ምሥጢረ ጥምቀት
ወደ ክርስትና ሕይወት መግቢያ የሚሰጡ ስሞች ምንድ ናቸው ?
ይህ ምሥጢር ከሚከበርበት መሠረታዊ ሥነ ሥርዓት፣ የተነሣ ጥምቀት በመባል ይታወቃል። ማጥመቅ ማለት
ውሃ ውስጥ "መንከር" ማለት ነው። የተጠመቀ ሰው በክርስቶስ ሞት ውስጥ ይነከራል፣ ከእርሱም ጋር "አዲስ
ሕይወት ሆኖ ይነሣል" (2ኛ ቆሮ 5፡17)። ይህ ምሥጢር "የመታጠብና በመንፈስ ቅዱስ አዲስ መወለድ" በመባልም ይታወቃል (ቲቶ 3፡5)፣ የተጠመቀ ሰው "የብርሃን ልጅ" (ኤፌ 5፡8) ስለሚሆን "ክስተት" ተብሎም ይጠራል።
ምስጢረ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን አስቀድሞ የታየው እንዴት ነው?
በብሉይ ኪዳን ውስጥ ጥምቀት በልዩ ልዩ መንገዶች ተገልጾአል፡- ውሃ፣ የሕይወትና የሞት ምንጭ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በውሃ በዳነው በኖህ መርክብ ይመሰላል። እንደዚሁም እሥራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ባወጣው ቀይ ባሕርን በመሻገር ይገለፃል፤ የእስራኤልን ሕዝብ የዘለዓለማዊ ሕይወት ምሳሌ ወደ ሆነው ወደ ተስፋይቱ ምድር ያመጣውን የዮርዳኖስ ወንዝ መሻገርን ያመለክታል።
እነዚህን ምሳሌዎች ተፈፃሚ ያደረገው ማነው?
የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች ሁሉ የተፈጸሙት በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ይፋ ሕይወቱን በጀመረ ጊዜ በመጥምቁ ዮሐንስ አማካይነት በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ የጥምቀትና የቅዱስ ቁርባን ምልክቶች የሆኑት ደምና ውሃ ከተወጋው ጎኑ ፈሰሱ። ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ "እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛሙርቴ አድርጉአቸው" (ማቴ. 28፡19) የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው።
ቤተክርስቲያን ማጥመቅ የጀመረችው መቼና ለማን ነው ?
ቤተክርስቲያን፣ ከጴንጤቆስጤ ቀን ጀምሮ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምን ማንኛውም ሰው ጥምቀት መስጠት
ጀመረች።
የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ምን ያካትታል?
የዚህ ምሥጢር ዋና ሥርዓት የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን ስም እየጠሩ ዕጩ ተጠማቂን ውሃ ውስጥ መንከርን ወይም በራሱ ላይ ውሃ ማፍሰስን ያካትታል።
ምስጢረ ጥምቀት መቀበል የሚችለው ማነው ?
ያልተጠመቀ ማንኛውም ሰው ጥምቀት መቀበል ይችላል።
ቤተክርስቲያን ሕፃናትን የምታጠምቀው ለምንድ ነው ?
ቤተክርስቲያን ሕፃናትን የምታጠምቀው በአዳም ኃጢአት ስለተወለዱ ነው። ስለዚህ፣ ከሰይጣን ኃይል ነፃ መውጣትና ወደ እግዚአብሔር ልጆች የነፃነት መንግሥት መግባት ይኖርባቸዋል።
ከሚጠመቅ ሰው ምን ይጠበቃል ?
የሚጠመቅ ሰው ሁሉ እምነትን መግለጽ ይጠበቅበታል። ይህም ሊሆን የሚችለው አዋቂ ከሆነ በራሱ፣ ሕፃናት ከሆኑ ደግሞ በወላጆችና በቤተክርስቲያን በኩል ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የክርስትና አባት ወይም የክርስትና እናት እንዲሁም መላው ክርስቲያን ማህበረሰብ ተጠማቂውን ለጥምቀት የማዘጋጀትና በጥምቀት ጊዜ የተሰጠውን እምነትና ጸጋ የማዳበርና የመጠበቅ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው።
ማጥመቅ የሚችለውማ ነው ?
