የታይላንድ ብፁዓን ጳጳሳት በባንኮክ በሚገኘው አስምሽን ካቴድራል ውስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር እ.አ.አ. ኅዳር 22 ቀን 2019 በተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የታይላንድ ብፁዓን ጳጳሳት በባንኮክ በሚገኘው አስምሽን ካቴድራል ውስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር እ.አ.አ. ኅዳር 22 ቀን 2019 በተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ  (Vatican Media)

የታይላንድ ብፁዓን ጳጳሳት ካቶሊኮች በመጪው ምርጫዎች ላይ የሥነ ምግባር ተምሳሌት ሆነው እንዲታዩ ጥሪ አደረጉ

የታይላንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ (CBCT) በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ካቶሊኮች በመጪው የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. በታይላንድ የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ በሃላፊነት እንዲመርጡ ሰሞኑን ባወጡት ሃዋሪያዊ ደብዳቤ ማሳሰባቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የታይላንድ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ለምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት እውነተኛ እና ፍትሃዊ የምርጫ ሂደትን በመጠበቅ ረገድ ምዕመናን ሥነ ምግባርን በማሳየት እና “ማህበራዊ ህሊናን” በመጠበቅ በኩል ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስታውሰዋል።

የታይላንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ዣቪየር ቪራ በአገር አቀፍ ደረጃ ለምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት ድምጽ መስጠት የዜጎች መብት ብቻ ሳይሆን በቤተክርስቲያኗ ማኅበራዊ አስተምህሮ ላይ የተመሰረተ የሞራል ኃላፊነት እንደሆነ አሳስበዋል።

“ድምጽ መስጠት ለጋራ ጥቅም የሞራል ግዴታ መሆኑን ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲገነዘቡ ቤተክርስቲያን ትጋብዛለች” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ቪራ፥ የመምረጥ መብትን መጠቀም ዝም ብሎ ህጋዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን ዜጎች በጋራ ለህብረተሰቡ ጥቅም ሲሉ ሊያሟሉት የሚገባ የሞራል መስፈርት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳሱ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ አስተምህሮን ጠቅሰው እንደተናገሩት፣ ዜጎች ግብር በመክፈል፣ አገርን በመጠበቅ፣ ድምጽ በመስጠት እና በመሳሰሉት ተጨባጭ ተግባራት ለጋራ ጥቅም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ምርጫን ችላ ማለት በህብረተሰቡ ውስጥ በሃላፊነት አለመሳተፍን ያሳያል ብለዋል።

የብፁዓን ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ ደብዳቤው ከምርጫው በፊት የምርጫ ዘመቻው እየጠነከረ በሚሄድበት ወቅት ለካቶሊክ መራጮች በታይላንድ የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያሉትን 500 መቀመጫዎች ለሚወስነው የምርጫ ሂደት መመሪያ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፥ አዲስ የሚመረጡ የምክር ቤት አባላት አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር የመሾም ስልጣን እንዳላቸው ተገልጿል።

እንደ የታይላንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ መልዕክት መሰረት ትክክለኛ የዲሞክራሲ ተሳትፎ በምርጫ ጣቢያው ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን፥ በምርጫ ሂደቱ ውስጥ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ የመሳተፍ ሂደትን መከታተልን፣ መመርመርን እና ትክክለኛ የስነ ምግባር አካሄድን መደገፍን እንደሚያካትት የጠቆመው መግለጫው፥ ከመምረጥ መታቀብ ከሥነ ምግባር አኳያ የሚፈቀደው ማንኛውም እጩ ዝቅተኛ የስነምግባር መስፈርቶችን የማያሟላ ከሆነ እና በልዩ ጉዳዮች ብቻ እንደሆነ አስረድቷል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ ዴሞክራሲን ወደ ሥርዓታዊ ሕጎች ዝቅ ማድረግ እንደማይገባ ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ ቪራ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ እውነተኛ ዴሞክራሲ የሕጎችና የመተዳደሪያ ደንቦች ውጤት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰብዓዊ ክብር፣ ሰብዓዊ መብቶች እና የጋራ ጥቅም የመሳሰሉ መሠረታዊ እሴቶችን ከመቀበል የመነጨ እንደሆነ ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው የቤተክርስቲያንን ማህበራዊ አስተምህሮ መመሪያን በመጥቀስ እነዚህ እሴቶች ከሌሉ ዲሞክራሲ “የተደበቀ አምባገነንነት” የመሆን ስጋት እንዳለበትና በመጨረሻም ህዝቡን የሚጨቁን መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የታይላንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ መልዕክት ካቶሊካዊያን መራጮች ሰብዓዊ ክብርን የሚያከብሩ፣ ከግል ወይም ከቡድን ጥቅም ይልቅ ለጋራ ጥቅም የሚያስቀድሙ እጩዎችን እንዲመርጡ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ለአካባቢው ማህበረሰቦች፣ በተለይም ለድሆች እና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እውነተኛ አሳቢነት ማሳየት እንደሚገባ ጠቁሟል።

