ገዳማውያት ኬንያ ውስጥ ጎጂ ሱሶችን በመዋጋት ላይ እንደሚገኙ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ኬንያ ውስጥ የሚገኘው የ “ሆሊ ኢኖሰንትስ” ማዕከል በሜሩ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ሳሌሲየስ ሙጋምቢ እና ማዕከሉን የሚያስተዳድረው የ “ሆሊ ኢኖሰንትስ” እህቶች ማኅበር መሥራች በሆኑት እህት ቬሮኒካ ንኪሮቴ ሩኩንጋ የተመሠረተ የማገገሚያ እና የአእምሮ ህክምና መስጫ ተቋም እንደሆነ ታውቋል።
እንደ ጎርጎርሳውያን በ2021 ዓ. ም. የተመሠረተው ማዕከሉ ኬንያ ውስጥ እጅግ አጣዳፊ በሆኑ ማኅበራዊ ቀውሶች ማለትም በአልኮል እና በዕፅ ሱሶች ምክንያት እየጨመረ የመጣውን የአእምሮ ጤና ተግዳሮቶችን ለማስወገድ የሚጥር መሆኑ ታውቋል። ገዳማውያቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ የቆሰሉትን በፍቅር፣ በምሕረት እና በርኅራኄ ለመፈወስ ባላቸው ተልዕኮ ማዕከሉ ዓላማውን የሚያሳካበት እና ስብራትን በተስፋ የሚጠግንበት አስተማማኝ ቦታ መፍጠራቸው ታውቋል።
በእምነት እና በርኅራኄ የተወለደ ተልዕኮ
እህት ቬሮኒካ ሩኩንጋ ማኅበራቸው ማዕከሉን ለማቋቋም የተንሳበትን ምክንያት ሲገልጹ፥ የ “ሆሊ ኢኖሰንትስ” እህቶች ማኅበር በኅብረተሰቡ ውስጥ በችግር እጅግ የቆሰሉትን መርዳት እንደሆነ ገልጸው፥ ተነሳሽነታቸው ልክ የማኅበሩ አባላት አሁን እንደሚያደርጉት በሱስ እና በአእምሮ ሕመም ከሚታገሉት ጋር እንደቆሙ ሁሉ፥ በተሰቃየው ልጇ አጠገብ ከቆመች ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የመጣ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የ “ሆሊ ኢኖሰንትስ” ማዕከል በአራት ዘርፎች በቀን 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፥ በባዮሎጂካል፣ በሥነ ልቦና፣ በማኅበራዊ እና በመንፈሳዊ ዘርፎች ሙሉ እንክብካቤን የሚሰጥ እና በዚህም ተረጂዎች በአካል ብቻ ሳይሆን በሙሉ ልብ፣ በክብር እና በርህራሄ መታከማቸውን እንደሚያረጋግጥ ታውቋል።
አካልን፣ አእምሮን እና ነፍስን መፈወስ
በማዕከሉ ውስጥ የሚሰጡት አገልግሎቶች ሰፊ እና ሆን ተብሎ የተጀመሩ እንደሆኑ ያብራሩት የማዕከሉ አስተዳዳሪዋ እህት ፑሪቲ ማቴንጌ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያን ከ2021 ዓ. ም. ጀምሮ በሆስፒታሉ ውስጥ የማገገም ዕድል፣ የአእምሮ ህክምና፣ የግለሰብ እና የቡድን ሕክምና፣ የመርዝ ማስወገጃ አገልግሎት እና መንፈሳዊ ምክሮችን መስጠታቸውን አስረድተዋል።
ቡድናቸው የሥነ አእምሮ ሐኪሞችን፣ ነርሶችን፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን፣ የላብራቶሪ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን፣ አማካሪዎችን እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞችን እንደሚያካትት ገልጸው፥ በሆስፒታሉ ውስጥ ሁሉም ሰው ሚና እንዳለው እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ተጨማሪ ሰዎች እንዲቀላቀሏቸው እንደሚጸልዩ እህት ፑሪቲ ተናግረዋል።
ሳይንስ እና ሙያዊ እንክብካቤ ከመንፈሳዊ ፈውስ ጋር ያገናኛሉ
