበቅ እንዳለባቸው መጠቆማቸውን አስታውሰዋል።
የበለጸጉ ሀገራት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር በመሆን በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርጉ የጠየቁት ብፁዓን ካርዲናሎቹ፥ ብፁዕነታቸው በርዕዮተ ዓለም ወይም በሃይማኖት ንጽህና ስም የኅሊና እና የእምነት ነፃነት መጣስ በመስፋፋቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ሦስቱ የአሜሪካ ብፁዓን ካርዲናሎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ላይ ያወጀውን “እውነተኛ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም” ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት በመግለጽ፥ ለሀገራቸው እውነተኛ ሥነ ምግባር የተላበሰ የውጭ ፖሊሲ እንዲኖር የጠየቁ ሲሆን፥ ‘ጦርነትን ለጠባብ ብሄራዊ ጥቅም ማስፈጸሚያ መሳሪያ አድርጎ መጠቀምን መተው እንደሚገባ እና ወታደራዊ እርምጃ በከባድ ሁኔታዎች ውስጥ እንደ የመጨረሻ አማራጭ ብቻ መታየት ያለበት እንጂ እንደ ብሄራዊ ፖሊሲ የተለመደ መሳሪያ መሆን እንደማይገባው በመምከር፥ “የሰው ልጅ የመኖር መብትን፣ የሃይማኖት ነፃነትን እና የሰብዓዊ ክብርን በዓለም ዙሪያ በተለይም በኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚያከብር እና የሚያራምድ የውጭ ፖሊሲ እንፈልጋለን” ብለዋል።
ሦስቱ ብፁዓን ካርዲናሎች በመግለጫቸው ማጠቃለያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ተግዳሮት በራሱ የሞራል መሰረት ላይ ያቆመውን ‘አክራሪነት፣ ወገንተኝነት እና ጠባብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍላጎቶችን’ ለማሸነፍ የሚያስችል ሚዛናዊ የሆነ ሃሳብ ለዩናይትድ ስቴትስ ማቅረባቸውን በማስታወስ አጠቃለዋል።
ዋናውን መግለጫ እዚህ ያንብቡ (Read the original statement here)