የብፁዓን ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ መልዕክት ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ዘጸአት ምዕራፍ 18 ቁጥር 21 ላይ “ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መርጠህ በህዝብህ ላይ የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆች፣ የአስር አለቆች አድርገህ ሹም፥ እነርሱ እግዚያብሔርን የሚፈሩ፣ እምነት የሚጣልባቸው እና በጉቦም የማይደለሉ ሰዎች መሆን አለባቸው” የሚለውን ለሙሴ የተሰጠውን መመሪያ ሃሳብ በመጥቀስ፥ ህዝቡ ታማኝ መሪዎችን እንዲመርጥ መክረዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ እንዲህ ያለው አመራር ለግል ጥቅም ሳይሆን እንደ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሠረት ለአገልግሎት የሚውል የእግዚአብሔርን የሥልጣን ራዕይን ያንጸባርቃል ያሉ ሲሆን፥ ጳጳሳቱ ከዚህም በተጨማሪ ለፖለቲካ መሪዎችን እና ለመንግስት ባለስልጣናት በቀጥታ ባስተላለፉት መልዕክት የምርጫው ሂደት ላይ ታማኝነት እንዲሰፍን የበኩላቸውን ማድረግ እንደሚገባቸው ጠይቀዋል።

መግለጫው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ከቁጥር 11-12 ላይ “በትንሽ ነገር የታመነ ሰው በትልቅ ነገርም የታመነ ይሆናል፥ በትንሽ ነገር የማይታመን ሰው ግን በትልቅ ነገርም አይታመንም፥ ታዲያ የዚህን ዓለም ሃብት በማስተዳደር የማትታመኑ ከሆናችሁ እውነተኛውን ሃብትማ ማን አምኖ ይሰጣችኋል?” የሚለውን የጌታችን ኢየሱስን ክርስቶስን አስተምህሮ በመጥቀስ፥ ጥቃቅን የድምፅ ግዢ ወይም የምርጫ ማጭበርበር ተግባራት እንኳን ቢሆን አንድን አገር ሊያጠፋ የሚችል የሙስና ዘር እንደሚዘራ አስጠንቅቀዋል።

“የፖለቲካ ሙስና የህዝብ ክህደት እና ከፍተኛ የማህበራዊ ፍትህ ጥሰት ነው” ያሉት ብፁዓን ጳጳሳቱ፥ በታይላንድ የምርጫ ታሪክ ውስጥ ድምጽ መግዛትን እና የፖለቲካ አክራሪነት መስፋፋትን ጨምሮ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ተግዳሮቶችን በመገንዘብ፥ መጪው ምርጫዎች “ለእግዚአብሔር እና እርስ በርስ ላለን ፍቅር ማረጋገጫ” እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም ምዕመናን ጸሎት እንዲያደርጉ ጋብዘው፥ እግዚአብሔር ለሁሉም ዜጎች ጥበብን እና ማስተዋልን እንዲሰጥ በመመኘት ህዝቡ መልካም የሆኑ መሪዎችን እና ጤናማ ህዝባዊ ፖሊሲዎችን እንዲመርጥ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የተመረጡት ሰዎች በቅንነት እንዲያስተዳድሩና ሕዝቡን ወደ “እውነተኛ ሰላም፣ ፍትህ እና ወንድማማችነት” እንዲመሩ ጸሎት በማድረግ አጠቃለዋል።

29 Jan 2026, 13:32