ማዕከሉ የተዋቀረ እና ግላዊ እንክብካቤን እንደሚሰጥ የገለጹት በማዕከሉ ውስጥ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት እና የክሊኒካል አገልግሎቶች ኃላፊ የሆኑት ኬልቪን ሙዌጋ፥ ሕሙማንን በማዕከላቸው ከመቀበላቸው በፊት እንደ ጉበት እና ኩላሊት ላሉ ወሳኝ የአካል ክፍሎች የላብራቶሪ ምርመራዎችን እንደሚያደርጉ ተናግረው፥ በግለሰቡ ፍላጎቶች ላይ በመመሥረት፣ ባዮሎጂካል፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና መንፈሳዊ ድጋፎችን ጨምሮ በሕክምና የታገዘ የመርዝ ማስወገጃ እና የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
“የቤተሰብ ቴራፒ እና የህይወት ክህሎት ስልጠናዎችም የፕሮግራሙ አካል ናቸው” ያሉት ሚስተር ኬልቪን ሙዌጋ፥ ታካሚዎቹ ከማዕከሉ ከወጡ በኋላ በማገገሚያ ጊዜያቸው በቤታቸው ጉብኝት እና ክትትል እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።
“የሚያስደስተኝ ሰዎች ከሕመማቸው ሲፈወሱ ማየት ነው” ያሉት ሚስተር ኬልቪን ሙዌጋ፥ ይህም ተስፋን እና ድፍረትን እንደሚሰጣቸው እንዲሁም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ምንም ዓይነት ችግር ሊወገድ እንደሚችል እና ለማገገም የሚያግዝ ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
ለሌሎች ሚያስብ ማኅበረሰብ
ይህ ሕይወትን የሚቀይር ሥራ ከገዳሙ ውጭ ያሉ በርካታ ሰዎችን በተልዕኮው እንዲቀላቀሉ ማነሳሳቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ከምዕመናን ወገን የሆነው ቪንሰንት ሙትዊሪ ይገኝበታል። የ “ሆሊ ኢኖሰንትስ” ማኅበር እህቶችን እንደሚደግፍ የተናገረው ቪንሰንት ሙትዊሪ፥ቸርነታቸው ልዩ እና አስቸኳይ እንደሆነ ተናግሮ፥ የእርሱ ድርሻ ገዳማውያቱ መድረስ ወደማይችሉበት ቦታ መሄድ እንደሆነ አስረድቷል።
ብዙውን ጊዜ “የሰካራሞች ጓደኞች” ተብለው የሚጠሩበት ስማቸው ገዳማውያቱ በትህትና የተቀበሉት ማዕረግ እንደሆነ ሚስተር ሙትዊሪ ተናግሮ፥ “ፍቅራቸው ሕይወትን የሚያድን መሆኑን ማኅበረሰቡም የሚያየው ነው” ሲል አስረድቷል።
“ብቻችሁን አይደላችሁም!”
በማዕከሉ ውስጥ ተንከባካቢ የሆኑት እህት ጆአን ኒያካቶ፥ ከሱስ ወይም ከአእምሮ ጤና ጉዳዮች ጋር የሚታገሉ ሰዎችን መድረስ እንደሚገባ እና ችግሮቻቸውን ለሌሎች ሰዎች ማጋራት እንደሚገባ አሳስበዋል። “ሁላችንም ጤናማ አእምሮ እና ጤናማ ሕይወት የሚያስፈልገን በመሆኑ ተገናኝተን መነጋገር ያስፈልገናል” ብለው፥ “ችግር ሲያጋጥም የሕይወት ፍጻሜ ባለመሆኑ እና ብቻችሁን ባለመሆናችሁ እጆቻችሁን ይዘን ከችግሮቻችሁ ለማውጣት ዝግጁዎች ነን” ብለዋል። እህት ጆአን አክለውም፥ “ሁሉም ሰው ጊዜውን፣ ሃብቱን ወይም እገዛውን ሊያበረክት ይችላል” ብለው፥ አብረን በመሆን ክፍተቱን መሙላት እና ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችን ከሱስ ነፃ እንዲያወጡ መርዳት እንችላለን” ብለዋል።
ለርህራሄ የቀረበ ጥሪ
ሱስ እና የአእምሮ ህመም ብዙውን ጊዜ መገለልን እና ዝምታን ባስከተለበት ዓለማችን ውስጥ ገዳማውያት እህቶች፣ ሠራተኞቻቸው እና ተባባሪዎቻቸው ኬንያ እና መላው ዓለም ከእግዚአብሔር የማዳን ሥራ የተገለሉ አለመሆናቸውን በማሳየት ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ጥሪያቸው ቀላል እና አስቸኳይ በመሆኑ ጤናማ፣ የተፈወሰ እና ርህሩህ ማኅበረሰብን ለመገንባት እና በአንድ ጊዜ አንድ ሕይወት ለማዳን በኅብረት መጓዝ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።