የጥምቀት መደበኛ አገልጋዮች ጳጳሳትና ካህናት ናቸው። በላቲን ቤተክርስቲያን ዲያቆንም ማጥመቅ ይችላል። አስፈላጊ ሲሆን፣ ዓላማው ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውን ለማድረግ ከሆነ፣ ማንኛውም ሰው ሊያጠምቅ ይችላል። ይህም የሚሆነው በተጠማቂው ራስ ላይ በማፍሰስና ለጥምቀት የተቀመጠውን ሥላሴአዊ ቃል በመድገም ማለትም "በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅሃለሁ" በማለት ነው።
ጥምቀት ለደኅንነት ያስፈልጋል ?
ጥምቀት ወንጌል ለተሰበከላቸውና ይህንን ምሥጢር ለመቀበል ችሎታው ለነበራቸው ሰዎች ደኅንነት አስፈላጊ ነው። ክርስቶስ ስለሁሉም ሰው ደኅንነት ስለሞተ ስለ እምነታቸው ያለ ጥምቀት የሞቱ ሰዎች ሊድኑ ይችላሉ፣ ይህም የደም ጥምቀት ይባላል። አዲስ ምእመናን እና ክርስቶስንና ቤተክርስቲያንን የማያውቁ እንኳ ቢሆኑ (በጸጋ ኃይል) እግዚአብሔርን በእውን የሚፈልጉና ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጥሩ ሰዎች ሁሉ ያለጥምቀት ሊድኑ ይችላሉ፣ ይህም የምኞት ጥምቀት በመባል ይታወቃል። ቤተክርስቲያን በሥርዓተ አምልኮዋ ያለ ጥምቀት የሚሞቱ ልጆችን ለእግዚአብሔር አደራ ትሰጣለች።
የጥምቀት ውጤቶች ምንድናቸው ?
ጥምቀት የአዳምን ኃጢአት፣ የግል ኃጢአትን በሙሉ እና በኃጢአት ምክንያት የሚመጣውን ቅጣት ሁሉ ያሰወግዳል። የተጠመቀውን ሰው በሚቀድስ ጸጋ ማለትም አንድን ሰው ከክርስቶስና ቤተክርስቲያኑ ጋር በሚያዋህድ የጽድቅ ጸጋ አማካይነት በቅድስት ሥላሴ መለኮታዊ ሕይወት ተሳታፊ ያደርገዋል። ሰውን በክርስቶስ ክህነት እንዲሳተፍና ከክርስቲያኖች ሁሉ ጋር አንድነት እንዲኖረው ያደርጋል። ነገረ መለኮታዊ ትሩፋቶችና የመንፈስ ቅዱስ ሰጦታዎችን ያስገኛል። የተጠመቀ ሰው ለዘላለም የክርስቶስ ወገን ይሆናል። በማይጠፋ የክርስቶስ ማሕተም ይታተማል።
በጥምቀት ጊዜ የሚሰጥ የክርስትና ስም ምን ትርጉም አለው ?
ስም ጠቀሜታ አለው፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን የሚያውቀን በስማችን ማለትም በግላዊ ሰውነታችን ነው። በጥምቀት አንድ ክርስቲያን በቤተክርስቲያን ውስጥ የራሱ ወይም የራስዋ ስም ይኖረዋል (ይኖራታል)። ስሙም ለተጠማቂው ሰው የቅድስና ምሳሌ የሚሆንና በእግዚአብሔር ፊት የመማለድ ብቃት ያለው (ያላት) የአንድ ቅዱስ ስም ቢሆን ይመረጣል።
ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካጸደቁት፣ በአጭሩ ከተጻፈው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ከዋናው ከላቲን ቅጂ ከተተረጎመው መጽሐፍ ከአንቀጽ 1213 -2167 ላይ የተወሰደ።